Sunday, 28 May 2017 00:00

ከሣኡዲ መመለስ ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አስግቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

• ጠ/ሚ ኃይለማርያም፤ ዜጎች ያሳዩት ቸልተኝነት አሳስቦኛል ብለዋል
• ቀነ ገደቡ 30 ቀናት ቀርቶታል፤ የተመለሱት ከ30ሺ አይበልጡም
• ከ150ሺ በላይ ዜጎች ያለ ህጋዊ ፈቃድ እንደሚኖሩ ይገመታል
• ከ5ሚ.በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች አገሪቱን ለቀው ይወጣሉ

የሣኡዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ህገ ወጥ ናቸው ያላቸው የተለያዩ ሃገራት ዜጎች፤ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ 30 ቀናት ብቻ የቀረው ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት፣ ዜጎች እድሉን ለመጠቀም ያሳዩት ቸልተኝነት አሳስቦኛል ብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ ከትላንት በስቲያ ወደ ሣኡዲ ተጉዘው ከሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ኢትዮጵያውያኑ በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ፣ ችግር ሳይገጥማቸው በሚወጡበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ታውቋል። ኢትዮጵያን ሠራተኞች ከዚህ በኋላ ያለ ችግር በኤጀንሲዎች አማካይነት ሄደው፣ በሣኡዲ መስራት የሚያስችላቸው የሠራተኛ ስምሪት ስምምነትም የሁለቱ ሃገራት የሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተፈራርመዋል ተብሏል፡፡
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ዜጎች በተቀመጠው ቀነ ገደብ ለመመለስ ያሣዩት ቸልተኝነት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልፀው፤ ቤተሰቦችና ሁሉም ዜጋ በሳኡዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከቀነ ገደቡ በፊት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ያቀርቡ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡
ቀነ ገደቡ ካለቀ በኋላ ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ የተሠጣቸውን እድል ተጠቅመው ቢመለሱ መልካም እንደሆነ በመጠቆምም፤መንግስታቸው ለሳኡዲ ተመላሾች የስራ እድል እንደሚያመቻች ጠ/ሚሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አባ ማቲያስ በተመሳሳይ፤ ዜጎች የምህረት አዋጅ ጊዜውን ተጠቅመው ያለ አንግልት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሣኡዲ ባስቀመጠችው የ90 ቀን ገደብ፤ ከ5 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው ይወጣሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን እስካሁን የወጡት ከግማሽ ሚሊዮን እንደማይበልጡ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡
ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፍቃድ ሳይኖራቸው በአገሪቱ እንደሚኖሩ የተገመተ ሲሆን እስካሁን የተመለሱት ከ30 ሺህ አይበልጡም ተብሏል፡፡ የተቀመጠው ቀነ ገደብም ሰኔ 20፣ 2009 ይጠናቀቃል፡፡ የኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ሶማሊያና ፊሊፒንስ ዜጎች በሃገሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ታውቋል፡፡
የሣኡዲ መንግስት ህገ ወጥ የሚላቸው፤ በህገ ወጥ መንገድ የሃገሪቱን ድንበር አቋርጠው የገቡ፣ለፀሎት ስነ ስርአት ሄደው በዚያው የቀሩ፣ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው፣ የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜ ያለፈባቸውና ያላሣደሱ፣ የስራ ፍቃድ ቢኖራቸውም የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው… የውጭ ዜጎች መሆኑ ታውቋል፡፡
 ከሁለት አመት በፊት ሣኡዲ፤ ህገ ወጥ ባለቻቸው የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ላይ በወሰደችው ከሃገር የማባረር እርምጃ  ከ160 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ አልፈው ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው የሚታወቅ ሲሆን በአጠቃላይ ከአገሪቱ 2.5 ሚሊዮን የተለያዩ ሃገራት ዜጎች መባረራቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል።









Read 5297 times