Sunday, 21 May 2017 00:00

ቀጣዩ የዓለም የጤና ድርጅት መሪ ማክሰኞ ይታወቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(25 votes)

• ዶ/ር ቴዎድሮስ ከ185 በላይ በሚሆኑ አገራት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የፈጀ የምረጡኝ ቅስቀሳ አድርገዋል
• ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ ድጋፍ እና ተቃውሞ ገጥሟቸዋል

ቀጣዩ የዓለም የጤና ድርጅት መሪ በመጪው ማክሰኞ ይፋ የሚደረግ ሲሆን፣ ለመጨረሻው ዙር ከደረሱት 3 ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የተደረገበትና ከ185 በላይ አገራትን ያዳረሰ ሰፊ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ የአፍሪካ፣ የፓሰፊክና የካሪቢያን ሃገራትን ሙሉ ድጋፍ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ግብፅና ኤርትራን ጨምሮ የሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ሙሉ ድጋፍ አግኝተው ለመሪነቱ ቦታ እየተወዳደሩ ቢገኙም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ እና በዲያስፖራ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት ከፍተኛ ተቃውሞና እንዳይመረጡ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ በውጭና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እየተደረገባቸው ከሚገኘው ከፍተኛ ተቃውሞ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ለሦስት ጊዜያት የተከሰተን የኮሌራ ወረርሽኝ ደብቀዋል በሚል ሰሞኑን በኒውዮርክ ታይምስ ላይ የወጣው ዘገባ በውጤታማነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ስጋት መፍጠራቸውም ተጠቁሟል፡፡  
ዶ/ር ቴዎድሮስ በዋናነት ተቃውሞ የቀረበባቸው ከአገራቸው ዜጎች መሆኑን የጠቆመው የግሎባል ቮይስ ድረ ገፅ ዘገባ፤ የተቃውሞ ማጠንጠኛውም ዶክተሩ “የኢትዮጵያን ህዝብ ሳይሆን አምባገነናዊ የሀገሪቱን መንግስት ነው የሚወክሉት፤ የዜጎቹን የሰብአዊ መብት የሚጥስ መንግስት አባል ናቸው፤ ሊመረጡ አይገባም” የሚል መሆኑን ጠቅሷል፡፡
የዶ/ር ቴዎድሮስ ዋነኛ ተፎካካሪ የሆኑት እንግሊዛዊው ዴቪድ ናባሮ አማካሪ፣ ላውረንስ ጎስቲን፣ ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓ.ም በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባቀረበው ሰፊ ፅሁፍ፤ ዶክተሩ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2011 የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በአገሪቱ የተከሰቱ ሦስት የኮሌራ ወረርሽኞችን ሆን ብለው ደብቀዋል ሲል የወነጀላቸው ሲሆን ዶ/ር ቴዎድሮስ ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ በሰጡት ምላሽም፤ ሚስተር ናባሮ ያልተገባ የምረጡኝ ቅስቀሳ መንገድ እየተከተሉ መሆኑን ጠቁመው፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በመጣመር ስሜን እያጠፉ ነው ብለዋል፡፡
ሚስተር ናባሮ በበኩላቸው፤ፅሁፉ በኒውዮርክ ታይምስ ላይ እንዲወጣ አለማዘዛቸውንና አማካሪያቸው በራሱ ፍላጎት እንዳወጣው አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም የዘገበው የሮይተርሱ ጋዜጠኛ ባሪ ማሎን በበኩሉ፤ዶ/ር ቴዎድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ወቅት በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ እንዳይዘግብ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች ጭምር ጫና ተደርጎበት እንደነበር በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡  
በነዚህ ሁሉ ተቃውሞዎች ውስጥ ሆነው የፊታችን ማክሰኞ ለመጨረሻው ውድድር የሚቀርቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ በተባበሩት መንግስታት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት አላቸው የሚባሉት የቀድሞ የእንግሊዝ አለማቀፍ የልማት ተቋም ዋና ሃላፊ የነበሩት አንድሪው ሚሼል፣በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑት የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ቶም ፍሬድ፣ታዋቂው ችሮታ አድራጊ ቶኒ ኤልሙሊን  ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች ድጋፋቸውን ሰጥተው ከጎናቸው መሰለፋቸው ተጠቁሟል፡፡  የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሣ ሣኪም የፊታችን ማክሰኞ በጄኔቭ በሚካሄደው የመጨረሻው የምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ድጋፋቸውን እንደሚገልፁ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና አስር ያህል የጤናው ዘርፍ ማህበራትም፣ዶ/ር ቴዎድሮስ በሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማምጣታቸውን በመመስከር፣ የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ሆነው እንዲመረጡ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
የዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ተፎካካሪ እንግሊዛዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በመስራት ልምድ ያላቸው ሲሆን በኢቦላ ወረርሽኝ መከላከልና  የአለም ጤና ድርጅትን በድንገተኛ በሽታዎች ላይ የሚያማክር ቡድን አባል እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡
ሌላኛዋ ተፎካካሪ ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሣኒያ ኒሽታር በበጎ አድራጎት ስራዎች ሰፊ ልምድ ያላቸውና በሃገራቸውም ሁለት በጤና ጉዳይ ላይ የሚሠሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማቋቋም ይታወቃሉ፡፡ የፓኪስታን የጤና፣ የሣይንስና ቴክኖሎጂ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትርም በመሆን ለሃገራቸው ያገለገሉት ዶ/ር ሣኒያ፤በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥም ከሴቶችና ህፃናት ጋር በተያያዘ ሃላፊነቶች ሰርተዋል፡፡ በአለም ጤና ድርጅት ውስጥም የህፃናት ውፍረትን መከላከል ኮሚሽን ውስጥ ተባባሪ ሊቀመንበር ሆነው መስራታቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ድረ ገፅ ያሠፈረው መረጃ ይጠቁማል፡፡
አፍሪካን በወከሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም፣ በእንግሊዛዊው ዴቪድ ናባሮ እና በፓኪስታናዊቷ ሳኒያ ኒሽታር መካከል ለወራት ሲካሄድ የቆየው የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ለመሆን የሚደረገው ፉክክር፣ ከ4 ቀን በኋላ የፊታችን ማክሰኞ በሚከናወን የመጨረሻ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት አሸናፊው ይታወቃል ተብሏል፡፡    

Read 7589 times