Sunday, 28 May 2017 00:00

ለቀጣዩ ዓመት ምርጫ፤ ከግማሽ ሚ. በላይ ምርጫ አስፈፃሚዎች ይመደባሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

• ከ62 ፓርቲዎች ህጋዊነትን ያሟሉት 10 ብቻ ናቸው ተባለ
• ቦርዱ ከኢንሣ ጋር የ18 ሚ. ብር ውል ተፈራርሟል
   በመጪው ዓመት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ከ500 ሺ በላይ ምርጫ አስፈፃሚዎች እንደሚመደቡ፣ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡ ለምርጫው ሂደት አፈፃፀም ቦርዱ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግና ከሌሎች መ/ቤቶችም ባለሙያዎችን  እንደሚያንቀሳቅስ ተገልጿል፡፡
ቦርዱ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንደገለፁት፤ መጪውን የአካባቢ ምርጫ ነፃ፣ ግልፅና ፍትሃዊ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባር ላይ ለማዋል ተዘጋጅተዋል፡፡ ከኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዘመናዊ የአይቲ ሥራ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ቀጥረው እንደነበር የገለፁት ፕሮፌሰሩ፤ ባለሙያዎቹ የተሻለ ደሞዝ ፍለጋ ጥለዋቸው እንደሄዱ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ከኢንሳ ጋር በመነጋገርና 18 ሚሊዮን ብር የሥራ ውል በመፈራረም ወደ ሥራ ገብተናል ብለዋል፤ሰብሳቢው፡፡
ቦርዱ በህጋዊነት መዝግቧቸው ከሚንቀሳቀሱ 22 አገር አቀፍ እና 40 ክልላዊ፣ በጠቅላላ 62 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅና በፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ መሰረት፣ የህግ ጉዳዮችን ያሟሉ 5 አገር አቀፍና 5 ክልላዊ ፓርቲዎች ብቻ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ ቀሪዎቹ 17 አገር አቀፍና 35 ክልላዊ፤ በጠቅላላው 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች የህግ ጉዳዮችን በከፊል ያሟሉ ናቸው፡፡
በ2008 በጀት ዓመት በፌደራል ወይም በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማከፋፈል ቦርዱ ከመንግስት ያስፈቀደው 10 ሚሊዮን ብር፣ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) 7.339.385.48 ብር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ  ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) 1.298.882.68 ብር እንዲሁም የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) 352.653.63 ብር እንዲከፈላቸው ተደርጓል። ቅድመ ሁኔታውን ያላሟሉ 4 ፓርቲዎች፡- የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ)፣ የአርጎባ (ጋሕአዴን) እና የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ክፍያ ያልተፈጸመላቸው መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡  


Read 4344 times