Sunday, 21 May 2017 00:00

“ጥበብ በአደባባይ” ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ሳምንታት ይከናወናል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   የከተማዋ ነዋሪዎች በየአደባባዩ ጥበባቸውን ይገልጻሉ

       በጎተ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ለቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት የሚከናወነውና ሁሉንም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያሳትፈው “ጥበብ በአደባባይ” የተሰኘ ልዩ የኪነ-ጥበባት ዝግጅት ስድስት ኪሎ በሚገኘው ድባብ መናፈሻ ትናንት የተመረቀ ሲሆን፣ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት ይቆያል፡፡
በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዟዟረ በሚካሄደው “ጥበብ በአደባባይ”፤ ህጻናትና አረጋውያንን ጨምሮ ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪና አርቲስቶች በመዲናዋ ጎዳናዎች ላይ በሚከፈቱ ልዩ ልዩ ባህላዊ ሱቆች ውስጥ በሚከናወኑ የፊልም ፣ ፎቶ ግራፍ ፣ ስዕል ፣ ሙዚቃ ፣ ስነ - ጽሁፍ ፣ አርኪቴክቸር (ስነ ህንጻ) እና ሌሎችም የኪነጥበብ ዘርፎች ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ስሜትና ተሰጥዖዋቸውን የሚገልጹበት ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ተነግሯል።
የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶቹ በመርካቶ፣ መገናኛ፣ መስቀል አደባባይ፣ ጀሞ፣ ቦሌ ድልድይ፣ አራት ኪሎ፣ ካራቆሬ፣ ብሄራዊ፣ ቦሌ መድሃኒያለም፣ ሜክሲኮና ባልደራስ ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች በሚገኙና በታዋቂው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ዲዛይን በተደረጉ አስር የ“ጥበብ በአደባባይ” ልዩ ባህላዊ ሱቆች ውስጥ እንደሚከናወኑም የፕሮጀክቱ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ አቶ በሃይሉ ሽፈራው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ኪነ-ጥበብን ወደ አደባባይ በማውጣት የከተማዋ ነዋሪ የዕለት ከዕለት ኑሮ አካል የማድረግ ዓላማ ያነገበውን ይህንን ፕሮጀክት ያዘጋጀውና እ.ኤ.አ በ1962 የተቋቋመው የአዲስ አበባው ጎቴ ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያና በጀርመን እንዲሁም በሌሎች የአውሮፓ አገራት መካከል የባህል ልውውጥን ለማሳደግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

Read 1455 times