Saturday, 20 May 2017 12:53

ኢትዮ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኤግዚቢሽን ሊካሄድ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ከሰባት ዓመት በፊት በ2002 ዓ.ም በ15 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ኢትዮ ሃይላንድ ማራቶን ኤቨንትስ ኦርጋናይዝ ኩባንያ ከነሐሴ 12-14 ቀን 2009 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ የትራንስፖርትና ሎጂስትክስ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ አስታወቀ፡፡
አዘጋጆቹ ባለፈው ሳምንት በካሌብ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ትራንስፖርት ያለ ሎጂስቲክ (የጭነት ዕቃ) የተሟላ አገልግሎት እንደማይሰጥ ሁሉ፣ ሎጂስቲክም ያለ ትራንስፖርት ብቻውን መቆም አይቻልም፤ ሁለቱ የተጣመሩና የተጎዳኙ ናቸው ብለዋል፡፡ ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁበት ዓላማ፣ ዘርፉ በሀገር ልማት ያበረከተውን አስተዋጽኦና መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጫወቱትን ሚና ለማሳየት፤ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የተሰማሩ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት ልምዶቻቸውንና ስኬቶቻቸውን የሚለወዋወጡበት መድረክ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ ውስጥ ያሉ አካላት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ሰፊ የገበያ ዕድል ለመፍጠርና በኤግዚቢሽኑ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ያሉት መልካም ጎኖች ተፈትሸው ጥናታዊ ጽሑፍ የሚቀርብበትን ወርክሾፕ ለማዘጋጀት ነው ብለዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑ የአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፌር በሚል ስያሜ በየዓመቱ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰው ጠቀሜታውንም ሲገልጹ፣ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ ለማሳደግ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል፣ በዘርፉ ያሉ ተዋናይና ባለድርሻ አካላት ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋወቁበታል፣ ተዋናዮቹ፣ በጋራ ችግሮቻቸው ላይ ተቀራርበው በመነጋገር የመፍትሄ ሀሳቦችን ያፈልቁበታል በማለት አስረድተዋል፡፡
በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ የትራንስፖርት ሚ/ር፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች፣ የሕዝብና የዕቃ ማጓጓዣ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ የባህር፣ የአየር፣ የየብስ፣ የባቡር፣ የወደብ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ዕቃ አስተላላፊዎች፣ ዕቃ የማሸግና ለጉዞ የማመቻቸት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫ አምራቾች፣ አስመጪና ላኪዎች፣ ጋራዦች፣ የንግድ ወኪሎች፣ የነዳጅ ኩባንያዎች፣ ባንኮችና ኢንሹራንሶች፣ ጎሚስታዎች፣… እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡

Read 1448 times