Sunday, 21 May 2017 00:00

‘ገለልተኛ’ እና ትርጉሙ፣ ... የፓርቲዎችን ድርድር አፈረሰ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

  ‘ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በአንዲት ቃል ትርጉም መግባባት አቃታቸው?!
በመገረም፣ “ይሄ ሊሆን አይችልም” እንዳንል፤... ነገርዬው አዲስ ‘ፈጠራ’ አይደለም። ‘ኑ... ኑ... እንወያይ፣ እንስማማ’... እያሉ ሲሰባሰቡ፣ ብዙ ጊዜ ተመልክተናል። በአንዲት ቃል ሰበብ ተወዛግበው፣ መደማመጥና መግባባት ተስኗቸው ሲፋረሱም ታዝበናል። ለዓመታት መላልሰን ያየነው ድራማ ስለሆነ፤... የፓርቲዎቹ  አለመግባባት፣ ፀብና ጥል፣ ብርቃችን አይደለም፤ ብዙም አይደንቀንም።
ቢሆንም፣ የሆነ የሚገርም ነገር አለው። በአንዲት ቃል ትርጉም እየተነታረኩ መበታተን፤ ምን የሚሉት ‘እርግማን’ ነው? በባቢሎን ቋንቋ ነው እንዴ የሚነጋገሩት?
እንግዲህ አስታውሱ። አገሪቱ፣ አምና በቀውስና በትርምስ ከተናወጠች በኋላ ነው፤ “ኑ፣ እንደራደር... ኑ፣ እንወያይ...” የሚል ሃሳብ የመጣው። ሲነገር ቀላል ይመስላል። ለካ፣ ቀላል አይደለም። ‘ማን ከማን ጋር ይደራደራል?’ በማለት በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወዛግበዋል። ተቃቅረውም በየፊናቸው ተቧድነዋል። በመረጡት አላማ የሚለያዩ፣ ወይም በሚያዘወትሩት ዝንባሌ ለየቅል ከሆኑ፤ ‘በግድ አንድ ላይ ካልተጨፈለቃችሁ!’ ልንላቸው አይገባም። እንደየ አላማቸውና እንደየ ዝንባሌያቸው ቢቧደኑ፣ ሃጥያትም ነውርም አይደለም። ይልቅስ፣ በዘር ተወላጅነትና በሃይማኖት ተከታይነት፣ በጭፍንና በጅምላ መቧደን ነው፣ ነውርና ሃጥያት።
ለማንኛውም፣ ውዝግቡ በዚህ አላበቃም። ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በተናጠልም ሆነ በቡድን፣ ሌላ ውዝግብ ለመፍጠር ጊዜ አልፈጀባቸውም። “ድርድሩን ወይም ወይይቱን ማን ይምራው?” የሚል ጥያቄ ተነስቶ፣... “በገለልተኛ አደራዳሪ እናምጣ!... አይ፣ ከፓርቲዎች የተውጣጣ አደራዳሪ ብንሾም ይሻላል” የሚል ክርክር ውስጥ ገቡ። ‘ማሟሟቂያ ድርድር’፣ ‘ሚኒ-ውይይት’ ተጀመረ ማለት ነው። ታዲያ፣ የፓርቲዎቹ ሚኒ-ውይይት፣... ጉዳያቸውን በማስረጃ የሚያስረዱበት፣ አይን ያለው ውይይት አይደለም - ጭፍን መደናቆር እንጂ። ጥቅምና ጉዳትን እያነፃፀሩ የሚያስረዱበት፣ ሚዛን ያለው ድርድርም አይደለም - ከንቱ ንትርክ ብንለው ይሻላል።
“ገለልተኛ ሰው የለም። በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ የሆነ ባለሙያ የለም። ቢኖርም አያስፈልግም”... በማለት ተከራከሩ የአንደኛው ፓርቲ ተወካዮች።
እና፣ ድርድሩን ማን ይምራው?
“ተደራዳሪ ፓርቲዎች በጋራ ድርድሩን ይምሩት። ከፓርቲዎች የተውጣጡ ሰዎች፣ በሰብሳቢነት እየተፈራረቁ እንዲመሩ ካደረግን፣ ድርድሩ ውጤታማ ይሆናል። ‘ገለልተኛ ባለሙያ’... የሚለው አባባል ግን ዋጋ የለውም።”... ይሄ የአንደኛው ፓርቲ ተወካዮች መከራከሪያ ነው።           
የተቀናቀኝ ፓርቲ ተወካዮች በዚህ አልተስማሙም። “ያለገለልተኛ ባለሙያ፣ ድርድሩ አይሳካም” ብለው ተከራከሩ። “ገለልተኛ ባለሙያ ሞልቷል። ውጤት የምናገኘው፤ ገለልተኛ ባለሙያ ድርድሩን ሲመራ ብቻ ነው። ... ተደራዳሪ ፓርቲዎች፣ ራሳቸውን እንዲሸመግሉና እንዲዳኙ መጠበቅ፣ የማይመሰስ የይስሙላ አባባል ነው። ከንትርክ ያለፈ ውጤት አያስገኝም”።... በማለት ተከራክረዋል - የዚህኛው ፓርቲ ተወካዮች።
ለሳምንታት ይህኑን ንትርክ ሲያጯጩሁ የከረሙት የአገራችን ፓርቲዎች፣ የሚያግባባ ሃሳብ ላይ ለመድረስ አልቻሉም፤ ወይም አልፈለጉም። በዚሁ ሰበብም፣ የኢህአዴግና የገሚሶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር፣ ገና ከመጀመሩ ፈረሰ።
ጥፋተኛው ፓርቲ የትኛው ነው?
በአንደኛው ፓርቲ ወይም በሌላኛው ላይ ለመፍረድ አትቸኩሉ። ፓርቲዎቹ ሃሳብ አስቸጋሪ ነው። ልያዝህ ቢሉት፣ እሺ አይልም። ሙልጭልጭ እያለ ያመልጣል፤ እየተከረባበተ ይለዋወጣል። በድርድሩ ዙሪያ፣ የፓርቲዎቹ ሃሳብ በግልፅ አይታወቅም ማለቴ አይደለም። ይታወቃል። አንደኛው ወገን “ገለልተኛ ማለት፣ ከንቱ ቅዠት ነው” በማለት አጣጥሏል። ሌላኛው ወገን ደግሞ “ገለልተኛ ማለት፣ ፍቱን መድሃኒት ነው” በማለት አወድሷል። የ“ገለልተኛ” ቲፎዞና ተቃራኒ ሆነው ተከራክረዋል። ነገር ግን...
“የፓርቲዎችን ድርድር ማን ይምራው?” የሚለው ጥያቄ ተቀይሮ፤ “የፓርቲዎችን የምርጫ ፉክክር ማን ይምራው?” በሚል ጥያቄ ከተተካ፤ በፓርቲዎቹ ሃሳብ ምን እንደሚሆን ተመልከቱ።
የፓርቲዎቹ አቋም፣ በአፍ ጢሙ ይገለበጣል። አዎ፤ አቋም መለወጥ ነውር አይደለም። ግን፣ አቋማቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የቃላትን ትርጉም ለመለወጥ ነው የሚፈልጉት።
“ገለልተኛ ሞልቷል! ገለልተኛ ማለት፣ ፍቱን መፍትሄ ነው!” በማለት ሲጮሁ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ “ገለልተኛ ብሎ ነገር የለም! ገለልተኛ ማለት፣ ከንቱ ቅዠት ነው!” በማለት ያጣጥላሉ - የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ሲነሳ።
“የምርጫ ቦርድን የሚመሩ ሰዎች፣.. ከፓርቲዎች የተውጣጡ ተወካዮች መሆን አለባቸው” በማለት ይከራከራሉ - በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች።
ኢህአዴግም እንዲሁ፤ አቋሙን ለውጦ ‘ይከረበታል’። ከዚህም ጋር፣... የቃላትን ትርጉም፣ እንዳሻው መከርበት የሚችል ይመስለዋል። “ገለልተኛ ሰው የለም። ቢኖርም፣ ገለልተኛ ማለት፣ ከንቱ ነው!” በማለት ሲከራከር የሰነበተው ኢህአዴግ፤... “የምርጫ ቦርድን የሚመሩ ሰዎች፣ ገለልተኛ ባለሙያዎች መሆን አለባቸው” በማለት ይደሰኩራል። “ገለልተኛ ባለሙያዎች ደግሞ ሞልተዋል”! በማለትም ለማሳመን ይጣጣራል - ኢህአዴግ።
በአጭሩ፤ በአገራችን ፓርቲዎች ዘንድ፣... ቃላት “እውነት”ን፣ “እውቀት”ን የሚወክሉ መሆናቸው ቀርቷል። ቃላት፣ እንዳሻን “የምንከረባብታቸው” የቁማር መጫወቻ ካርዶች ሆነዋል።       
ይህንን በማየት የሚያዝን፣... በዚህ ክስተት የሚገረም፣... ሰው ካለ፣ ጥሩ ነው። ለብዙዎቻችን ግን፣ “ቃላት”... መጫወቻ መሳሪያ ሲሆኑ ማየት፣... “ኖርማል” ነው። አለመግባባትና መደናቆር፤ መወዛገብና መበታተንም፣ “ኖርማር” ናቸው። በእርግጥም፣ የቃላት ፍቺ፣ ከተጨባጭ እውነታ ጋር ከተፋታ፣... የቃላት ትርጉም እንደፓርቲዎች ስሜት የሚከረባበት የሚለዋወጥ ተለጣፊ ከሆነ፣... እንዴት መግባባት ይቻላል? አይቻልም።    
  በባቢሎን ቋንቋ ተደናቁሮ መበታተን!
በቃላት መቆመርና አክሮባት መስራት፣ እንደ ‘ኖርማል’ ከመታየት አልፎ፣ እንደ ብልሃትና እንደ ብልጠት ነው የሚቆጠረው - በብዙዎቻችን ዘንድ። የምንቃወመው ፓርቲ፣ ምንም ይበል ምን፣ ሁሌም እንቃወመዋለን። የምንደግፈው ፓርቲ፣ ምንም ይበል ምን፣ ችግር የለውም። ሺ ጊዜ ‘ቢከረበት’፣ ታማኝ ‘ቲፎዞ’ እንሆንለታለን። በነገረን ሁሉ መስማማት፣ በሰማነው ሁሉ ማጨብጨብ ነው ሆኗል ስራችን።  በሌላ አነጋገር፣ የቃላት ቁማር ምርኮኛ፣ የጨዋታው የዘወትር ደንበኛ ነን - በተሳታፊነት፣ በቲፎዞነት ወይም የዳር ተመልካችነት።
የቃላት ጨዋታ ምርኮኛ ካልሆንን፣ ወይም ድንገት ከባነንን ግን፣... የፓርቲዎቹ ውዝግብ፣ አስገራሚ፣ ከዚያም አሳሳቢ እንደሚሆንብን አያጠራጥርም። በእርግጥ፣ ውዝግቡ ለአፍታ አስቂኝ ሊሆንብን ይችላል - ግን ለአፍታ ብቻ ነው። ጉዳዩ ‘ቀልድ’ አይደለማ። መዘዙም ክፉና ብዙ ነዋ። ቢሆንም፣ “በአንዲት ቃል ትርጉም መግባባት ተሳናቸው?!” ብንል... “ወይ ጉድ! አጃኢብ ነው! በባቢሎን ቋንቋ መደናቆር ይሉሃል እንዲህ ነው”! ብንል፣ እያጋነንን አይደለም።
በእርግጥ፣ “የባቢሎን ቋንቋ”፣ ቅሬታ ሊያሰማ ይችላል። “ስሜን አታጥፉ” ብሎ ቢመጣብን አይፈረድበትም። “የባቢሎን ቋንቋ”፣ “እኔ፣ የመደናቆር ቋንቋ አይደለሁም” ብሎ ለማስረዳት የሚከብደው አይመስለኝም። ‘ከፈለጋችሁ፣ መዝገበ ቃላትን ተመልከቱ’ ሊለን ይችላል - “የባቢሎን ቋንቋ”። መዝገበ ቃላት?
መዝገበ ቃላት? አሁን ገና፣ ሁነኛ መፍትሄ ብልጭ አላለላችሁም?
“ኑ... ኑ... እንደራደር፤ እንግባባ” ብለው የተሰባሰቡት የአገራችን ፓርቲዎች፣ በአንዲት ቃል ትርጉም ተወዛግበው ቢበታተኑ፤ ከእንግዲህ ችግር የለውም። ፓርቲዎቻችን፣ የቃላትን ትርጉም ሲከረብቱ ቢከርሙ እንኳ፣ መፍትሄው ቀላል ነው። የትኛው ትክክል፣ የትኛው ስህተት እንደሆነ፣ እርግጡን መለየት አይከብደንም። ቢከብድ ቢከብድ፤... መዝገበ ቃላት ገልጦ ማመሳከር ነው። አይደለም እንዴ? በቋንቋና በቃላት መግባባት ላቃታት አገር፣ ሁነኛው ፈውስ፣... በቃላት ቁማር በሚወዛገቡ ፓርቲዎች ሳቢያ ለምትናጥ አገር፣ ፍቱኑ መድሃኒት፣... መዝገበ ቃላት ይሆናል ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ?
በዚህችው አጋጣሚ፤ እስቲ፣... በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ መዝገበ ቃላትን በቅጡ በማዘጋጀት ቀዳሚዎቹ እንደማን እንደሆኑ ገምቱ። የባቢሎን ምሁራን ናቸው። ለነገሩ፤ ያለ እውቀትና ያለ ቃላት፣ የስልጣኔ ቀዳሚ መሆን አይቻልም። የባቢሎን ጠበብቶች የስልጣኔ ቀዳሚ የሆኑትን ያህል፤ መዝገበ ቃላትን በስፋትና በብዛት በማዘጋጀትም፣ ከሌላው ዓለም፣ በሺ ዓመታት ይቀድማሉ። የባቢሎን ቀዳሚነት፣ 4000 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።
በቃላት መግባባት ተስኗቸው የተደናቆሩ፣ መስማማት አቅቷቸው የተፋረሱ፣ መከባበር ርቋቸው የተበታተኑ የባቢሎን ሰዎች፤... መዝገበ ቃላት ነበራቸው? “ነበራቸው” ብንል፣ ክብራቸውን ዝቅ እናደርገዋለን። በየአይነቱ የተዘጋጁ በርካታ መዝገበ ቃላት፣... ለምሳሌ፣ የሙያ አይነቶችን የሚዘረዝር መዝገበ ቃላት፤ የሕግ መዝገበ ቃላት፤... በሁለት ቋንቋ (በጥንታዊው ቋንቋና በባቢሎንኛ...) የተጠናቀረ መዝገበ ቃላት... በየአይነቱና በብዛት፣ ድንቅ መዝገበ ቃላት ተዘጋጅተዋል - በባቢሎን አገር። የዛሬ 3000 ዓመት ገደማ የተዘጋጁ ሁለት የተለያዩ መዛግብተ ቃላትን መጥቀስ ይቻላል።
አንደኛው መዝገበ ቃላት፣ በ42 ክፍል፣ ከ14ሺ በላይ ቃላትን ከነትርጉማቸው የሚዘረዝር ነው። ሌላኛው በጥራትና በብዛት ተዘጋጅቶ የተሰራጨው መዝገበ ቃላት ደግሞ፣ 10ሺ ገደማ ቃላትን ይዘረዝራል። (Philosophy before the Greeks, The Pursuit of Truth in Ancient Babylonia, Marc Van De Mieroop, Princeton and Oxford University ገፅ 35 እስከ 87።... በነገራችን ላይ፣ በ300 ገፅ ገደማ የታተመው ይሄ መፅሐፍ፣ አዲስ ነው። የኢንተርኔት ዘመን አንዱ ጥቅም ይሄው አይደል? በአለማችን ቁንጮ ዩኒቨርስቲዎች አምና ያሳተሙት ድንቅ የጥናት መፅሐፍ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ማንበብ መቻል!)
የሆነ ሆኖ፣ በባቢሎን ምድር፣ የዛሬ አራት ሺ ዓመት፣ የፅሁፍ እውቀትና ጥበብ ያበበው፤ የፅሁፍ ነገር ቀላል ስለሆነ አይደለም። በሰው ልጅ ታሪክ ቀዳሚ የሆነው የፊደል ዓይነት በመጠቀም ፅሁፍን ያስፋፉት የባቢሎን ፀሐፊዎች፣ እነዚያን ሁሉ መዝገበ ቃላት ያዘጋጁት፣ በወረቀት ላይ አይደለም። ብራና ላይም አይደለም። ሐውልት ላይ እና የጭቃ ሸክላ ላይ እየፃፉ ነው፤ እውቀትንና ስነፅሁፍን ያስፋፉት።የባቢሎን ሰዎች፣ ‘አዲስ ነገር የለመደና አዲስ ችሎታ ያገኘ ሕፃን’ አይነት ናቸው። ቀን ከሌት ያለእረፍት ሲፅፉ የነበሩ ይመስላሉ። የባቢሎን እህት ከተማ (ወይም ተፎካካሪ ከተማ) የነበረችውን ነነዌ ማየት ይቻላል። ማየት እንኳ አይቻልም። እንደባቢሎን ተቃጥላ ፈራርሳለች። ከአፈር ክምር ስር፣ በቁፋሮ ከተገኘው ቤተመፃሕፍት ውስጥ ግን፣ ከ25ሺ በላይ ሰነዶች ወጥተዋል። ከእነዚህም ውስጥ፣ 900 ያህሉ የመዝገበ ቃላት ሰነዶች ናቸው። ተዓምረኛ ሰዎች!
ወደ ቃላት ቁማር? ወደ እንጦሮጦስ!
እንግዲህ አስቡት፤ 10ሺ ቃላትን ከነትርጉማቸው በ24 ሸክላዎች ማስፈርና መሰነድ፣ ድንቅ አይደለም? እነዚህን በብዛት እያዘጋጁ ለባቢሎን ከተሞች ማሰራጨት! ዝርዝሩ ‘ድንቅ ነው፣ የሰው ልጅ አቅም’ ያሰኛል። 13ኛው ሸክላ ላይ አራት መቶ ያህል የቤት እንስሳትን ይዘረዝራል። 14ኛው ሸክላም አራት መቶ ያህል የዱር እንስሳትን ያስተዋውቃል።... ይቀጥላል የቃላትና የትርጉማቸው ዝርዝር።
ታዲያ፣ መዝገበ ቃላትን በማዘጋጀት የአለም ቀዳሚ የሆኑት የባቢሎን ሰዎች፣ እንዴት በቃላት መግባባት አቅቷቸው ተበታተኑ?
13ኛውን የመዝገበ ቃላት ሸክላ ተመልከቱ። በሸክላው ከተዘረዙት አራት መቶ ያህል የቤት እንስሳት መካከል፣ በርካታ የበግ ዓይነቶችን እናገኛለን። የበግ አይነቶችን በፆታና በእድሜ በየክፍላቸው ተሰድረው መቅረባቸው፣ መልካም ነው። ነገር ግን፣ ከ180 የበግ አይነቶችን ወደ መዘርዘር መግባት ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። ጥቁር በግ፣ ነጭ በግ፣ ቀይ በግ፣ ብጫ በግ፣ ጠቃጠቆ በግ፣ አመዳማ በግ፣ የሁለት ዓመት በግ፣ አንበሳ የበላት በግ፣ ቀበሮ የበላት በግ፣ አምላክ የበላት በግ፣... 180 የበግ አይነቶች ተዘርዝረዋል።
ይህም ብቻ አይደለም።  
እህል ለመስፈር፣ ውሃ ለመቅዳት፣ አረቄ ለመለካት፣ ቡና ለማፍላት ጀበና፣ ቡና ለመጠጣት ሲኒ ... (መጠጫ፣ መስፈሪያ፣ መለኪያ፣... የሚሉ ቃላትን መጠቀም ተገቢ ነው። ጋን፣ እንስራ፣ ደንበጃን፣... እንደየመጠናቸውና እንደየአገልግሎታቸው ለይቶ ማወቅም እንዲሁ ጥሩ ነው። ነገር ግን ለእህል መስፈሪያ፣ ለአረቄ መለኪያ የተለያዩ ቃላት ስለተበጁ ብቻ፤... እንዳሻን በዘፈቀደ ቃላትን የሚፈለፍሉ ሰዎች ከመጡ፤... ‘የአሳማ መስፈሪያ’፣ ‘የአህያ መለኪያ’፣ ‘የዝሆን ማፍያ’... የሚሉ በእውን የሌሉና ሊኖሩ የማይችሉ ቁሳቁሶችን በምናብ ብቻ እየፈጠሩ፣ በመቶ የሚቆጠሩ አዳዲስ ቃላትን መፈልፈል ምን ይባላል? ከ300 በላይ የመስፈሪያ ዓይነቶች ተዘርዝረዋል - በባቢሎን መዝገበ ቃላት! የበሬ መስፈሪያ እንስራ?!
ይሄ የጤና አይደለም።
ግን፣ አላዋቂዎች የሚፈፅሙት ስህተት አይደለም። ያወቁ ሰዎች ናቸው ይህንን የሚፈፅሙት። የአጋዘን መስፈሪያ ጋን የሚል ትርጉም የተለጠፈለት አዲስ ቃል የፈጠሩት፣... እንዲህ አይነት ነገር እንደሌለና እንደማይኖር ስለማያውቁ አይደለም። በቃ! እያወቁ በድፍረት የፈፀሙት ጥፋት ነው።
የአገራችን ፓርቲዎች የቃላት ቁማር፣ የእኛም ምርኮኛነት፣... ከእውቀት እጦት የመነጨ ስህተት አይደለም። እያወቁ በድፍረት የሚፈፀም ጥፋት እንጂ!

Read 2460 times