Saturday, 27 May 2017 13:05

የቅድስት አርሴማን ቤተ ክርስቲያን ያፈረሱ የወረዳ ሓላፊዎች በእስራት ተቀጡ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የፍርድ ቤት የእግድ ትእዛዝ በመጣስ፣ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ስሙ የካ አባዶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የምትገኘውን የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ያፈረሱ፣ የወረዳ 12 አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሓላፊ፣ በ15 ቀን ቀላል እስራት እንዲቀጡ የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ወሰነ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትፈርስ የሥር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ግን፣ “ይግባኝ አያስቀርብም” ብሏል፡፡
በይግባኝ ባይ፥ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና በመልስ ሰጪ፥ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽ/ቤት መካከል ያለውን የይግባኝ ቅሬታ ሲመረምር መቆየቱን ከትላንት በስቲያው ውሳኔው ያስታወቀው ፍ/ቤቱ፤ መልስ ሰጪዎቹ፥ የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመላሽ ጎሳ እና የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ሓላፊ አቶ ዳዊት ሙሉጌታ፤ የፍ/ቤትን የእግድ ትእዛዝ እያዩ፣ ክርክር የቀረበባትን ቤተ ክርስቲያን ማፍረሳቸው፣ የፍርድ ቤትን ሥራ ማወክ በመኾኑ ጥፋተኛ ኾነው እንደተገኙ ገልጿል፡፡
በይግባኝ ባይ በኩል የቀረቡ አራት ምስክሮች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት በየነ አሰፋ፥ “የፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ አለ፤ በሕግ አምላክ አታፍርሱ” እያሉ ለተጠቀሱት ሁለት ሓላፊዎች እንዳሳዩዋቸው፤ እነርሱ ግን ለማቆም ፈቃደኛ እንዳልነበሩና በግብረ ኃይል ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዳስፈረሱ፣ በበቂ ሁኔታ ማስረዳታቸውን ፍ/ቤቱ በውሳኔው ጠቅሷል፡፡ በመልስ ሰጪዎች የቀረቡ ሁለት ምስክሮች፣ አፍራሽ ግብረ ኃይል ሆነው የማፍረስ ተግባር ያከናወኑና ምስክርነታቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ ሆኖ በመገኘቱ፣ “ገለልተኛና ተኣማኒነት ያለው ኾኖ አላገኘነውም፤” ብሏል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ “የጣስነው ሕግ የለም፤ የወሰድነው ርምጃም ተቋሙን ወክለን ነው፤” በሚል የቅጣት ማቅለያ ያቀረቡ ቢኾንም፣ ፍ/ቤቱ፥ “ጥፋተኞችንም ኾነ ሌሎች ግለሰቦችን ያስተምራል፤” በሚል አቶ ደመላሽ ጎሳ እና አቶ ዳዊት ሙሉጌታ፣ ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በ15 ቀን ቀላል እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፤
በሌላ በኩል፣ የሥር ፍ/ቤት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታና ግንባታ ሕገ ወጥ ነው፤ በሚል መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ የሰጠው ውሳኔ፣ የሚነቀፍበት ምክንያት እንዳላገኘበት የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፤ “መልስ ሰጪን መጥራት ሳያስፈልግ፣ ይግባኙ አያስቀርብም” በማለት መዝገቡን መዝጋቱን በተጨማሪ ትእዛዙ አስታውቋል፡፡ የደብሩ አስተዳደር፣  ለሰበር ሰሚ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡

Read 4180 times