Monday, 22 May 2017 00:00

በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዳዲስ ምዕራፎች ተከፍተዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከግንቦት 8 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድዬም ሲካሄድ ነበር፡፡ ሻምፒዮናውን በቂ ተመልካች በአዲስ አበባ ስታድዬም ተገኝቶ እየተከታተለው አልነበረም፡፡ በተለይ ዋናዎቹ ታዳሚዎቹ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ የክለብና የክልል ክለቦች ተለያዩ ስፖርት ኃላፊዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው አዳዲስ ምእራፎች መክፈቱን በተለያዩ ሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የሻምፒዮናው  ዓላማ “በክልሎች፣ በከተማ አስተዳድሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል መፍጠር፤ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት፣ ለአህጉርና አለም አቀፋዊ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አገራችንን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን መምረጥ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በተለይ ከ4 ወራት በኋላ የእንግሊዟ ከተማ ለንደን ለምታስተናግደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ውጤታማ አትሌቶች በእጩነት የሚያዙበትም እንደሆነ ጠቁሟል። በብሄራዊ ሻምፒዮናው ላይ ውጤታማ የሚሆኑ ሻምፒዮን አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮን ለመሳተፍ እጩ ሆነው የሚቀርቡበት ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር  የተቀመጠውን ሚኒማ ለማሟላት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በተሰጠው የውድድር መድረክ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚመዘገብ ሚኒማ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽ ማህበር እውቅና የማያገኝ በመሆኑ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በሚቀጥሉት ዓመታት የባህር ዳር፣ የሐዋሳና የወልዲያ ስታድዬሞችን በአዲ.ኤ.ኤ.ኤፍ እውቅና እንዲያገኙ አበረታች ጥረቶች አሉ፡፡ የሚሳኩ ከሆነ ለዓለም ሻምፒዮና እና ለኦሎምፒክ ሚኒማ ማሟያ የሚሆኑ ውድድሮች በኢትዮጵያ ሊዘጋጁ ይችላሉ፡፡
የማልታ ሶፊ ስፖንሰርሺፕ እና
የአትሌቲክስ ልማት
በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ10 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ አብይ ስፖንሰር አግኝቷል፡፡ በሻምፒዮናው ዋዜማ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሄኒከን ኩባንያ ጋር በማልታ ሶፊ ምርቱ ልዩ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በመፈፀሙ ነው፡፡ የስፖንሰርሺፕ ስምምነቱ  ለሚቀጥሉት 5 አመት ይቆያል፡፡ ሄንከን ኩባንያ ከፌደሬሽኑ ጋር በአትሌቲክስ ልማት ላይ አተኩሮ በመስራት እስከ 30ሚሊዮን ብር ይከፍልበታል፡፡ የአትሌቲክስ ልማቱ በትጥቅ፤ በስልጠና፤ በውድድሮች ስፖንሰርሺፕ፤ እና በሙያዊ ድጋፎች ያተኩራል፡፡ የማልታ ሶፊ ስፖንሰርሺፕ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ከፍተኛው ገቢ የተገኘበት የውል ስምምነት ነው፡፡ ከማልታ ሶፊ በፊት የአትሌቲክስ ሻምፐዮናውን ላለፉት 10 ዓመታት ስፖንሰር አድርጎ የቆየው በኢትዮጵያ የሳምንሰንግ ምርቶች ዋና አከፋፋይ የሆነው ጋራድ ኩባንያ ነበር፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በስፖንሰርሺፕ የሚያገኘውን የገቢ መጠን እያሳደገ መቀጠል ይፈልጋል፡፡ በስሩ የሚንቀሳቀሱ ክልሎችና ክለቦችም በተመሳሳይ አቅጣጫ እንዲሰሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮናው ከሚካፈሉት መካከል የደቡብ ክልልለ በዚህ ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። የደቡብ ክልል በሻምፒዮና ላይ ሲካፈል ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ በስፖንሰር ሺፕ በማግኘት ነው፡፡ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ የአትሌቶች ትጥቅና የስፖርት ቁሳቁሶች በማሟላት እንዲሰራ አግዞታል፡፡ ሌሎቹ ክልሎች እና ክለቦችም ከፌዴሬሽኑ በጀት ከመጠበቅ ይልቅ የደቡብ ክልልን ተመክሮ በመቅሰም ገቢያቸውን የሚያጠናክሩበት መንገድ መቀየስ አለባቸው፡፡
የሜዳ ላይ ስፖርቶች መጠናከር፤ የኃይሌ ተስፋ እና ክትትል
ባለፈው ሐሙስ በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው 3ኛ ቀን መርሃ ግብር ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ተገኝተን የታዘብነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከሩጫው ባሻገር ከሜዳ ላይ ስፖርቶች ትኩረት መስጠቱን ነው። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረስላሴ በተለይ ለሜዳ ላይ ስፖርቶች በቂ ትኩረት በመስጠትና ተስፋ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለስፖርት አድማስ ገልጿል። በሻምፒዮናው ላይ በሱሉስ ዝላይ በሁለቱም ፆታዎች አዳዲስ የኢትዮጵያ ክብረወሰኖች መመዝገባቸው ፌደሬሽኑን አበረታቶታል፡፡
በእለቱ ይካሄዱ ከነበሩ የሜዳ ላይ ስፖርቶች አትሌት ኃይሌ በቅርበት ሲከታተል የተመለከትነው በአግድመት ዝላይ የሴቶች ውድድር ነበር፡፡ ኃይሌ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በስፖርት አይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አቅም ሻምፒዮናው እንደሚያሳይ አምነውበታል። ስፖርተኞች በግል ጥረታቸው ያሉበት ደረጃ ያስደንቃል የሚለው ሻለቃ ኃይሌ በመደበኛ የስልጠና መርሃ ግብሮች እና በብቁ ባለሙያዎች የምንደግፋቸው ከሆነ ከሩጫ ስፖርቶች ባሻገር ለአፍሪካ እና ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ብሎም ለኦሎምፒክ ብቁ የሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት አይቸግረንም ሲል ተናግሯል፡፡
በአግድመት ዝላይ የኢትዮጵያን ሪከርድ በ5.84 ሜትር የያዘችው የንግድ ባንኳ አትሌት አሪያት ሲቦ ፌዴሬሽኑ ትኩረት መስጠቱ፣ የእነ ኃይሌ የቅርብ ክትትል እንዳስደሰታት ለስፖርት አድማስ ተናግራለች፡፡ አሪያት ዲቦ በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሶስተኛ ጊዜ በውድድር አይነቱ የወርቅ ሜዳልያ በመጎናፀፍ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ለመሆን በቅታለች፡፡ በየስፖርቱ በስልጠና፣ በትጥቅ እና ሌሎች ድጋፎች ተጠናክረን የምንሰራ ከሆነ ለትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የማንበቃበት ምክንያት የለም ስትልም ትናገራለች፡፡ በንግድ ባንክ ክለብ ስተሰራ ሁለት ዓመት የሆናት አሪያት ዘንድሮ የሻምፒዮናን የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፈችው 5.81 ሜትር በመዝለል ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ ደረጃ በናይጄርያ፤ በሞሮኮ እና በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያን በመወከል በስፖርት አይነቱ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች በአግድመት ዝላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ሚኒማው 6 ሜትር ነው፡፡ “ይህን በልምምድ ሜዳ የምናሳካው ነበር፡፡ ትኩረት ተሰጥቶን፤ ስልጠናው ተሻሽሎ ከሰራን ወደፊትም ሚኒማ ለሟሟላት አንቸገርም” ብላለች፡፡
46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በነገው ዕለት ፍጻሜውን ያገኛል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 1.6 ሚሊዮን ብር በጀት በመያዝ ያዘጋጀው ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች ከ1000 በላይ ስፖርተኞችን የሚያሳትፍ፣ ከ150 በቢሮ ልዩ ልዩ ባለሙያዎችና 80 ዳኞች የተመደቡበት ነው፡፡ በሻምፒዮናው በየደረጃው ለሚያሸንፉት የቀረቡትን የገንዘብ ሽልማቶች 100 ፐርሰንት በማሳደግ 480 ሺ ብር ይበረከታል፡፡ 11 ክፍሎችና የከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከ30 በላይ ክለቦች ተሳታፊ በሆኑበት 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም ፆታዎች 42 የውድድር አይነቶች ይካሄዳሉ፡፡

Read 2069 times