Sunday, 28 May 2017 00:00

እንግዳ እና ‘ሬድ ሌብል’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…አንድ የምናውቀው ሰው እቤቱ የዘመድ እንግዶች ድንገት ይመጡበታል። እንዳጋጣሚ ሆኖ ከተገናኙ ረጅም ጊዜ ነበር። ቀድመው ሳይደውሉ ወይም በሌላ መንገድ እንዲያውቅ ሳያደርጉት አንድ እሁድ ቀን ‘ከች’ ይላሉ፡፡ እሱ ደግሞ ኑሮ ትንሽ ጠመም ብሎበት ከሚስቱ ጋር ጀርባ አዙረው መተኛት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…(በኑሮም ቅጣት፣ ‘በዛም’ ቅጣት!) ደግሞላችሁ…“ከሬድ ሌብል፣ ከኋይት ሆርስ፣ ከቆርቆሮ ቢራ የትኛው ይሻልሀል?” ብሎ ልግስና ቀርቷል።
እናማ… ሚስቱ ወጣ ትልና ከእንትና ሱቅ በዱቤ ለስላሳ ምናምን ገዛዝታ ትመጣለች፡፡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው…የእንግዶቹ ፊት ‘አሸቦ’ መሰለላችሁ። ውስኪውስ? ቆርቆሮ ቢራውስ! “ይሄ ጥሬ ሥጋ ሙልጭ ብሎ ካላለቀማ መጣላታችን ነው!” የሚባለው ያዙኝ፣ ልቀቁኝ ግብዣውስ! ‘እንግዶቹ’ በስንት ጊዜያቸው እግር ጥሏቸው ቢመጡ… የለመዱትን ውስኪና ጥሬ ሥጋ ስላላገኙ…እንዳኮረፉ ተቀምጠው፣ እንዳኮረፉ ሄዱና አረፉት፡፡  
እኔ የምለው… ጊዜ እኮ ተለውጧል! ባለ ሸላይ መኪና እንደበዛው ሁሉ ባለጠማማ ጫማዎችም በዝተናል እኮ! በዕቃ ብዛት ‘ጧ’ ሊሉ የደረሱ የኮንዶሚንየም አንድ ክፍል ስቱዲዮ የሚያካክሉ ‘ፍሪጆች’ እንደበዙ ሁሉ፣ ሦስት ድስት አጣበው ሊይዙ የሚችሉ፣ አሁን ግን ነፋስ ሞልቶ የተረፋቸው ‘ፍሪጆች’ በዝተዋል እኮ! እናማ እንኳን ጥሬ ሥጋ ሊያቀርብ ሚስቱ የባልነት መብቱ ላይ እንኳን ማዕቀብ ጥላበት ይታዘንለታል እንጂ ይኮረፋል!  ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የምር ግን ዘንድሮ ‘እንግዳ ማስተናገድ’ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በገንዘብ ችግር የጤፍ ፍጆታውን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀምሳ በመቶ የቀነሰው ሰውዬ እንዴት ነው ብላክ ሌብል ውስኪ፡ ዊንተር ምናምን ቮድካ ሊያቀርብልን የምንጠብቀው! ዘንድሮ አሥራ ምናምን ብር የገባች ስኒ ሻይም ከቀረበ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ደግሞላችሁ…በፊት ከዘመድ ወይም ከጓደኛ ‘እንግዳ’ ጋር እንደ ልባችን እናወራ ነበር፡፡ አለ አይደል …
“ምን ይለኛል?”  
“ደግሞ ቀድታኝ ሄዳ ለማን እንደምትናገር ማን ያውቃል!”
“እንዲህ አለች ብላ ከሰው ብታቆራርጠኝስ!”
“‘እናንተን አይወዳችሁም ብሎ ቢያስጠቁረኝስ!” (ቂ…ቂ…ቂ… ልጄ ዘንድሮ ‘መጥላት’ ብቻ ሳይሆን ‘አለመውደድም’… ‘ጥርስ የሚያስነክስበት’ ዘመን ሆኗል።)
አይነት ስጋቶች የሉብንም ነበር፡፡ መቀለድ ብንፈልግም ለሳቅ ያልነው ዞሮ እኛ የምንሳቀቅበት ይሆናል የሚል ስጋት አልነበረንም፡፡
ዘንድሮ ሁሉም ተለውጧል፡፡ እና በፊት ‘የኩሼ’ ቤት ወሬ እንኳ ሳንደባበቅ እናወራው የነበረውን ሰው “ከእንትን ፋብሪካ የገዛሁት አንሶላ እንደተመቸኝ ነገር…” ብንለው… የሆነ ‘ቡድን ውስጥ ልንከተት’ እንችላላን፡፡ (ሰው በሚጠጣው ቢራ ‘የእንትን ቡድን አባል’ የሚባልበት ዘመን! “ስንት ባንክ እያለ አንተ እዛ ባንክ ምን ወሰደህ!” የሚባልበት ዘመን!)
ደግሞላችሁ…የሆነ ‘የዘመድ እንግዳ’ ይመጣል፡፡ እንዴት ናችሁ ምናምን አይነት ልውውጥ ይካሄዳል።
“ባለቤትህ ደህና ነች?”
“ደህና ነች፡፡”
“ምነው፣ የለችም እንዴ?“
“አክስቷ ታመው ወደ አስኮ አካባቢ ሄዳለች…” ትላላችሁ፡፡ ዘመዶች ለጥቂት ጊዜ ዝም ይላሉ፡፡ ከዛም…
“አክስቷ ሞታለች አልተባለም እንዴ?”
“ይቺኛዋ በአባት በኩል ያለችው ነች፡፡”
“ነ…ው!” የድምጹ ቃና “ድንቄም አክስት!” አይነት ነው፡፡ “ዘንድሮ አክስቴ አጎቴ እያሉ የሚሄዱ ሚስቶች ምንም ደስ አይሉኝም” ይባላል፡፡
እኔ የምለው…በአክስትና ለቅሶ ቤት ለሰልስት በማደር ማሳበብ ቀርቷል እኮ! ዘንድሮ ‘ሌላ ነገር ቢያስቡ’ እንኳን ምን ሰበብ ያስፈልጋል፡፡ “ጉዳይ አለኝ፣ ማታ ትንሽ እቆያለሁ…” ማለት በቂ ነው። እናማ… በሰላም የተቀመጠውን ሰው ‘የዘመድ እንግዶች’ ሚስቱን እንዲጠረጥር ሊያደርጉት ይሞክራሉ፡፡
ከሆኑ ሰዎች ጋር ሰብስብ ብላችሁ ባላችሁበት የድሮ ትምህርት ቤት ጓደኛ ይመጣል፡፡
“አጅሬው፤ አንተ እኮ ድሮም ቢሆን የዋዛ አልነበርክም፣፡”
ስሙኝማ...አንዳንዴ የድሮ ጓደኛ ችግሩ ምን መሰላችሁ…ጨዋታ ያሳመረ ይመስለውና…በቃ፣ ኤድዋርድ ስኖውደን ሆኖ ቁጭ! ስንት ዘመን ሁሉ ከአገር ምስጢርነት ባልተናነሰ ስትጠብቁት የኖራችሁትን ሁሉ…አለ አይደል…አውላላ ሜዳ ላይ ያሰጣዋል ነው የምላችሁ።
“ስማ..ያኔ ዘጠነኛ ክፍል ሳለን…ትዝ ይልሀል…አስረኛ ዲ ክፍል ጓሮ…” ብሎ ‘መቀባጠር’ ሲጀምር…ፈጠን ብላችሁ
“አዎ… ጊዜ ይሮጣል አይደል!” ምናምን ትላላችሁ። ከዛም… “አንተ ግን የት ጠፍተህ ነው የከረምከው! ከተገናኘን ቆየን እኮ…” ድንበር ዙሪያ ግንብ መገንባት በሉት፡፡ ዝም ብሎ ከለፈለፈ ሁሉም ነገር በማግስቱ ጠዋት መብራት ባለበትም፣ መብራት በጠፋበትም (‘አብዛኛውን ቦታ’ ለማለት ያህል!) ሁሉ ይዛመትላችኋል። እሱዬው ግን የተቦተረፈ የጤፍ ጆንያ ምናምን ነገር ይሆንላችኋል፡፡
“ስማ እሷ ልጅ አለች እንዴ…”
ሰውዬው አሞታል እንዴ!
“እኔ እንጃ፣ የስንት ዘመን ወሬ ነው የምታወራው…” ስንት ነገር ተቀይሯል፡፡ ጭቃ ሹሞች ተለውጠዋል፣ ሚሌኒየሙ ተለውጧል፣ የእንትናዬዎች የዳሌ ቅርጽ ተለውጧል! እሱ የድሮ አስረኛ ዲ ክፍል ጓሮ ወሬ ያወራል!
ይሄኔ የሆነ ሰው የኮረኮረው ይመስል ከት ብሎ ይስቃል፡፡
“ስማ…እኔ እኮ እስካሁን የማልረሳው ከንፈሯ እንደዛ የተፈነከተ ሀብ፣ ሀብ የመሰለው እንዴት አድርገህ ብትስማት ነው!…ቦይ ፍሬንዷ ሰምቶ ብረት ቦክስ ይዞ የመጣው ትዝ አይልህም!”
ይሄኔ በቃ ኩላሊት፣ ጉበት ምናምን ቦታ ሲለዋወጡ ይታወቃችኋል፡፡ እንደ ምሳሌ የምትታዩትን ሰው!
“ምን አይነት የተባረከ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገው…” የምትባሉትን ሰው!
“ሰው ቀና ብሎ አያይም፣ እንዴት አይነት የተባረከ ሰው መሰላችሁ!” የምትባሉትን ሰው!
“ቁመቱ ባያጥር ኖሮ  (ቂ…ቂ…ቂ…) ልጄን ከአራት ልጆቿ አባት አፋትቼ እድርለት ነበር…” የምትባሉትን ሰው!
ደግሞላችሁ የዘመድ እንግዶች አሉላችሁ፡፡ የሆኑ  የሥራ ባልደረባችሁ፣ ወይም የኮንዶሚኒየም ጎረቤት፡ (ይቅርታ…ከጎን ያለ በሩ ሁልጊዜ የሚዘጋ ቤት እንጂ ለካስ የኮንዶሚኒየም ጎረቤት የለም…) ብቻ የሆኑ ሰዎች አብረዋችሁ አሉ፡፡ እና አንዷ ‘ዘመድ’…
“አንተ በቃ እምቢ አልክ አይደል…” ትላለች፡፡ የምን ነገር! በቃ… ‘ፈንጂ ወረዳው’ ፊታችሁ መጥቶ ድቅን፡፡
በኮንዶሚኒየሙ ‘ከጎናችሁ ወደሚኖረው’ ሰው ዘወር ብላችሁ…
“የውሀውን ጉልበት ለምንድነው የማይጨመሩልን! እኔ’ጋ እኮ ብታያት እንደ ዓይን ጠብታ ነው የምትወርደው።”
‘ዘመድ’ ትቀጠላለች፡፡ ‘ምልክቱ’ አልገባትማ!
“ያቺን የመሰለች ልጅ አግባ ስትባል እምቢ ብለህ አሁን ብታያት እንዴት አይነት ሴት ወይዘሮ መስላለች…ስንትከረፈፍ አመለጠችህ…”
ሌላኛዋ ‘ዘመድ’ ትቀጥላለች…
“እሱ እባክሽ ሲነግሩት መች ይሰማል..ድሮስ እንዴት ያስቸግረን እንደነበር አታስታውሺም!...” (ይሳሰቃሉ)
የመጀመሪያዋ ትቀጥላላች…
“እሱንማ ተዪው… ጎጃም በረንዳ እየሄደ አረቄውን ላይ በላይ መገልበጥ ለምዶ መለኪያዋን አክሎ ነበር እኮ…እሱን አወፍር ብዬ ያረድኩት ሙክት አንድ በረት ይሞላል…” (ይሳሳቃሉ)
ዙሪያችሁ ያሉ ሰዎች ልክ በሪሞት ኮንትሮል ይመስል በአንድ ጊዜ ግንባራቸው መስመር ያለው ሉክ መስሎ ቁጭ!
“ከውሀ በስተቀር ምንም ቀምሶ የማያውቅ” ሰው የምትባሉ ናችሁ እኮ! “ለምን አንድ ሁለት ቢራ አንጠጣም…” ለማለት እንኳን ‘እናስቀይመዋለን’ ተብሎ ተፈርቶ ከማኪያቶ ውጪ አትጋበዙም እኮ!
በ‘መልካም ጠባያችሁ’ የተነሳ “ለምንድነው ዓለም አቀፍ ሽልማት የማይሰጠው…” ብለው የሚቆጩላችሁ ብዙ ነበሩ እኮ! ‘ዘመዶች’ ሊበቃቸው ነው!
“እሱንማ ተዪው…ያቺን የእድር ዳኛውን ልጅ ያደረጋት ትዝ አይልሽም…አባቷ እስከ ዛሬ እኮ ቂም እንደያዙ ነው…”
እናማ… እንግዳ ማስተናገድ አስቸጋሪ ነው። የምንጋብዘው እንኳን ‘ሬድ ሌብል’ ምናምን ሊኖረን ‘ሬድ’ መልክ ያላት ቲማቲምም የቅርብ ሩቅ ሆናብናለች፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1666 times