Sunday, 21 May 2017 00:00

“ካልኩሌተር የጠጣን…”፣ “የአራዶች ቤት አራዶች!...”

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

 በደርግ የመጨረሻዎቹ አመታት...
የደብረ ማርቆስ ወጣት፣ ለአቅመ መዝናናት እስኪደርስና ጎራ እስኪልበት የሚናፍቀው አንድ ቦታ ነበር - “አራዶች ቤት!”...
ስሙን ስትሰማ፣ ሲኒማ ቤት፣ ካፌ፣ ዳንስ ቤት ወይም መሰል የአራዶች መዝናኛ ስፍራ ሊመስልህ ይችላል፡፡ አይደለም!... የእኔ ትውልድ የማርቆስ ወጣት፣ ለእንዲህ ያለ መዝናኛ ስፍራ አልታደለም!... ብቸኛ መዝናኛው ጠላ ቤት ነበር... ይሄም ሆኖ፣ ከጠላም ጠላ፣ ከጠላ ቤትም ጠላ ቤት ያማርጥ ነበር... ከሁሉም የከተማዋ ጠላ ቤቶች፣ የብዙዎች ምርጫ የነበረው ግን፣ “አራዶች ቤት” ነበር...
ወጣቱ አራዶች ቤትን የሚመርጠው፣ የተለየ ጠላ ስለሚያቀርብ አልነበረም፡፡ አራዶች ቤትን ተወዳጅ ያደረገው፣ ከጠላው ይልቅ ቀጂዎቹ እና ሂሳብ አሰላላቸው ነው...
አራዶች ቤት ጎራ ስትል፣ ምን የመሳሰሉ ቆነጃጅት እህትማማቾች በፈገግታ ይቀበሉሃል... ዘመራ ጠላ ይቀዱልሃል!... ማጣጫ ግብጦ ከፈለክም ያቀርቡልሃል!... በቃ ይንከባከቡሃል!...
በስተመጨረሻ...
የጠጣኸውን ጠጥተህ (ለምሳሌ 6 ብርጭቆ ጠላ)፣ ሂሳብህን ከፍለህ ለመውጣት ታስብና ከእህትማማቾቹ አንዷን ትጠራለህ... ቆንጅዬዋ አስተናጋጅ፣ ፈጠን ብላ ወደተቀመጥክበት ትመጣለች... ስትመጣ ግን፣ እንደሌሎቹ የደብረ ማርቆስ ጠላ ሻጮች ባዶ እጇን አይደለም... ካልኩሌተር ይዛ እንጂ!...
ሌሎች ጠላ ሻጮች ቢሆኑ፣ “ስንት ብርጭቆ ነበር የጠጣኸው?...” ብለው ይጠይቁህ ነበር፡፡
የጠጣኸውን ብዛት ስትነግራቸው፣ አንዱን ብርጭቆ ጠላ በአስር ሳንቲም አስልተው፣ ሂሳብክን ደምረው ይነግሩህ ነበር፡፡
አራዶች ቤት ግን፣ ጥያቄና መልስ የለም!...
ቆንጅዬዋ አስተናጋጅ፣ ከፊትህ ትቆምና፣ ካልኩሌተሯን ጠቅ ጠቅ ጠቅ ታደርጋለች፡፡
“አንድ ብር ከአርባ ሳንቲም!...” ብላ ሂሳብህን ትነግርሃለች፡፡
ይሄኔ ትጠራጠራለህ - የጠጣኸው ስድስት ብርጭቆ ጠላ ብቻ እንደሆነ ታውቃለሃ!...
ሌላ ቤት ቢሆን ኖሮ፣ አስራ አራት ብርጭቆ ጠላ አልጠጣሁም ብለህ፣ ሂሳቡን እንድታስተካክል ልትነግራት ትችል ይሆናል፡፡ ያለኸው ግን እዚህ ነው... አራዶች ቤት!... አራዶች ቤት ደግሞ፣ መከራከር የለም!... አራዶች ቤት ገብተህ ከተከራከርክ፣ አራዳ አይደለህም ማለት ነው!... አራዳ አለመሆንህን አምነህ፣ ተታልያለሁ በሚል ቁጭት፣ ግግም ብለህ “አስተካክይ፣ ተሳስተሻል!...” እያልክ ከተከራከርክ ግን...
“ካልኩሌተር ይሳሳታል!?...” ስትል በጥያቄ ታፋጥጥሃለች - አስተናጋጇ፡፡
ይሄኔ... የአስተናጋጇን ጥያቄ የሰሙ፣ ከጎንህ ቁጭ ብለው የሚጠጡ “ኦሪጅናል አራዶች” ጣልቃ ይገቡና እማኝነታቸውን ይሰጣሉ...
“ኧረ በፍጹም!...” በማለት፡፡
ምርጫ የለህም!... የማይሳሳተው የአራዶች ቤት ካልኩሌተር የጣለብህን ቁርጥ ግብር ከፍለህ፣ ሹልክ ብለህ ትወጣለህ!...
“ልክ እንደ ባቄላ አይን የለውም አተር
አራዶች ገብቼ ጠጣሁ ካልኩሌተር” እያልክ እያንጎራጎርክ!...
.የማርቆስ ልጅ ሆነህ፣ ጠላ ካልጠጣህ...
ያኔ በኛ ጊዜ... የማርቆስ ልጅ ሆነህ... ጠላ ላለመጠጣት በቂ ምክንያት የለህም!...
መጠጥ ጥሩ አይደለም ብለህ ማሰብህ፣ እድሜዬ ለመጠጥ አልደረሰም ብለህ መታቀብህ፣ ለጤናህ መጠንቀቅህ፣ ስካር መልካም ነገር አይደለም ብለህ ማመንህ፣ ጠላ አለመውደድህ ወዘተ... ጠላ ላለመጠጣትህ ምክንያት መሆን አይችሉም!...
የማርቆስ ልጅ ሆነህ፣ “ጠላ አልጠጣም” ስትል ከተሰማህ፣ በሁለት ነገሮች ትጠረጠራለህ...
አንድ - በትምህርት ጎበዝ እንድትሆን የሚያደርግ፣ አብሾ የሚባል መድሃኒት ወስደሃል! (አብሾ የወሰደ ሰው፣ ጠላ ከጠጣ ወፈፍ ያደርገዋል ተብሎ ይታመን ነበር)
ሁለት - ጴንጤ ሆነሃል!...
ልጅ ሆኜ...
እንድ ዕለት፣ ጠላ ግዛ ተብዬ ወደ እማ አበቡ ቤት ተላክሁኝ... ማንቆርቆሪያውን ለእማ አበቡ ሰጥቼ፣ ጠላውን እስኪቀዱልኝ፣ ከበሩ አጠገብ ቆሜ እጠብቃለሁ... እማ አበቡ ግን፣ አንድ ብርጭቆ አንስተው ጠላ ቀዱልኝና “እንዳይደቃህ ቅመስ...” ብለው ሰጡኝ...
አልጠጣም አልኩ፡፡
ይሄኔ... ጠላ ቤቱ ውስጥ ተሰባስበው ከሚጠጡት ጎረምሶች አንዱ ጣልቃ ገባና አፈጠጠብኝ...
“ምን ወግቶህ ነው እማትጠጣ!?... አብሾ ወስደህ ነው አይደል!?...” አለኝ ኮስተር ብሎ፡፡
“ኧረ እማየል!...” አልኩ ፈራ ተባ እያልኩ፡፡
ለእሱ እና ለብዙሃኑ የከተማዋ ነዋሪ... ጠላ አልጠጣም የሚል ማርቆሴ፣ አብሾ ካልወሰደ፣ ጴንጤ ሆኗል ማለት ነው!...
.ደብረ ማርቆስ ከስነ-ጽሁፍ ባልተናነሰ በስፋት የምትታወቅበት እሴት ነበር - ጠላ!...
እግር ጥሎህ ወደ ከተማዋ ጎራ አልክ እንበል...
ደብረ ማርቆስን ዞር ዞር እያልክ ስትጎበኝ፣ ከተማዋ በርካታ የጥበብ ሰዎችን ማፍራቷ ትዝ ይልሃል...
እነ ሃዲስ አለማየሁ፣ ጌትነት እንየው፣ በእውቀቱ ስዩም፣ እንግዳ ዘር ነጋ፣ ሙሉቀን መለሰ... እና ሌሎች ብዙዎች በበቀሉባት የጥበብ ምድር ላይ ዞር ዞር ስትል ቆይተህ፣ አንዱን የከተማዋ ነዋሪ ትጠራዋለህ...
“የእነ ጌትነት እንየው ሰፈር የት አካባቢ ነው?...” ብለህ ትጠይቀዋለህ፡፡
እሱ ሲመልስልህ... እንዲህ ብሎ ነው...
“እዚያ ማዶ የእማ ዳሳሽ የጠላ ምልክት ይታይህ የለ?... እሱን አልፈህ ወደ ቀኝ ስትታጠፍ፣ አምራቾችን ታገኘዋለህ...” ብሎ ሲልህ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ የብሎኬት አምራቾች ያለህ እንዳይመስልህ፡፡
አምራቾች የማርቆስ የጠላ ኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነ ታዋቂ ሰፈር ነው፡፡ እዚህ ሰፈር ውስጥ፣ ግራና ቀኙን በመደዳ የተሰለፉ ከ30 በላይ ጠላ ቤቶችን ታገኛለህ፡፡
“አምራቾችን እንዳለፍክ፣ ሽቅብ ትወጣና የእማ አበቡን ቤት በግራህ ትተህ፣ ቁልቁል ስትሄድ በመደዳ የተተከሉ ስድስት የጠላ ምልክቶችን ታገኛለህ... ትንሽ ወረድ እንዳልክ የተሰጣ ጌሾ አታጣም... ከእሱ ጀርባ ነው የእነ ጌትነት ሰፈር!...”
.ጠላ 20 ሳንቲም ገባ!...
የሆነ ጊዜ ላይ... የደብረ ማርቆስ ጠላ፣ በሁለት ተከፈለ፡፡ “ባለ አስር” እና “ባለ ሃያ”!... ባለ አስሩ ቀጠን ያለ ሲሆን፣ ባለ ሃያው ወፈር ያለ ነው፡፡
የከተማዋ ጠላ ጠማቂዎች፣ የ10 ሳንቲም ጭማሪ በማድረግ የአንድ ብርጭቆ ጠላን ዋጋ 20 ሳንቲም ማስገባታቸው፣ ለኔ ቢጤ ጠላ ሊገዙ የሚላኩ ብላቴናዎች ትልቅ የማጭበርበር ዕድልን ፈጠረ...
“እንዴት?...” ማለት ጥሩ!...
ለምሳሌ...
እናቴ አምስት ብርጭቆ ባለ ሃያ ጠላ ግዛ ብላ፣ አንድ ብር እና ማንቀርቆሪያ ሰጥታ፣ ወደ እማ ቀኔ ቤት ትልከኛለች...
እማ ቀኔ ቤት ስደርስ...
“ባለስንቱን ላርግልህ?...” ብለው ይጠይቁኛል፡፡
“ሶስት ብርጭቆ ባለ ሃያ እና ሁለት ብርጭቆ ባለ አስር!...” እላለሁ እኔ፡፡
እንዳልኳቸው ይቀዱልኛል፡፡
አንድ ብሩን ስሰጣቸው፣ ሃያ ሳንቲም ይመልሱልኛል፡፡
ቤት ደርሼ...
ማንቆርቆሪያውን ለእናቴ አቀብዬ ወደ ጓዳ እገባለሁ...
“ዛሬስ የእማ ቀኔ ጠላም አይመስል!... አቅጥነውታል!...” ሲል እሰማዋለሁ አባቴ፣ የተቀዳለትን ጠላ እየቀመሰ...

Read 1571 times