Sunday, 21 May 2017 00:00

ጊፍት ሪል ኢስቴት በሲኤምሲ አካባቢ የገነባቸውን የመንደር ሁለት ቤቶች ለነዋሪዎች አስረከበ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ጊፍት ሪል ኢስቴት በሲኤምሲ አካባቢ ከሚሰራቸው የመኖሪያ መንደሮች አንዱ የሆነውንና ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን የመንደር ሁለት ቤቶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ የዛሬ ሳምንት ለነዋሪዎች አስረከበ፡፡
ባለፈው ሳምንት ግንቦት 5 ቀን 2009 መሪ ሎቄ አካባቢ በሚገኘው የመንደር ሁለት ግቢ ውስጥ በተከናወነው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተለያየ ዲዛይን የተሰሩ 350 ቪላዎች፣ ሮው ሃውስ፣ ታውን ሃውስና አፓርትመንቶች ለነዋሪዎች የተላለፉ ሲሆን በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው ታዋቂ ሰዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡
የመንደር አንድ ግንባታን ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ባለፈው ዓመት ለነዋሪዎች ያስተላለፈው ጊፍት ሪል ኢስቴት፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ግንባር ቀደም ተቋማት አንዱ ሲሆን በሊዝ በተረከበው 16.3 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነቡ 1500 ቪላ፣ ታውን ሃውስ፣ ሮው ሃውስና አፓርትመንት ቤቶች ግንባታ ጠቅላላ ኢንቨስትመንት 2 ቢሊዮን ብር እንደሚጠጋ የሪል ኢስቴቱ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የሦስት መንደር ልማት ፕሮጀክቶች ከ1500 በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ታውን ሃውስ፣ ሮሃ ሃውስና ቪላ ቤቶች፣ 44 ብሎክ አፓርትመንቶች፣ 12ና ከዚያም በላይ ፎቅ ያላቸው የንግድ ሕንፃዎችን የሚያካትቱ እንደሆኑ፣ ከ1,500 ለሚበልጡ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በሚገነባቸው ቤቶች ጥራት በደንበኞች ዘንድ ምስጉን የሆነው ጊፍት ሪል ኢስቴት፤ በገባው ቃል ባለማስረከብ ይወቀሳል፡፡ የዚህንም ችግር አቶ ገብረየሱስ ሲናገሩ፤ ‹‹የመኖሪያ መንደሮች ግንባታ አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ እጅግ ፈታኝና የድርጅቱን ሕልውና አደጋ ላይ የጣሉ፣ ደንበኞችንም ለስጋት የዳረጉ ክስተቶች አስተናግደናል። በተዋረድ በሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በፈጠሩት ውስብስብ ችግሮች ድርጅቱ ለዓመታት አስተዳደራዊ አገልግሎት እንዳያገኝ ተከልክሎ ቆይቷል፡፡ ይህ እርምጃ በብዙ መልኩ ድርጅቱን ቢጎዳውም፣ ከደንበኞች ጋር የገባነውን ቃል ለማክበር ጥረት ስናደርግ ቆይተናል›› ብለዋል፡፡
ደንበኞች እስካሁን ለጠበቁት ጊዜ በቂ ማካካሽ ባይሆንም ድርጅቱ እንደ ምስጋና መግለጫ ይሆነው ዘንድ 14 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በውል ላይ ከሰፈረው ውጪ በLTZ መሠራት የነበረባቸውን ታውን ሃውስና አፓርትመንት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በአሉሚኒየም መቀየሩን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ሙሉ በሙሉ በአስፋልት መቀየሩን፣ ለነዋሪዎች ምቾትና ለግቢው ውበት ባለፏፏቴና በአረንጓዴ ዕፅዋት ያማረ መናፈሻ ማዘጋጀታቸውን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ጊፍት ሪል ኢስቴት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመውጣት አኳያ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል መኖሪያ ቤት በመስጠት፣ ለቀይ መስቀል ማኅበርም በተመሳሳይ መኖሪያ ቤት በመስጠትና በማንኛውም ሀገራዊ የልማት ተግባር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ ተናግረዋል፡፡
ጊፍት ሪል ኢስቴት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ “እናስረክባለን” ባሉት ጊዜ ኃላፊነታቸውን ያለመወጣት ችግር አለባቸው፡፡ ሁለትና ሦስት ዓመት የመቆየት ችግር የተለመደ ነው፡፡ ፍ/ቤት ደጃፍም የረገጡም አሉ፡፡
ጊፍት ሪል ኢስቴት፣ “አስረክባለሁ” ባለው ጊዜ ባለማስረከብ፣ “ዘግይቷል” የሚለው ቃል አይገልጸውም። ምክንያቱም ሰባትና ዘጠኝ ዓመት የጠበቁ ደንበኞች ስላሉ ነው፡፡ ከሁለተኛው መንደር ቤት የተረከቡ ሰዎች ምን ይላሉ?
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፡- የነዋሪዎች ኮሚቴ ሊቀመንበር ነው፡፡ የቤት ርክክቡ በጣም ዘግይቷል። በመኻል  የቤት ባለቤቶች ኮሚቴ ተቋቁሞ ከድርጅቱ ጋር ብዙ ክርክሮች ተደርገዋል፡፡ በመጨረሻ የጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ መስተዳደር ጽ/ቤትና የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ተጨምሮበት በተሰጠው አመራር፣ የቤቱን ግንባታ በትብብር በመሥራት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲያልቅ ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ ይኸው እንግዲህ ባለፈው አንድ ዓመት በተደረገው ርብርብ የቤቱ ግንባታ አልቆ ልንረካከብ ችለናል፡፡
ችግሩ ምንድን ነው? የተባለ እንደሆነ፣ እኛ ቤት ለመረከብ ውል የገባነው በ18 ወር ነው፡፡ የፈጀው ግን 7 ዓመት ነው፡፡ ይታይህ፣ ይህንን መዘግየት አይገልጸውም። ያ አይደለም የሰዎቹ ጥያቄ፡፡ እሺ ዘገየ፤ መቼ ነው የሚያልቀው? የሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ የለውም። ከ20 ዓመት በላይ ነው በሉንና ቁርጣችንን አውቀን ሌላ አማራጭ እንፈልግ። ወይም ከ20 ቀን በኋላ በሉንና ደስ ይበለን እያለ ነበር ሲወተውት የነበረው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ማለቅ አለበት ተብሎ እኛም ችግሮችን አብረን ሆንን እየፈታን ለመረከብ በቃን፡፡
የእኔ ቤት ታውን ሃውስ የሚባለው ስለሆነ ብዙም ችግር አልነበረውም፡፡ ነገር ግን የሌሎች ካላለቀ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ናይጄሪያውያን የሚሉት አንድ አባባል አለ፡- “ልጅን ለማሳደግ መንደር ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡ የመንደሩ ቤቶች ካላለቁ የእኔ ቤት ብቻ ቢያልቅ ዋጋ ያለውም፡፡ ስለዚህ የእኛ ክርክር ሁሉም ቤቶች ይለቁ የሚል ነበር፡፡ ይኸው ዛሬ ሁሉም ቤቶች አልቀው ለመረከብ በቃን፡፡ ጥቂት ነገሮች ቢቀሩም ወደ መኖሪያነት ተቀይሯል፡፡ ውሃና መብራት ገብቶልናል፤ ዘጠና ከመቶ ተጠናቋል፡፡
ትልቁ ችግር የነበረው ዋጋው ነው፡፡ መጀመሪያው ከ7 ዓመት በፊት የነበረው ዋጋ፣ የእኛ ቤቶች ከ800 እስከ 1.2 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በ1997 የዛሬ 12 ዓመት ማለት ነው፡፡ ያኔ የቀን ሠራተኛ ዋጋ 30 ብር ነበር፡፡ ዛሬ 140 ብር ሆኗል፡፡ ሌላ ሌላውም እንደዚሁ ጨምሯል፡፡ በተለይ ችግር የተፈጠረው ‹‹በየትኛው ዋጋ ነው የምንከፍለው?›› የሚል ነው። በተለይ ከፍለው የጨረሱት፡፡ ‹‹በዛሬ ዋጋ ክፈሉ›› ሲባሉ ‹‹እናንተ ባዘገያችሁት ለምንድነው በዛሬ ዋጋ የምንከፍለው?›› ይሉ ነበር፡፡ ችግሮች በሽምግልና በድርድር እየተፈቱ ዛሬ ጥሩ ቀን ላይ ደርሰናል፤ በማለት ገልዷል፡፡ አቶ አዲስ ሚካኤል፤ ‹‹ብዙ ሪል ኢስቴቶች ላይ ያሉ ችግሮች ጊፍት ሪል እስቴትም ላይ ይታያሉ። ዋናው ነገር በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፎ እዚህ መድረሱ በጣም ደስ ይላል፡፡ እኔ ከዛሬ 8 ዓመት በፊት በ1.7 ሚሊየን ብር የገዛሁት ቤት ተጎራባች ወይም ታወን ሃውስ  የሚባለውን ነው፡፡ የጊፍት ሪል እስቴት ትልቁ ቁምነገሩ ቤቶችን በጥራት መሥራቱ ነው፡፡ እናም ከሌሎቹ ሪል ኢስቴቶች ጊፍትን መርጠን ቤት እንድንገዛ ያደረገን የጥራቱ አሠራር ነው፡፡
አሁን ሁሉም ነገር በሰላም አልቆ፣ ውሃና መብራት ገብቶላቸው ተረክበን እየኖርንበት ነው፡፡ የቤቶቹ ግንባታ የዘገየበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የቦታ ማለትም የወሰን ማስከበር፤ የባለሙያ፣… ችግር ነበረበት፡፡ ገዥዎችም ላይ በወቅቱ ያለመክፈል ችግር ይኖራል፡፡ በመጨረሻ ሁሉ ችግር አልፎ እዚህ መድረሱ በጣም ደስ ይላል፡፡›› ብለዋል።
ወ/ሮ ስርጉት ተክሉ፣ የሦስት ልጆች እናት ናቸው፤ ‹‹የተመዘገብኩት ከ7 ዓመት በፊት ሲሆን ቤቱን የተረከብኩት ደግሞ ካቻምና በ2007  ዓ.ም ነው፡፡ በፊት በመዘግየቱ ተከፍተን ነበር፡፡
አሁን ግን ቤቱን ተረክበን ገብተንበት ስናየው ቤቱን ሰርቶ (አቁሞ) እንዲያስረክበንና የውስጥ ዲዛይን እኛ በፈለግነው መንገድ እንድንጨርሰው ነበር፡፡
በውላችን መሠረት ቤቱን አስረከበን፤ እኛም በፈለግነው መሰረት የውስጥ ዲዛይኑን ጨርሰን ገባንበት። ምንም ቅር አላለንም፤ በዚህና በቤቱ ጥራት በጣም ደስተኞች ነን፡፡
የእኔ ቤት 370 ካሬ ላይ ያረፈ ቪላ ነው፡፡ 7 መኝታ ክፍሎችና፣ 2 ሳሎንና 2 ወጥ ቤት አለው፡፡ ውስጥ ዲዛይኑና ፊኒሽንጉ በራሴ በመሆኑ ሙሉውን አልከፈልኩም፡፡
ሁለት ሚሊዮን ብር ያህል ከፍያለሁ፡፡ በፊት ግንባታው በመዘግየቱ የተነሳ ብከፋም፤ አሁን ከገባሁበት በኋላ ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ አየሩንም፣ ጎረቤቶቼንም፣ ጊፍትንም ወድጃቸዋለሁ። በጣም በደስታ ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር እየኖርኩ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

Read 1863 times