Sunday, 28 May 2017 00:00

ከእኔና ከጥላሁን ማን ይበልጣል?

Written by  ቤተማርያም ተሾመ betishk@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

 (ጥላሁን ግዛውን ማለቴ ነው!)
                            
       ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሳይቸግረኝ እራሤን ከጥላሁን ግዛው ጋር ማነፃፀር ጀምሬአለሁ፤ ለምን? ብዬ እራሴን ስጠይቅም፡- ከኑሮ ውጣ ውረድ ተራ ባተሌነት የዘለለ አንዳች ፋይዳ ያለውና ለታሪክ የሚቀር ተግባር አለመፈፀሜ፣ እድሜዬ እየገፋ ሲሔድ በቀቢፀ ተስፋ ተሞልተው የነበሩ ጀብደኛ ምኞቶቼ ቀስ በቀስ እየተነኑ መሬት መያዝ በመጀመራቸው፤ ይሔው የመብሰሌ ጣጣ የፈጠረብኝ “ሃገሬ ለኔ ምን ሠራች?” ሳይሆን “እኔ ለሀገሬ ምን ሠራሁ?” የሚል የበሠለ ሰው ሃሳብ ባለቤት መሆኔ፤ እና በተለይም እንደ ሙጃ በየጠዋቱ አድገው የሚያድሩት ልጆቼ (ሲያቀብጠኝ ቶሎ ወልጃለሁ) የሠላ አንደበት፤ ተስፋና ህልም ያረገዙ ውብና ትላልቅ አይኖቻቸው ከፍቅራቸውና ሙቀታቸው ጀርባ “አንተስ ምን ሠርተሀል?” እያሉ የሚታዘቡኝ እየመሠለኝ፣ በፍርሃትና ሃፍረት መሠቃየቴ፤ ከብዙ ምክንያቶቼ መሃል ሚዛን የሚደፉት መሆናቸውን ተረዳሁ።
እናም አሁን በቅርቡ “how to stop worrying and live a successful life” የሚል ርዕስ ያለው አንድ መፅሃፍ በ”How to ….” ከሚጀምሩ አያሌ መፅሀፍት መካከል በመምረጥ ስላነበብኩ፤ ፍርሃቴን መፍራት አቁሜ፣ ፍርሃቴን መጋፈጥ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አመንኩ። እናም ገድል አልባና ቀዝቃዛ ህይወቴን የተጠና እና የጠራ መስመር ባለው ትግል በማጀብ፣ እንደ ቀደሙት አቻዎቼ (በተለይም እንደ ጥላሁን ግዛው) ለፈዘዘው ትውልዴ ፋና ወጊ በመሆን ታሪክ ለመስራት ወሠንኩ።
የታሪክ ሰሪነት ታሪካዊ እርምጃዬንም ወሳኝና መሠረታዊ ጥያቄዎቼን ነቅሶ በማውጣትና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት፣ የትግል አቅጣጫዬን መስመር መወሠን ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፤ የአመት እረፍቴን ለቃቅሜ፣የታሪክ ሰሪነት መስራች ጉባኤ ከራሴ ጋር ተቀመጥኩ።
እናም ታሪካዊውን ማኒፌስቶ ያዘጋጀሁበትን ቃለ ጉባኤም በእንደዚህ መልክ ከትቤ ለትውልድ በማቅረብ፣ታሪክ ሰሪነቴን አሃዱ አልኩ (ማን ከማን ያንሳል)። ቃለ ጉባኤው እነሆ፡-
ማኒፌስቶው የሚጀምረው ለትግሌ ጅማሬ የመሰረት ድንጋይ የሆነውን ስር የሰደደ “የምን ሰራሁ?” ፍርሃቴን በመመርመር፣ የጠራና የተጠና አቅጣጫ የያዘ መልስ በመስጠት ነው።

ለምን መፍራት ጀመርኩ ?
እኔም በጥላሁን የእድሜ ክልል ገደማ ነኝ፤ በዚህ ቆቅ ትውልድ መሃል ግን እንደ እርሱ ተለይቼ የነቃሁና የበቃሁ ባለመሆኔ፤ (ሁሉ ነቅቶ በየት በኩል ለብቻ ይነቃል!)
ከራሴና ከጓዳዬ አልፎ ማህበረሰብን የሚሞግት ጠጣር ፍልስፍና ባለቤት ያለመሆኔ፤
ከፕሪሚየር ሊግና ከአሠልቺ የህይወት እሩጫ የተራረፉ ሰአቶቼን ሠባስቤ በእግሬ ጭኖች መሃል ተሸጉጠው፣ በውብ አይኖቻቸው እሚያባብሉኝን የልጆቼን እራስ እያሻሸሁ የማወራው የአባቴን የመሠለ የጅብዱ ታሪክ (የኢህአፓ፣ የቀይ ሽብር፤ የነጭ ሽብርና የእናቸንፋለን አይነት) እጦት ምክንያት፣ ቤቴ አስጠልቶኝ ማፈር መጀመሬ፤
የቀደሙት እኩዮቼ ያልታገሉበት ጉዳይና ያላነሱት የማህበረሰብ ህፀፅ የሌለ እስኪመስል ድረስ ለመታገልና ለማመፅ ሁነኛና ወጥ ርእስ ማጣቴ፤
እንደቀደሙት አቻዎቼ አርአያ (ጀግና)በቀላሉ አለማግኘቴ፤ ተጠቃሽ ምክንያቶቼ  ናቸው።

የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች እና ተግዳሮቶቻቸው
"ሊታገሉዋቸው የሚገቡ የማህበረሰብ ጠንቆች” የሚለውን ሃሳብ ወደ እንግሊዘኛ ተርጉሜ በጉግል የመረጃ አፈላላጊ ድረ-ገፅ ባፈላልገውም ውጤቱ እምብዛም አመርቂ አልሆነልኝም።
እንደ 1960ዎቹ አቻዎቼ አርአያ ፍለጋ በየዌብ ሣይቱ ብንከራተትም አንዳች የረባ ውጤት አጣሁ።
እንደ “እናቸንፋለን” አይነት ጠንካራና የትግል መንፈስን የሚያነሳሳ ብሎም ሃሳቤን በአጭሩ የሚገልጥ “Motto” ብመርጥና ባዘጋጅም እርካታ ላገኝ አላቻልኩም።
ከሁሉም በላይ ተግዳሮት የሆነብኝ ግን እንደ ቀደሙት አቻዎቼ ተጠንቶ የተቀመጠና እንደወረደ ልኮርጀው የምችለው ርእዮተ አለም ከቻይና አልያም ከሩሲያ መቅዳት አለመቻሌ ሲሆን ይህ ችግር ቀስ በቀስ ማኒፌስቶ እንዳይኖረኝ አደረገኝ።
ከተግዳሮቶች ሁሉ በላይ እጅግ የመረሩትና የትግል ጅማሬዬን ጎዳና፣ ወጣ ገባ ያደረጉት ሁለት መራር መሰናክሎች ግን ቀጣዮቹ ናቸው፡-
1ኛ- ከዚህም ከዛም ብዬ ያረቀቅሁትንና በታላቅ ድካም ያሰናዳሁትን “Ideology” ስራዬ ብሎ የሚያደምጥ አንድ ወጣት እንኳን ማጣቴ፤
2ኛ- የትግል አቅጣጫዬን (አካሔድ) የጠራ መስመር ለመምረጥ የተወጠኑ ሁለት አቅጣጫዎች ማለትም፤ “ትግል ከገጠር ወደ ከተማ” እና “የከተማ ውስጥ የማህበረሰብ ድረ-ገጽ ነውጥ” ን በተገቢው ምክንያትና ትንታኔ ተመርቼ፣ ቁርጠኛና ፈጣን አቋም መውሰድ አለመቻሌ ከበድ ያሉት ቢሆኑም በቀጣይ የተገለጡት ተግዳሮቶችም ቀላል የማይባል አሉታዊ ተፅእኖ ነበራቸው።
ትግሌን የሚደግፉ አለም አቀፍ ጓዶች (frends) ከሌሎች ወንድም ሀገራት አለማግኘቴ፤
ትግሌን ለመጠንሰስ የሞራልና የወኔ ብቃት የሰነቁ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መንግስታዊ ድርጅቶች ማጣቴ (የአብዛኛው ተማሪ ጥያቄና የአመጽ ምንጭ ከ”ቅቤ እነሰን” እና ከ”ሽሮው ጎረና” የዘለለ ባለመሆኑ)።
የትግሉን አላማዎች ለማሳወቅ፤ ለማንቃትና የህዋስ አደረጃጀት ለመዘርጋት የመሠብሰቢያ ቦታ ማጣቴ።
እንዲሁም በፌስቡክ ያዘጋጀትሁትን የድርጅቴን ገጽ አልፎ አልፎ ላይክ ከማድረግ የዘለለ comment እና share የሚያደርጉ ጓደኞቼ ቁጥር እጅግ አናሣ መሆኑና ሌሎች ተግዳሮቶች ነበሩ።

እናስ ምን ባደርግ ይበጃል? (የመፍትሔ ሃሳቦች)
ከሠፊውና ከመራሩ ቅድመ ትግል ጥናቴ ያገኘኋቸውን ግብአቶች በመመዝገብና በመተንተን ቀጣይ የትግል አቅጣጫዬን ለመወሰን፣ እኔ እና እራሴ በአንድ ታሪካዊ ካፌ ተቀመጥን። (ለድርጅታዊ አሠራርና ምስጢራዊነት ሲባል የካፌው ስም ተዘልሏል) የመጀመሪያውን ድርጅታዊ ጉባኤ በማካሔድ ከላይ ለተዘረዘሩት የትግል ተግዳሮች የማያዳግም ምላሽ በመስጠትና ቀጣዩን የአቋም መግለጫ በማውጣት፣ ታሪካዊውን ትግል ለመጀመር ቆርጠን፣ ታሪካዊውን ጉባኤ ዘጋን።

የተጠኑ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሃሳቦቻቻው
ለትግል የሚበቁ የማህበረሰብ ህፀፆችን በማፈላለጉ ሒደት እምብዛም ያልረዳንን የgoogle search engine በመገምገም ብቁ ባለመሆኑና ፈረንጅ ተኮር በመሆኑ፣ እንደ ትግል ግብአት መታየቱ ተቋርጦ በሌሎች search engine እንዲተካ፤ ወይም ሌላ የማህበረሰብ የትግል መነሻ ህፀፆች አጥኚ ቋሚ ኮሚቴ ቢቋቋም።
 ለትግል ጅማሬና ሒደት እንደ ምሳሌ የሚታዩ ታጋይ ጓዶች እንደ ቀድሞው ዘመን ቼጉቨራና ሆቼሚኒ ጦረኛና ተዋጊ አመፀኞች ሳይሆኑ፤ እንደ ዙከርበርግ ስቲቭ ጆብስ የመሣሠሉ በቀላሉ ሊኮረጁ የማይችሉ የIT ጂኒሶች፤ አልያም እንደ ቢል ጌትስና ዋረን በፌ የመሳሰሉ በአለባበስ፤ በጠመንጃ አያያዝ፤ አልያም በቶስካኖ (ቶባኮ ሲጃራ) አጎራረስ በቀላሉ ሊኮረጁ የማይችሉ ቢሊየነርስ በመሆናቸው እነርሱን በመተውና ወደ እራስ በመመለስ፣ ድብቅ ተምሳሌቶችንና ጀግኖችን በማሰስ ሀገር በቀል icon መፍጠር ቢቻል።
እንደ ቀደምት ታጋዮቸ የትግል አነሳሽና ወኔ ቀስቃሽ መፈክር “እናቸንፋለን”ን አይነት በዚህ ጉራማይሌ ቋንቋ በዋጠው ማህበረሰብ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ከባድና በተለይም ሁሉም ዜጋ የገዛ ቋንቋውንና ፊደሉን (ፊደል የሌለውም ቢሆን ከውጭ ተበድሮ) ለማሳደግ በሚራወጥበት የፌደራሊዝም ማበብ ማግስት የጋራ መፈክር ለማግኘት መታገል፣ ማህበረሰብን ነፃ ለማውጣት ከመታገል ያላነሰ ጊዜና ጉልበት በመፈለጉ፣ የ”መፈክር ይኑረን” ሃሳብ ቢሠረዝ።
የህቡእ ድርጅቱ አባላት እንደቀደሙት አቻዎቻችን ከመከም ጎፈሬ፣ ቤል ሱሪና ሠፊ ኮሌታ ያለው ደማቅ ሸሚዝ፣ ወቅቱን የተከተለ ባለመሆኑና በተቃራኒውም በከባድ ፍጥነት ከሚለዋወጠው የፋሽን ኢንዱስትሪ እኩል መራመድ የእለት ጉርስን መሸፈን ለተሣነው ወጣት፤ ከትግሉ ይልቅ ሊከብድ በመቻሉ ሃሳቡ በአጠቃላይ ቢሰረዝ።
 የቀደሙት አቻዎቼን ታሪካዊ ስህተት ላለመድገምና ያልተገባ ደም መፋሰስን ላለመከሰት (ብዙ ላብ ደምን ይቆጥባልና) ተሽቀዳድሞና ተቻኩሎ የከተማ ነውጥ አካሔድን ከመከተል ይልቅ ትግል ከገጠር ወደ ከተማ የሚለውን የትግል አካሔድ ብናምንበትም ከወቅቱ አደረጃጀት ማለትም ከአነስተኛና ጥቃቅን አልያም ከ1ለ5 አደረጃጀት ያመለጠ አንድም ወጣት ባለመገኘቱ ልዩ አደረጃጀት አደራጅ ድርጅት ቢደራጅ።
እንደ ቅርቦቹ የሰሜን አፍሪካ ጎረቤቶቻችን የማህበረሰብ ድረ-ገጽ ነውጥን ብንመርጥም እንደ ልብ በከተማችን የማይገኘው የwi-fi መሠረተ ልማት አናሳነት ከስማርት ስልኮች ስርጭት አናሳነት ጋር ተዳምረው ይሔንን የትግል አቅጣጫ እስከ 4G Network ዝርጋታ ለማቆየት በመወሰን፤ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮችን በነውጥ በተዳከሙና ሽብርተኛነትን በሚቀፈቅፉ ጎረቤቶቻችን ድንበር በኩል አስርጎ ማስገባት፣ የጦር መሣሪያን አስርጎ እንደማስገባት አይነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራ። የሚሉ እና መሠል መፍትሔዎችን እንደ ፓርላማችን በሙሉ ድምፅ አሳልፈን ወደ ተግባራዊ እርምጃ ከመግባታችን በፊት ግን እንደ ሳልቫኬር የአንድ ሳምንት የምክክርና ጥሞና ጊዜ አስፈለገን (እኛ እያልኩ እንደ ሃይለ ስላሤ የማወራው ብዙ ሆነን ሳይሆን ከመራሩ ትግል በኋላ እልፍ እንደምንሆን በማመን እንጂ ለጊዜው የጉባኤው አባል እኔ እና እኔ ብቻ ነን)።
ከረጅሙ የጥሞና እና የራስ ምክክር ጊዜዬ ስመለስ፣ ከወቅቱ የአፍሪካዊ እድሜ ጣሪያ አንፃር አብዛኛውን የፈጀውን የእድሜዬን ጉዞ፣በእጅግ ከባድና የማይናቁ ፍሬ ነገሮች መሞላቱን ድንገት አጤንኩ፤ ምናልባትም በፍጥነትና በጥድፊያ ወደ ትግል አለመግባቴ፣ለቀጣዩ አፈንጋጭ ድምዳሜዬ ግብአት ሳይሆን አልቀረም።
ድምዳሜ /የውሳኔ ሃሳብ/
በትግል ጅማሬው አጥቢያ የተነሱ የትግል እክሎቼና መፍትሔዎቻቸው በአጠቃላይ የቀደሙት አቻዎቼ (በተለይም የጥላሁን ግዛው) ዘመን የትግል አቅጣጫዎች እንጂ ዘመናዊ ይዘት የሌላቸው መሆኑን ማጤን ሲገባኝ፣ ዘመናዊ ተግዳሮቶቼን በጥንታዊ የትግል አካሔድ ለመፋለምና እንደ ቀደሙት ሁሉ ከጦርነትና አመፅ ውጪ ሌላ ታሪክ መስሪያ የህይወት አቅጣጫና ፍልስፍና አለማሠቤ፣ በእነ ጥላሁን ተጽዕኖ ውስጥ መኖሬን በመገንዘብ በድንገት ነቃሁ። እናም ቀጣይ ያልተጤኑ የዘመኔ ከባድ ተግዳሮቶችና እውነታዎች እንደ ራዕይ ድንገት ተገለጡልኝ።
በፈጣን የአስተሳሰብ ለውጥ እየቀዘፈ በፍጥነት ከሚነጉድ ባተሌ ትውልድ እኩል ሳይፎርሹ መራመድ።
እንደ መዳፍ በጠበበች አለም እራስን ከትኩስና ወሳኝ መረጃዎች ለቅፅበት ሳይነጥሉ፣ ከአለም ህዝብ ጋር በየሰከንዱ መስተካከል።
በምንም የስነ-ምጣኔ (Economics) ቀመር ያልተደረሰበት የወጪና ገቢ አለመመጣጠን
ሃገራዊ ተግዳሮትን ተቋቁሞ፣ ውብ አይኖች የታደሉ ፈጣን ልጆች የማስተዳደርና ቀጣይ ትውልድ የመቅረጽ እልህ አስጨራሽ ትግል።
ባለ ሁለት አሀዙ የኢኮኖሚ እድገት የፈጠረውን የዜጎች ቅጥ ያጣ የኑሮ ልዩነት ተቋቁሞ፣ እራስን መሃከለኛ ገቢ ካላቸው (ይኑሩ አይኑሩ ባላውቅም) ዜጎች መሃከል ያለማጉደል ጦርነት ።
 በስፋት የተዋቀረው ግዙፍ የሙስና (ጢስ አልባው ኢንዱስትሪ) ሰንሰለት የፈጠረው የሞራልና ግብረገብነት ብቻ ሳይሆን የመሆን አለመሆን ጥያቄ ምላሽ አዙሪት።
ድንገት በፈነዳው የኒዮ ሊበራሊዝምና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍናዎች ፍጭት በተፈጠሩ ጎጦች የተከሠተ ቀዝቃዛ የአለም ጦርነት (እንዲያውም ለብ ያለ ጦርነት ቢባል) እና ተጽዕኖው።
ከወቅታዊው የአለም የበርሜል ነዳጅ ዋጋ ጋር ምንም ግንኙነት ሳይኖረው  እንደተሠቀለ የቀረው የነዳጅ ዋጋና ተያይዞ የሚከሠተው የእንቁላል ዋጋ ጭማሪ፤
 በየጊዜው እየተቃጠሉ ላልተፈለገ ወጪ የሚዳርጉኝ የልጆቼ ተች ፓዶችና ሌሎች የዘመናዊ ኑሮዬ፣ ዘመናዊ አክሎችን ሳያስተውል የተሸከመው ጫንቃዬ ጥዝጣዜ ድንገት ተሰማኝና አነቃኝ! የ “እናቸንፋለን!” “መሬት ላራሹ!” እና “ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም!” አመፆችን ከከሠተ ፍልስፍና እና ንቃተ ህሊና ይልቅ የኔዎቹን ሳንካዎች ለመቋቋም ይበልጥ ምሉእ በኩለሔና ቆራጥ መሆን እንደሚያሻ ተገነዘብኩ።
እንደ መርግ የከበዱ ሸክሞቼን ሳስተውልና ፍግም! ብዬ አለመደፋቴን ሳስብ፣ እኔም እንደ አትላስ ምድርን ከእነ ግሳንግሷ ብቻዬን ተሸክሜ እንደቆምኩ አስተዋልኩ። ማኒፌስቶ በሌለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥም ፊት አውራሪ መሆኔን አመንኩ። ይህን ምድርን እንደ አትላስ ለብቻ ተሸክሞ የደደረ ትከሻዬን ብርታት፤ ከፈጣን ቀዛፊ አለም ቅንጣት ያለመጉደል ብቃት፤ በምንም የኢኮኖሚ ትንታኔ ያልተደረሰበትን የገቢና ወጪ ማቻቻል አስማት ተቋቁሞ፣ የመኖር መራር የትግል ታሪኬን እያወጋሁ፣ የልጆቼን ውብ አይኖች ፊት ለፊት ለማየት በልበ ሙሉነት ወሰንኩ። የታሪክ ሠሪነቴንና የጀግንነቴን ገድል እንዴት ባለ ጎርናና ድምፅ አጅቤ፣ ፀጉራቸውን እያሻሸሁ በኩራት እንደምናገር ሳስብ፣ ቤቴ እራቀኝ፣ የታክሲው ወረፋ ተንዘላዘለብኝ፤ ባቡሩ ቆየብኝ።

Read 1443 times