Sunday, 28 May 2017 00:00

ምሁራን በፌደራል ሥርአቱ ስጋቶች ላይ ጥናቶች አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

• ፓርቲ በመንግስት ተቋማት ውስጥ ጣልቃ መግባቱ መገታት አለበት
• ተቃዋሚዎች በፓርላማ አለመኖራቸው ለስርአቱ ስጋት ነው ተባለ

የፌደራል ስርአቱ በህገ መንግስቱ መሰረት በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑ፣ የሀገሪቱን አንድነት ስጋት ላይ እንደጣለ ሰሞኑን የቀረቡት ጥናቶች ያመለከቱ ሲሆን በፓርላማው የተቃዋሚ ድምፅ አለመኖሩም ለፌደራል ስርአቱ ስጋት ነው ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከትናንት በስቲያ በተከናወነ የአንድ ቀን አውደ ጥናት ላይ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን “በፌደራል ስርአቱ ላይ” የቀረቡ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ካቀረቡት ምሁራን መካከል ፕ/ር አሰፋ ፍሰሀ፤ባለፉት 26 ዓመታት የተገነባው የፌደራል ስርአት የተለያየ ማንነት ያላቸውን ህዝቦች በራስ የመተዳደር መብት በማጎናፀፍና እርስ በእርስ በማቀራረብ በኩል ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤በዚህ መሃል ግን የዜጎች መብት በተለያዩ ግለሰቦች መጣሱ ለፌደራል ስርአቱ አደገኛ ነው ብለዋል፡፡
ዜጎች ከሀገራዊ እሳቤ ይልቅ ክልላዊና መንደራዌ እሳቤ ላይ ማተኮራቸው አሳሳቢ መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ፤ ይህን አመለካከት ለመቀየር በርካታ የፖለቲካ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የፌደራሊዝም ስርአቱ ዋነኛ አላማ፤ ጎሰኝነትንና ክልላዊነትን ማስፈን እንዳልሆነ ባልተገነዘቡ ሰዎች፣ ባልተገባ መንገድ እየተተረጎመ መሆኑንም አስረድተዋል -ምሁሩ፡፡  
በፌደራሊዝም ስርአት ግንባታ ውስጥ ዋነኛ ምሰሶ የሆነው ህገ መንግስቱ በሚገባ በተግባር ላይ ካልዋለ ቅሬታና ግጭት እንደሚያስነሳ በጥናታቸው ያመለከቱት ሌላው የፅሁፍ አቅራቢ ፕ/ር ካሣሁን በሪሁን፤ ህገ መንግስቱ መሬት ላይ ሲተረጎም በአግባቡ አለመሆኑ የፌደራሊዝም ስርአቱ ተግዳሮት ነው ብለዋል፡፡ የመንግስትና የፓርቲ ጉዳይ መደበላለቅም የወቅቱ የፌደራሊዝም ስርአቱ እንቅፋቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ጥናት አቅራቢዎቹ፤ ፓርቲ በመንግስት ተቋማት ውስጥ ጣልቃ መግባቱ መገታት አለበት ብለዋል፡፡  
“በቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች፣የሌላ ብሄር ተወላጆች በየጊዜው መፈናቀላቸው ብሄርና ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌደራሊዝም ውጤት ነው” የሚል አስተያየት ከመድረኩ የተሰነዘረ ሲሆን ጥናት አቅራቢዎች፤ ”የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ችግር የፈጠረው ነው” ብለዋል፡፡ ፌደራሊዝሙ ለምን በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና በህዝብ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አይሆንም የሚል ጥያቄም ከተሣታፊዎች የተሰነዘረ ሲሆን ከመድረኩ በተሠጠው ምላሽ፤ ከዚህ በኋላ አሁን ያለውን የፌደራል ስርአት ቅርፅና ይዘት አጠናክሮ ከማስቀጠል ውጪ ወደ ኋላ መመለስ አደጋ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ “ችግሮቹን ነቅሶ አውጥቶ፣ እያረሙና እያስተካከሉ መጓዝ እንጂ ከዚህ በኋላ እንደገና መመለስ የሚፈጥረው ቀውስ ከባድ ይሆናል”
“የማንነት፣ የወረዳና ዞን እንሁን” ጥያቄዎች በሰፊው እየቀረቡና ለግጭትም መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው ፌዴራሊዝሙን አደጋ ላይ እንደጣለው የተጠቆመ ሲሆን መፍትሄው ፖለቲካዊ መግባባት መፍጠርና የዜጎች ድምፅ የሚሰማበትን አማራጭ ማስፋፋት ነው ተብሏል፡፡
የዘንድሮ 26ኛው የግንቦት 20 በዓል፤ ‹‹የህዝቦች እኩልነት፣ ፍትሃዊነትና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአት እየገነባች ያለች ሃገር›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ሲሆን በዓሉ በዋናነት በክልሎችና በውጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በድምቀት እንደሚከበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Read 6491 times