Sunday, 28 May 2017 00:00

ለድርቅ ተጎጂዎች፤የ398.4 ሚ. ዶላር አስቸኳይ እርዳታ ጥሪ ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በድርቁ ምክንያት የማሽላ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል
     በኢትዮጵያ ለሚገኙ 7.8 ሚሊዮን የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች፤ 398.4 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት፣ ከትናንት በስቲያ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ባስተላለፈው ጥሪ አስታውቋል፡፡
በአሁን ወቅት ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር፣ የኢትዮጵያ የላቀውን ድርሻ መያዙን አስታውቆ፤ ከግንቦት እስከ ጥቅምት ወር ላለው ጊዜ ብቻ የ319.3 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡  
የተጠየቀው እርዳታ ካልተገኘ ሁኔታው አሳሳቢ እንደሆነ የጠቆመው ድርጅቱ፤ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚጠበቀው ዝናብ አለመገኘቱና በመላው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰብል አጥፊ የተምች ወረርሽኝ መከሰቱ የተረጂዎችን ቁጥር ሊያሻቅበው እንደሚችልም ስጋቱን አስታውቋል፡፡    
በኢትዮጵያ በቅርቡ የተረጂዎች ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን ወደ 7.8 ሚሊዮን እንዳሻቀበው ሁሉ፣ በሶማሊያም ከ2.9 ሚሊዮን ወደ 3.2 ሚሊዮን ማሻቀቡን ድርጅቱ ጠቁሞ፤ለሶማሊያ የድርቅ ተጎጂዎች ለ5 ወር የሚሆን የ290.7 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ያስፈልጋል ብሏል። በኬንያም የ30.2 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ያስፈልጋል ያለው ድርጅቱ፤በአጠቃላይ ሶስቱ ሀገራት ለገጠማቸው ችግር ለ5 ወራት መቋቋሚያ 719.3 ሚሊዮን ዶላር የአለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲለግስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በድርቁ ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መሆኑን የጠቆመው ተቋሙ፤እስካሁን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ብቻ 116,660 ሰዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል፡፡ በኬንያም 38,660 ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ብሏል ተቋሙ፡፡ ድርቁን ተከትሎ በኢትዮጵያ የማሽላ ዋጋ ባለፈው አመት ከነበረው በእጥፍ (48 በመቶ) መጨመሩን አመልክቷል- የዓለም ምግብ ፕሮግራም፡፡

Read 2843 times