Sunday, 21 May 2017 00:00

እንሰበሰባለን፣ እናጨበጭባለን ‘እንክት አድርገን’ እንበላለን!

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው መሥሪያ ቤት ውሎ ቤቱ ይገባል፡፡ መሥሪያ ቤት ደግሞ ስብሰባ ነበር፣ ለሦስተኛ ቀን። ቤቱ ሲገባ ሚስት ሆዬ ግንባሯን ከስክሳ “ማነሽ፣ እራት አቅርቢለት…” ብላ የአቴዝና ባህርን  መጨረሻ ለማየት ቴሌቪዥኗ ላይ ማፍጠጥ፡፡
እሱ ሆዬ “ኤሊፍን ስንገላገል ባህር የሚሏት መጣችብን!” እያለ ቀመስ፣ ቀመስ አድርጎ መኝታ ቤት ይገባል፡፡ የዕለት ማስታወሻውን ያወጣል…ይጽፋልም፡፡ ይሄ የዕለት ማስታወሻ ከዕለታት አንድ ቀን ‘ለልማት ተብሎ የሚፈርስ ጎጆ ስር’ (ቂ…ቂ…ቂ…) መገኘቱ አይቀርም፡፡ ቀኑ ይጻፋል፣ ይጀመራልም፡፡
ደከሞኛል በጣም ደክሞኛል፡፡ ሰሞኑን በስብሰባ ተንበሸበሽናል፡፡ የስብሰባ ብዛት አንገት ቀና የሚደረግ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ አንገታችን ፕሉቶ ማዶ አዲስ ወደተገኘችው ፕላኔት ይደርስ ነበር፡፡ ምን ላድርግ፣ ልቀልድ እንጂ!
በአሁኑ ሰዓት የምፈልገው መኝታዬ ውስጥ ገብቼ ጥቅልል ብዬ መተኛት ነበር፡፡ ግን የዕለት ማስታወሻዬን መጻፍ አለብኝ፡፡ ምክንያቱም…እንደ እውነቱ አሁን ስምንተኛው ሺህ ለመድረሱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስምንተኛው  ሺህ ባይደርስ ኖሮ እንዲሀ መጫወቻ አንሆንም ነበራ!
የአዳራሹ ግድግዳ ጨርቅ ላይ በተጻፉ መፈክሮች ተዥጎርጉሯል፡፡ ጠረዼዛው በባንዲራና በወረቀት መፈክሮች ተብለጭልጯል፡፡
‘የተጀመረውን ልማት አጠናከረን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንሠራለን…’ ይላል ትልቀኛው መፈክር። ደግነቱ “እስከ ዛሬ የምትሠሩት በቁርጠኝነት አልነበረማ!” ብሎ የሚመጣ ቢኖር ምን እንል ይሆን ብሎ የሚጨነቅ የለም፣ ጠያቂ አይኖርማ!  የጊዜው የስብስባ ‘ኮምፐልሰሪ’ መፈክር ከተለጠፈ በቂ ነው፡፡  ስብሰባ አዳራሹ በሰው ጢም ብሏል…‘የቀረ ሰው ይጠቆራል’ ስለተባለ የቀረ የለም፡፡ በሰበብ አስባቡ የሚያስጠቁር በበዛበት ዘመን ማን ጥርስ ውስጥ ይገባል! ደግሞ ዘንድሮ ስብበሳ አዳራሽ የምንቀመጠው እየበዙ በሄዱ ‘መለኪያዎቻችን’ በመፈላላግ ሆኗል፡፡ እንደ አንድ መሥሪያ ቤት የሥራ ባልደረቦች ሳይሆን እንደ ቤተ ዘመድና እንደ ‘አገር ልጅ’ ተፈላልገን ትከሻ ለትከሻ መግጠም የጋራ መግባቢያ አይነት ነገር የሆነ ይመስላል፡፡ በተለይ ይቺ ‘የአገር ልጅነት’ መፈላለግ በየስፍራው እየገባች ግራ እያጋባችን ነው፡፡
ሦስት ሰዓት የተጠራው ስብሰባ አራት ሰዓትም አልተጀመረም፡፡ የክብር እንግዳው አልመጣማ! የእሱ መክፈቻ ንግግር ከሌለበት ስብሰባው ለአቅመ የምሽት ዜና አይበቃማ!
አብዛኛውን ጊዜ የክብር እንግዳ የሚባሉት ወይ የመሥሪያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ወይም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ቆይማ…ሰዎቹ በድርጀቱ ፔይሮል ላይ እየፈረሙ ደሞዝ የሚነጩ ሠራተኞች አይደሉም እንዴ! ታዲያ ‘የክብር እንግዳ’ የሚለው ቅጥያ ምን አመጣው! በገዛ ቤታቸው!
እንደዛም ሆኖ ሰዓት አክብሮ ቢመጣ ጥሩ፡፡ እሱ ልክ ለአራት ሰዓት ሰባት ደቂቃ ሲቀረው ይመጣል፡፡ (አርፍዶ መምጣት ‘የክብር እንግድነት’ አንዱ መለያ የሆነ ይመስላል፡፡) እናማ…ጭብጨባ ይጀመራል። ከበሩ ጀምሮ መቀመጫው እስኪደርስ ድረስ በጭብጨባ እናጅበዋለን፡
የሰለቸኝ ይሄ ጭብጨባ ነው፡፡ የአሥር ሺህ ሜትር ሬከርድ አልሰበረ!… ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች አልገባ! በቃ፣ እንደኛው የድርጅቱ ቅጥር ሠራተኛ ነው፡፡ እንደውም በየቢሯችን ስለ እሱ የምንንሾካሾከው ነገር አደባባይ ቢወጣ፣ ካሊም ተከናንቦ ቤቱ ይከረቸም ነበር፡፡ ለነገሩ አብዛኞቻችን የምናጨበጭበው ‘ላለመጠቆር’ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ሲያጨበጭብ እኛ ዝም ብለን ከቆምን አለቀልና! የዚህ አገር ነገር እንደዚህ ሆኗላ! “ትጉህ ሠራተኛ ነው?” ከማለት ይልቅ “ትጉህ ደጋፊዬ ነው?” የሚለው ጥያቄ ይቀድማላ!
ቀጥሎ የስብሰባ መሪው የአስተዳደርና የፋይናንስ ኃላፊው ወደ መናገሪያው ሲሄድ እሱንም በጭብጨባ እናጅበዋለን፡፡ ቲማቲም ሲወደድ ጭብጨባ የረከሰባት አገር! …ቂ…ቂ…ቂ…
መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የምድር ኑሯችንን የገሀነም የሰቆቃ ኑሮ አደረግብን የምንለው አንዱ የአስተዳደርና የፋይናንስ ኃላፊው ነው፡፡ የስብሰባ መሪ ሆኖ ሳንወድ ያስጨበጭበናል! እሱ በ‘ውሀ ቀጠነ’ ደሞዝ የቆረጠብን ሰዎች ብንሰባሰብ አንድ ዕድር መመስረት እንችላለን፡፡ የዛሬ ዓመት የደሞዜን እሩብ ሲገነድስብኝ “ሆድ ይፍጀው” ብዬ ዝም ብያለሁ፡፡ ዝም ባልልስ ምን እንዳላመጣ!
ጉሮሮውን አሥር ጊዜ ያጠራል፡፡
ታዲያላችሁ…የክብር እንግዳውን ልክ በሆነ ነገር ኦስሎ ላይ የኖቤል ሽልማት ተሸልሞ የተመለሰ ይመስል አናታችን ላይ ይቆልለዋል፡፡ “ውድ ጊዜዎን ሰውተው በዚህ ስብሰባ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘትዎ በድርጅቱ ሠራተኞችና በራሴ ስም የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፣...” ይላል፡ እንደፈረደብን አዳራሹን በጭብጨባ እናናጋዋለን፡፡ ወይም… ‘ከስብሰባ የቀረ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰድበታል’ የሚለው ማስጠንቀቂያ ተሻሽሎ… ‘ከስብሰባ የቀረ፣ ተገኝቶም ያላጨበጨበ’ በሚል ይስተካከል፡፡ ሌላ ጊዜ “በቃሪያ ጥፊ ባጠናገርኩት እንዴት ደስ ይለኝ ነበር!” የምንለውን ሰው በጭብጨባ ትከሻው ላይ የኮከብ መአት እንደረድርለታለን፡፡
ሌላው ደግሞ ሥራ አስኪያጁ “ውድ ጊዜዎን ሰውተው…” ብሎ ነገር ምን ማለት ነው! እሱም እንደ እኛ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኛ አይደለም እንዴ!….የእሱ ጊዜ ‘ውድ’ ሲሆን የእኛ ‘ርካሽ’ ነው ማለት ነው! እናማ…ብዙ ጊዜ የክብር እንግዶች ለስብስባው የሚያመጡት የተለየ ግብአት የለም፡፡ ያው “የዛሬውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው…”
“በተያያዝነው የእድገት ጎዳና…”
“ከመካከለኛ ገቢ አገሮች ጎን ለመሰለፍ…ምናምን የሚሉ ሀረጋትን መደርደር ነው፡፡
የእኛም ሥራ አስኪያጅ ሁሉም በገዛ ድርጅታቸው ‘የክብር እንግዳ’ የሆኑ ሥራ አስኪያጆች የሚያደርጉት ንግግር ይደርጋል፡፡ በአንድ ሺህ አንድ ችግሮች የተተበው መሥሪያ ቤታችን፤ “በእውነቱ የሠራተኛው የሥራ ፍላጎትና ትጋት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው፣” ይላል፡፡ ምነው፣ ስንተዋወቅ! የእኛ ድርጅት ለሌላው ምሳሌ ከሆነ፣ በርከክ ያለች አገር አንደኛዋን በእንትኗ ዘጭ ነው የምትለው፡፡
ሌላ ግራ የሚገባኝ ነገር ደግሞ የዘንድሮ ‘የስብሰባ ቋንቋ!’ “መሥሪያ ቤቱ የእድገት አጀንዳውን ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ሆኖ ለስኬት ለማብቃት…” ምናምን የሚሉት ፈሊጥ አለ፡፡ እኔ የምለው…ለምን በሌላ አቀራረብ ሊሉት አይሞክሩም! ለምን ድግምግሞሽ እንደሚያሰለች አውቀው ለየት ለማለት አይሞክሩም! ሁሉም ሰው “ደመቅሽ አበባዬ…” እያለ መዝፈን አለበት እንዴ! አሀ… አንዱ “ደመቅሽ አበባዬ…” ካለ ሌላኛው  “አገሯ ዋርሳ መገና…” ለምን አይልም!
ስብሰባው ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነበር፡፡ ነገ ያልቃል ተብሏል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ትናንት ከ‘በላይ አካል’ ምን እንደተባለ እንጃ ዛሬ ሲያንጫጫን ዋለ፡፡ ስብሰባውን ሲከፍት ለሌሎች ምሳሌ እንደምንሆን ሲነግረን የነበረ ሰው፣ ዛሬ ቀኝ ኋላ ዞሮ የእኛንም ናላ አዞረው፡፡ “በዘንድሮ ዓመት ድርጀቱ የእቅዱን ሀምሳ ሦስት ነጥብ ሰባት በመቶ አሳክቷል፡፡”
አጨበጨብን፣ ልባችን እስኪጠፋ አጨበጨብን። ምን! ለሀምሳ ሦስት በመቶ ጭብጨባ! እንደውም ከእቅዳቸው ከሰማንያ በመቶ በታች የሚያስመዘግቡ ሁሉ አይደለም ማጨብጨብ በሀዘን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ማድረግ ነበረባቸው፡፡
ከዚያም አለቃችን “በመሆኑም፣ ድርጀቱ በዚህ ዓመት ቦነስ መስጠት አይችልም፡፡”
አናጋነዋ! አዳራሹን በተቃውሞ ጫጫታ አናጋነዋ! አይደለም ሀምሳ ሦስት ለምን ሀያ ሦስት በመቶ አይሆንም… ለምንድነው ቦነሳችንን የሚከለክሉን! ለእሱ በየወሩ መኪና ይለዋወጥለት የለ እንዴ! በዓመት ውስጥ የቢሮው ምንጣፍ ስንቴ ነው የተለወጠው!  ለሥራ ጉዳይ ተብሎ ስንት አገር እየዞረ ሲዝናና ከርሞ የለም እንዴ!  
ይሄ ሁሉ ገንዘብ ከየት መጣ?
ማጉረመረማችን ጠንከር ሲል አለቃችን… “ይህ እኮ የስብሰባ ቦታ ነው፣ መርካቶ አይደለም..” ብሎ ሲቆጣ በአብዛኛው ድምጻችን ቀነሰ፡፡ ጥቂት ሰዎች ግን ማጉረመረማቸውን ቀጠሉ፡፡ ይሄኔ… “እዚህ አዳራሸ ውስጥ ሆነ ብለው ስብሰባውን ለመረበሽ የሚፈልጉ የእነእንትና ተላላኪዎች አሉ…” ሲል የሰፈነው ጸጥታ ትንኝ ብታነጥስ ይሰማ ነበር፡፡ ነገ ስብሰባው ይዘጋል፡፡ ምን በሚባል ሆቴል የእራት ግብዣ አለን ተብሏል፡፡
“ለእኛ ቦነስ የጠፋ ገንዘብ ለግብዣ ከየት መጣ?” ብለን አንቃወምም፡፡“ከእቅዳቸን ሀምሳ ሦስት በመቶ ብቻ አሳካን ተብሎ የምን በገንዘብ ጨዋታ ነው!” አንልም፡፡
“ለእራት የሚወጣው ገንዘብ ለተሰባበሩት ወንበሮችና ጠረጴዛዎች መጠገኛ አይውልም!” አንልም፡፡
እንበላለን፡ እንጠጣለን፡፡ የአለቆቻችንን የዘወትር ኑሮ እኛ በዓመት አንድ ምሽት ብናየው ምናለበት!
ደግሞ…አይ ባለቤቴ እየመጣች ነው፡፡ ይበቃኛል። ምነው የእሷ ፊትም እንደኔው ቀጨመ! ያ አቴዝ ባህርን ደግሞ ምን አድርጓት ይሆን! ልጄ… ስንት የደላው አለ!
እንግዲህ ይኸው ነው… እንሰበሰባለን፣ እናጨበጭባለን ‘እንክት አድርገን’ እራት እንበላለን! ቀን በነገር የምንሞላው ሳያንስ… ማታ በእራት ‘ሆዳችንን የሚሞሉልን’ እንደ ቦነስ እየቆጠሩት ይሆን እንዴ!
እንዲህም ሆኖ የዕለት ማስታወሻው ተገባደደ፡፡ አራት ነጥብ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7694 times