Sunday, 21 May 2017 00:00

አዲስ ዓለም አቀፍ ካተሪንግ ‹‹የ2016 የአፍሪካ ምርጥ ምግብ አዘጋጅ›› በመባል ተሸለመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ታዋቂው የኳታር አየር መንገድ ካተሪንግ አገልግሎት፤ አዲስ ዓለም አቀፍ ካተሪንግ (የምግብና የመጠጥ ዝግጅት) ‹‹የ2016 ምርጥ የአፍሪካ ምግብ አዘጋጅ›› በሚል ለሁለተኛ ጊዜ ሸለመ፡፡ ከአሁን ቀደምም በ2014 በተመሳሳይ መሸለሙ አይዘነጋም፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል የሆነው አዲስ ዓለም አቀፍ ካቴሪንግ፣ ለኢትዮጵያና ለሌሎች አገሮች አየር መንገዶች፣ ለዓለም አቀፍ ጉባዔዎችና በአዲስ አበባ አካባቢ ለሚደረጉ ትላልቅ ዝግጅቶች ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ምግብ ለማቅረብ በ1998 የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡
በመላው ዓለም ከ150 በሚበልጡ መዳረሻዎች የሚበረው ባለ 5 ኮከቡ የኳታር አየር መንገድ፣ በሚበርባቸው አገሮች 105 የምግብና መጠጥ አዘጋጆች (ካተርስ) ሲኖሩት በአፍሪካ ወደ 24 መዳረሻዎች  ይበራል፡፡ የተሳፋሪዎችን አስተያየት፣ ወቅታዊ (ኦን ታይም) አቅርቦት፣ የተሳፋሪዎች ግብረ-ምላሽና ከምግብና ከደህንነት ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮችን የመዘኑ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ ከምግብ አዘጋጆች ናሙና እንደሚወስዱ፣ መሳሪያዎች እንደሚመረምሩ፣ ግንኙነት እንደሚታይ፣ የአለቃ ሪፖርትና የአዘጋጃጀት ቅልጥፍና እንደሚታይ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዓለም አቀፍ ካተሪንግ ከኳታር አየር መንገድ በተጨማሪ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለሚጠቀሙ ሌሎች ደንበኞች ለምሳሌ ለጂቢቲ፣ ለግብፅ፣ ለኢምሬትና ለኬንያ አየር መንገዶች አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቀሰው መግለጫው፤ ለቪአይፒ፣ ለኪራይና በግል ለሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች፡- እንደ አቢሲኒያ ፍላይት ሰርቪስና እንደ ትራንስ ኔሽን ላሉ ትናንሽ በረራዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡  በተጨማሪም፣ አዲስ ዓለም አቀፍ ካተሪንግ፣ ለጀርመን ኤምባሲ ት/ቤት፣ ለዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ ት/ቤት፣ ለየን ኻርት አካዳሚና ለሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ት/ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ ኤምባሲዎች፣ ባንኮችና ለግል ዝግጅቶች አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡

Read 1603 times