Saturday, 20 May 2017 12:32

የወግ መጣጥፍ

Written by  በላዕከማርያም ልሳነወርቅ
Rate this item
(0 votes)


“መጣች ውላ ውላ
መጣች ውላ ውላ
መቸም አይሰፈር
አይለካም ብላ፡፡ “  አለ አንዱ ቆለኛ
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ይህ ግጥም ወደ ተገጠመበት የገጠር ቀዬ ልውሰዳችሁ፡፡ ቦታው ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን 180 ኪ. ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው በቀድሞ አጠራር በሸዋ ክፍለ ሀገር መርሀቤቴ አውራጃ፤ በአሁኑ አጠራር በሰሜን ሸዋ ዞን መርሀቤቴ ወረዳ ታች ቤት አንዷ የቀበሌ ገበሬ ማህበር በሆነችው “ማርያም ሰርቃ”  ነው። በማርም ሰርቃ የመጠጥ ውሀ ቀድቶ ለመመለስ በእግር ጉዞ ከሶስት እስከ አራት ሰዓት ይፈጃል፡፡ ከቦታው ርቀትና ወጣገባነት የሸክም አገልግሎት የሚሰጡት አህዮች ናቸው፡፡ ያውም ወደል አህዮች፡፡  ሴቶች አህዮች የአካባቢውን በረሀነትና ሁለንተናዊ ችግር ተቋቁመው አገልግሎት መስጠት ስለማይችሉ ተፈላጊነታቸው እምብዛም ነው፡፡
በማርያም ሰርቃ ህይወትን ለመጀመር ሲታሰብ ቀድሞ ወደ ህሊናችን ድቅን የሚለው የውሀ ችግርና ለችግሩ መፍትሄ የሚሆነው የወደል አህያ ባለቤት መሆን ብቻ ነው፡፡  አህያ ካለ “ የውላ ውላን” ውሀ መጠጣት ይቻላል፡፡ ከቦታው ርቀትና በረሀነት አንጻር “የውላ ውላ” ውሀ በዛ ቦታ መገኘቱ የተፈጥሮን ድንቅነትና ሚስጢራዊነትን ያሳያል፡፡ በዚህ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሚኖሩ ህዝቦች የሚተዳደሩት በእርሻ ስራና በከብት ርባታ ነው፡፡ ወንዶች የእርሻ ስራን ሲያከናውኑ ሴቶች ደግሞ የቤት ውስጥ  ስራን ያከናውናሉ፡፡ ልጆችን ይንከባከባሉ፡፡ ያሳድጋሉ፡፡
ከላይ እንደነገርኳችሁ፤ የውላ ውላ ውሀ ርቀትና ወጣ ገባነት ታክሎበት ውሀ ለመቅዳት ውላ ውላ የወረደች ሚስት ቶሎ ስለአልተመለሰች እቤት ቁጭ ብሎ የሚጠባበቀው አባወራ በሚወዳት ሚስቱ ትንሽ ሰውኛ ቅናትና ጥርጣሬ ጫር ሲያደርግበት እንዲህ ብሎ ገጠመ፡-
“መጣች ውላ ውላ
መጣች ውላ ውላ
መቸም አይሰፈር
አይለካም ብላ፡፡ “አለ ይባላል፡፡
እናንተ ከተሜዎች፤ ይህን ግጥም ተሳስታችሁ እንዳታቀነቅኑት? የናንተ ዘፈንና ግጥም  ባብዛኛው ስለማታው እንጂ ስለቀን እምብዛም ሲዜም ስላልሰማሁ ነው፡፡ ውሀው በቤታችሁ፣ ሱቁ እደጃችሁ፣ ገበያው  በአቅራቢያችሁ ስለሆነና በጥቅሉ የዘመነ ኑሮ ተቋዳሽ ስለሆናችሁ አይመለከታችሁም።
ይሁንና ማታ  ትዝታችሁና ናፍቆታችሁ የትየለሌ ሳይሆንባችሁ አልቀረም ብዬ አስባለሁ። ዘፈኑ ሁሉ  “ነይልኝ ማታ ማታ….ላግኝሽ ….ማታ …ማታ …… ማታ ……ሲመሽ …ሲጨላልም …..ለብቻዬ….. ተክዤ ….” የሚሉ ዘፈኖች በየቦታው ስለበዙ የቀን ውሎን እንደቆለኛው አባወራ ስላልተጠራጠራችሁ ብጹዓን የሆናችሁ ይመስለኛል፡፡  ከጥርጣሬስ ምን ይገኛል?  ምንስ ትርፍ አለሁ?  ዋናው  ከቁጥር አለመጉደል ነው። እኔ እንደዚህ አወጋኋችሁ የናንተን እይታ አላውቅም፡፡ ብቻ ግጥሙን አጣጥሙት፡፡ ለአንድ ነገር ስም ከማውጣታቸው በፊት የሚያደርጉትን ጥንቃቄና እሳቤ ከውላ ውላ ብዙ ነገር መማር አይቻልም ትላላችሁ? 

Read 2043 times