Sunday, 28 May 2017 00:00

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ስለ ኢቢሲ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

    (ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ ውይይቶች)

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ተጠሪነቱ ለህዝብ እንደራሴዎች ነው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ሚዲያ አልሆነም የሚሉ ትችቶችና ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ በ10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ኢቢሲን ጨምሮ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ወገንተኛ መሆን እንዳልቻሉ አመልክቶ ነበር፡፡ ከሰሞኑም ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ችግሮች የሚቀርፍ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያደርግ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት
ታዟል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ችግሮች ምንድን ናቸው? ለምን የህዝብ አመኔታ ማግኘት ተሳነው? እንዴትስ ተሻሽሎ የህዝብን ቀልብ መግዛት ይችላል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የቀድሞ ማስታወቂያ ሚኒስትር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲከኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

             “ኢቢሲ ከማንኛውም ፓርቲ ነጻ መሆን አለበት”
              ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ፖለቲከኛ)

---------------------

                  “የኢቢሲ ጉድለቱ በአስተሳሰብ ብዝኃነት አለማመኑ ነው”
                   አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

      ኢቢሲ እስካሁን ህዝብ የሚተማመንበት ሚዲያ መሆን ያልቻለው ሥርአቱ፤ ጣቢያው በዚህ መልኩ እንዲሰራ ስለፈለገ ነው፡፡ በዚህ መልኩ እንዳይሰራ ቢፈለግ መቀየርና ማሻሻል ያስቸግራል ብዬ አላስብም፡፡ እንደ‘ኔ ዋናው የኢቢሲ ጉድለቱ በአስተሳሰብ ብዝኃነት አለማመኑ ነው፡፡ ሚዲያው እንደ ሚዲያ ፖሊሲ ሊኖረው ይችላል፣ “ነፃና ገለልተኛ” ነን ሲሉም ይደመጣል፤ ግን በተግባር እየሰራ ያለው እንደሱ አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ ሆን ተብሎ የሚደረግ ነው፡፡ በብቃት ማነስ ወይም በስህተት አይደለም፡፡ ብዝኃነትን እንዳያስተናግድ የተደረገው ሆን ተብሎ ነው፡፡
ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለማምጣት በሚደረግ ትግል ውስጥ ጣቢያው በተቃራኒው ነው እየተጓዘ ያለው፡፡ ዲሞክራሲ ማለት ግዑዝ ነገር አይደለም። በቃ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማስተናገድ ነው። ህዝቡን የሚመስል ሚዲያ መፍጠር ነው፡፡ ኢቢሲ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው እየሄደ ያለው። የመረጃ ማቅረብ ስራ ሳይሆን የአንድን ፓርቲ አይዲኦሎጂ በማራመድ የፕሮፓጋንዳ ማስረፅ ስራ ነው የሚሰራው፡፡ ይሄ አይነት ሚዲያ ደግሞ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ቅኝት ውስጥ ነው ሊታይ የሚችለው፡፡ በዲሞክራሲ ሂደት ይሄ አይነት ሚዲያ የሚፈለግ አይደለም፤ ተቃራኒ ውጤት የሚያመጣ ነው፡፡ ይሄ በእውቀት ችግር ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር ነው፡፡
 ይሄ ደግሞ እንዳየነው ለራሱ ለስርአቱም ለህዝቡም አልጠቀመውም፡፡ እንደውም ስርአቱ በህዝብ እንዲጠላ፣ ከህዝብ ጋር እንዲራራቅ ነው ያደረገው፡፡ ስለዚህ ኢቢሲ ለመንግስት ከመኖሩ ይልቅ ባይኖር ይመረጣል፡፡ ህዝብ እንደማያምነው የምንረዳው፣ በገጠር አካባቢ እንኳ ሳይቀር፣ ድሃ የሚባለው ህዝብ ጭምር ተበድሮም ቢሆን ሳተላይት ዲሽ አስገብቶ የውጪ መገናኛ ብዙኃንን እያየ ነው ያለው፡፡ ይሄ መሬት ላይ ያለ ሃቅ ነው። ለአንድ መንግስት ደግሞ መደመጥ ያለመቻልን ያህል ትልቅ ውድቀት የለም፡፡ ስለዚህ አሁን ህዝቡና መንግስት የሚገናኙበት መስመር የላቸውም፡፡ ኢቢሲን ማዳመጥ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሳል። ብዙ ጊዜ ህብረተሰቡ ከሚያውቃቸው እውነታዎች የራሱ ነገሮችን ስለሚያስተላልፉ እውነት ቢናገሩ እንኳ የማያምንበት ደረጃ ደርሷል፡፡ በህዝብና በመንግስት ሚዲያ መካከል ያለው የመተማመን ድልድይ ተሰብሯል ማለት ይቻላል፡፡
አንድ ነገር ግን አስረግጦ መናገር ይቻላል፤ ኢቢሲ እንዲቀየር ወይም ለውጥ እንዲያመጣ አይፈለግም። ቢፈለግ ኖሮ 25 ዓመት መጠበቅ አያስፈልገውም ነበር፤ አንድ ሳምንት ብቻ በቂ ነው፡፡ ያልተቀየረው እንዲቀየር ስላልተፈለገ ነው። አሁንም እንዲቀየር ይፈለጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይሄ ደግሞ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ እንዲሄድ አድርጎ በመጨረሻም የስርአቱን ውድቀት ያፋጥነዋል፡፡ እኔ ኢቢሲ አካባቢ ያሉ ሰዎችን መንግስትም በሚገባ የሚያውቃቸው አይመስለኝም፡፡ ጣቢያው የተዛባ መረጃ ሆን ብሎ ሲያስተላልፍ፣ እንዲያርም ሲጠየቅ እንኳ የመንግስት ትዕዛዝን አይቀበልም፡፡ ስለዚህ ጣቢያውን ማን እንደሚያዘውም አይታወቅም፡፡ የተለየ ኃይል የሚያዘው ሚዲያ ነው የሚመስለው፡፡
አንድን ሚዲያ ነፃና ገለልተኛ ማድረግ ማለት የሮኬት ሳይንስ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም፡፡  ተቋሙ በህገ መንግስቱ መሰረት እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ ግልፅ የሆነ ፖሊሲ አስቀምጦ፣ ለሙያቸው ተገዥ የሆኑ ሰዎችን መመደብ ነው፡፡ ግን በቦታው በተቃራኒው ያለው ካድሬ ነው፡፡ የለውጥ እርምጃ ለመውሰድ የፈለጉ ሰዎች‘ኮ ሳይወሉ ሳያድሩ ሲባረሩ አይተናል፡፡

----------------------

                            ‹‹ኢቢሲ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን ሃላፊነቱንም አልተወጣም››
                         ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

       ኢቢሲ ለህዝብ ምን ያህል ሰርቷል ለሚለው ጥያቄ፤ ቀላሉ መልስ ምንም! የሚለው ነው፡፡ እንደውም የዜጎች ድምፅ ከመሆን ይልቅ ለመንግስት ነው ያገለገለው፡፡ ህዝብ መከቱን እንዲያውቅ መንግስት ግዴታውን እንዲወጣ በማድረግ በኩል ባለፉት 25 ዓመታት ሚናውን አልተወጣም። በተቃራኒው መንግስትን ዘላለማዊ ለማድረግ ሲሠራ ነው የታዘብነው፡፡ የህዝብን በደልና ቅሬታ ሲያስተናግድ አለየሁም፡፡ ህዝብ የመንግሰትን ባለስልጣናት ስህተት ሰርታችኋል፤ የሚል ጥያቄ ለማቅረብ የህይወት መስዋዕትነት እስከ መክፈል የሄደው ብሶቱን ድምፁን የሚያሰማለት ተቆርቋሪ ሚዲያ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ ኢቢሲ አገልግሎቱ ለመንግስት እንጂ ለህዝብ አይደለም። በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን ሃላፊነቱንም አልተወጣም።
የህዝብ ድምፅ ለምን እንዳልሆነ ለማወቅ በየእስር ቤቱ የተወረወሩ ጋዜጠኞችን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ራሳቸው የሚቆጣጠሩት ሚዲያ፣ ጋዜጠኞች ይቅሩና በግላቸው ገንዘባቸውን አውጥተው ሚዲያ እናቋቁም ያሉ ጋዜጠኞች፤ የመንግስትን አሠራር በመተቸታቸው ማረፊያቸው እስር ቤት ነው የሆነው፡፡ ጣቢያው የኛ የተቃዋሚዎችን ድምፅ ለህዝብ ለማስተጋባት ቀርቶ እኛን ለማጥቃት ነበር የሚሠራው፡፡ ለበህዝቡ እንደ ጭራቅ መስለን እንድንታይ በምርጫ ወቅት ዶክመንተሪ ሳይቀር የሠራብን ጣቢያ ነው፡፡ በዚህ በፖለቲካው አካባቢ ከ7 አመት በላይ ቆይቻለው፤ ነገር ግን ኢቢሲ በ”ስርአት መጥቶ እስቲ የእናንተ አስተሳሰብ ምንድን ነው” ብሎ ጠይቆ ለህዝብ ያደረሰበት አጋጣሚ የለም፡፡ አንድ ጊዜ ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር ኢንተርቪው አድርጌ ሁሉም ድምፁ ጠፋብን ብለው ሳያስተላልፉ ቀሩ፡፡ የኔ ኢንተርቪው በሚገርም ሁኔታ ጠፍቶባቸው ማስተላለፍ ሳይችሉ ቀሩ፡፡
እዚህ ሃገር ህዝብ ስልጣን ሲኖረው ነው፣ሁሉም ነገር የህዝብ የሚሆነው የሚል እምነት አለኝ። የሚዲያውም ጉዳይ በዚሁ የሚታይ ነው። ፓርላማውም ቢሆን በገዥው ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ስር ያለ ነው፡፡ እንደውም በእነዚሁ ጥናት መሰረት፤ ኢቢሲ እና ፓርላማው ባይኖር፤ ሃገሪቷ ምንም የሚቀርባት ነገር የለም፤ልትቀጥል ትችላለች ብለው ነው እነሱ ራሳቸው ያረጋገጡት፡፡
ዞሮ ዞሮ ችግሩን እያወቁት ስለሆነ መፍትሄ የማይፈልጉት፣ ፍላጎታቸው ግልፅ ነው፤በስልጣን መቆየት፡፡ ስለዚህ አሁን በተያዘው መንገድ ብዙ ለውጥ አይጠበቅም። እንደውም ኢቢሲን ከማሻሻል በራሳቸው ጥረት የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ማሰር ማቆም በቂ ነው፡፡

------------------------

                   “የትኛው ባለስልጣን ነው በኢቢሲ ጣልቃ የሚገባው?”
                 አቶ ግርማ ሠይፉ (ፖለቲከኛ)

      ህገ መንግስቱ ላይ በህዝብ ፋይናንስ የሚደረግ ሚዲያ፤ምን ተግባር መፈፀም እንዳለበት በግልፅ ተቀምጧል፡፡ እሱን ለምን አላከበራችሁም ብሎ ለመጠየቅ ደግሞ “ይሄን እንዲጠይቅ የተቀመጠው ምክር ቤት” ራሱ ህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት ነው ወይ የሚሰራው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። የም/ቤቱ አባላት ለህሊና ሳይሰሩ ቀርተው “ኢቢሲን በተቀመጠልህ መሰረት አልሰራህም” ማለታቸው ብዙም ውጤት አያመጣም ባይ ነኝ፡፡ ፓርላማው ባለስልጣናት ኢቢሲ እየደወሉ ጣልቃ ይገባሉ ብሏል። የትኛው ባለስልጣን ነው ጣልቃ የሚገባው? ለምን በስም አይጠቅሱም? ይሄ ግልፅነት እንደሌላቸው ነው የሚያሳየው፡፡
ኢቢሲ የተቀመጠለትን ቻርተር መሰረት አድርጎ ቢሰራ ኖሮ፣ የህዝብ ተቀባይነት ይኖረው ነበር። እንዲመጣ ለሚፈለገው ዲሞክራሲም አጋዥ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ ስርአቱ ለዚህ አይነቱ ሁኔታ የታደለ አይደለም፡፡ የትኛው ተቋም ነው በነፃነት የሚሰራው? ኢቢሲ ብቻ የተለየ ነገር የለውም፡፡ በሁሉም ሲስተም ነው ችግሩ ያለው። ትልቁ ጉዳይ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ነው። የፖለቲካው ምህዳር ባልሰፋበት ስለ ኢቢሲ መለወጥ ብቻውን ማውራት ዋጋ የለውም፡፡     

------------------------

                     “ኢቢሲ የህዝብ ድምጽ ሆኖ አያውቅም”
                  አብርሃ ደስታ (ፖለቲከኛ)

      እኔ ኢቢሲን የማየው እንደ ህዝብ ድምፅ ሳይሆን የህዝብን ድምፅ ለማፈን የተዘጋጀ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ያህል ነው፡፡ የህዝብ አፈና እንዳይጋለጥ ያፍናል፡፡ ይሄ ደግሞ ከፖለቲካ ምህዳሩ ጋር ነው የሚያያዘው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ዲሞክራሲን ለማስፈን ቢፈልግ፤ ሚዲያውም ይስተካከል ነበር። እስካሁን ድረስ ግን ኢቢሲ በኔ አተያይ የገዢው ፓርቲ የማፈኛ መሳሪያ እንጂ የህዝብ ድምፅ ሆኖ አያውቅም፡፡
እኛም ጣቢያውን እንደ ኢህአዴግ ድርጅት ስለምንመለከተው ቀርበን ሀሳባችንን እንዲያስተላልፍልን አልጠየቅነውም፤ እሱም አልጠየቀንም፡፡ ስለዚህ የኛን አስተሳሰብ እንኳ በጣቢያው በኩል ህዝብ ያወቀበት አጋጣሚ የለም። ይሄ የአስተሳሰብ ብዙኃነት ለማስተናገድ ዝግጁነት እንደሌለው ማሳያ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጣቢያው ችግር የሚመነጨው ከኢህአዴግ የሚዲያ አተያይና ፖሊሲ ነው፡፡ በኢቢሲ ውስጥ ያሉ ሰዎች ትንሽ ወጣ ብለው ሊሰሩ ቢሞክሩ እንኳ ኢህአዴግ እርምጃ መውሰዱአይቀርም፡፡ የህዝብ ድምፅ ለመሆን ሙከራ ቢያደርግ፣  ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደማይፈቅዱለት ነው እኔ የምረዳው፡፡
ኢቢሲን ከማስተካከል ይልቅ ሌላ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል የግል ሚዲያ እንዲኖር መፍቀድ ነው የሚሻለው፡፡ የግል ሚዲያ በእውነተኛ ነፃነት እንዲሰራ ከተደረገ፣ ኢቢሲ ሳይወድ በግዱ ወይ ያስተካክላል አሊያም በአቋሜ እቆርባለሁ ካለ፣ በዚያው ይሞታል ማለት ነው፡፡ ለኔ በዚህች ሀገር የህዝብ ድምፅ የሚስተናገድበት ሚዲያ መፍጠር ከተፈለገ አማራጩ ይሄ ይመስለኛል፡፡

Read 7724 times