Sunday, 28 May 2017 00:00

የመሐመድ ኢድሪስ፤ ‹‹ሣልሳዊ ዐይን››

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

     
                      “መሐመድ በእኔ እይታ Plotter ነው፡፡ ወጣኝ ነው፡፡ መጀመሪያ መፃፍ ከመጀመሩ በፊት የታሪኩ የራሱ እጥፋቶች የሚገለፁት ይመስለኛል፡፡ የታሪኩን ውጣ ውረድ በአእምሮው ከወጠነው በኋላ ለተቀየሰው የታሪክ አፈሳሰስ የሚሆኑ ገፀባህሪያትን ከህይወት ተሞክሮ አልበሙ አገላብጦ ይመርጣል፡፡ የተመረጠውን በታሪኩ ቅያስ ወሳኝ ቦታ ላይ ቁጭ ቁጭ ያደርጋቸዋል፡፡ “…
           የመሐመድ ኢድሪስን ድርሰቶች የተዋወቅሁት አዲስ አድማስ ጋዜጣን ሳውቅ ነው፡፡ ወደ አስራ አምስት አመታት ገደማ ማለት ነው፡፡ አንድ ወይ ሁለት ፅሁፍ ከወጣልኝ በኋላ ወደ ጋዜጣው የዝግጅት ክፍል ብቅ ማለት ጀመርኩኝ፡፡ የአጭር ልብወለድ ፀሐፊ የመሆን ህልም ስለነበረኝ በጋዜጣው ላይ ዘወትር በአጭር ልብወለድ አምድ ስር የሚወጡትን ድርሰቶች በተለይ እከታተላለሁኝ። መሐመድ ኢድሪስ ብዙ አጭር ልብወለድ በማምረት ከጊዜው ወደረኞች አንዱ እንደሆነ ሊያስተዋውቁኝ ጠቆሙኝ። መልካም አርዓያ አገኘሁ አልኩኝ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን እኔም ሆንኩ እሱ ለጋዜጣው ማበርከታችንን አላቋረጥንም፡፡ ከአስር አመት በላይ አያሌ የአጭር ልብ ወለድ ድርሰት አበርክተው ግን መፅሐፍ ባለማሳተማቸው ይቆጨኝ ከነበሩ ሶስት ደራሲያን መሀል መሐመድ ኢድሪስ ዋነኛው ነው። የተቀሩት ሁለቱ ዮናስ ነ.ማርያም እና አሸናፊ አሰፋ ናቸው፡፡ አሸናፊ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የአለም አጭር ልብ ወለዶችን ወደ አማርኛ ወደ መተርጎሙ ያተኩራል፡፡
አሁን በአለፈው ወር መሐመድ ‹‹ሣልሳዊ ዐይን›› በሚል የልብወለድ መድበል የአንባቢን ገበያን ተቀላቅሏል። መሐመድ ከእኔ የቁጭት ሰለባነት ነፃ ወጥቷል፡፡ ዮናስና አሸናፊም ተራቸው እንደሚደርስ እተማመናለሁ፡፡
ስለ አጭር ልብ ወለድ በጥቅሉ
ብዙ ጊዜ ስለ አጭር ልብ ወለድ የሚነሳ ውዝግብ አለ፡፡ የትኛው ነው ‹‹አጭር ልብ ወለድ›› ለሚለው ስያሜ የሚመጥን ፅሁፍ? የሚለው ዘወትር አከራካሪ ነው፡፡ በመሆኑም፤ ስለ መሐመድ አጭር ልብ ወለድ ከማውራታችን በፊት የአጭር ልብ ወለድ ትርጉም እንደሚቀድም ስለተሰማኝ ጥቂት ልበል፡፡
‹‹ምንድነው አጭር ልብ ወለድ?” የሚለው ጥያቄ በተነሳ ቁጥር አንዲት ብልጥ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ‹‹አሊቨር ክሮምዌል ምን ምን አከናውኗል?›› ተብላ ስትጠየቅ የመለሰችው መልስ ትዝ ይለኛል። ‹‹አሊቨር ክሮምሜል?!... እሱ ምን ያላከናወነው አለ ብለህ ነው!›› ብላው አሪፍ ማምለጫ ለራሷ አበጀች። አሜሪካኖቹ የአጭር ልብወለድን ዘውግ ፈጥረናል ብለው ስለሚተማመኑ የእነሱን መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩኝ። ‹‹the Greatest American Short stories›› የሚል መጽሐፍ ስለ ኢ-ልብወለድ የጽንስ ሀሳብ ትርጉምና አመጣጥ፣ ታሪኩን ጥሩ አድርጎ ስለሚዘረዝር እሱን ተመረኮዝኩኝ፡፡ ‹‹አጭር ልብ ወለድ ምንድነው?›› ለሚለው ጥያቄ የሚከተለውን ይላል፡- ‹‹እንደ መነሻ አጭር ልብ ወለድ ምን እንደሆነ እቅጩን ከመናገር ይልቅ ምን እና ምን እንዳልሆነ መዘርዘር ይቀላል። አጭር ልብ ወለድ አንድን አጋጣሚ የሚተርክ ወግ (anecdote) አይደለም። አፈ-ታሪክ አውሪ፣ ገድል ዘካሪ፤ የሀገረሰብ ታሪክ (folkatale) ማሸጋገሪያ አይደለም። ወይንም ተአምራዊ ታሪክ፣ ሀይማኖታዊ ምሳሌ (parable)፣ ድንቃይ (fable) አይደለም፡፡ አጭር ልብ ወለድ በእንስሳት ተወክሎ የሚቀርብ አስተማሪ ታሪክ አይደለም። አጭር ልብ ወለድ በዝርው ቢቀመጥም ወግ (essay) አይደለም ወይም ለጉባኤ የሚዘጋጅ የስብከት (sermon) ፅሁፍ አይሆንም። የአንድን አጋጣሚ ምስል በግርድፍ ለመንገር የሚጠቅም (sketch) ወይንም የአንድን ሰው ግለ ታሪክ ወይንም የሀገር ታሪክም አጭር ልብ ወለድን አይገልፅም። እንደ ‹‹አንድ ሺ አንድ ሌሊት›› (Arabian Nights) ተረቶችን መንገርም የአንድ ልብ ወለድ ፈንታ አይደለም።… እዚህ ከላይ የተዘረዘርኳቸው በሙሉ ተረክን የማስተላለፊያ ራሳቸውን የቻሉ መንገዶች ቢሆኑም… አጭር ልብ ወለድን በተለየ መንገድ ቢመስሉም ሙሉ ለሙሉ ናቸው ማለት ግን አይቻልም›› ይላል መፅሐፉ፡፡
አጭር ልብ ወለድ እንደዚህ ሁሉ ካልሆነ ምን የራሱ ማንነት ተረፈው?! ታዲያ ብለን ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል፡፡… ግን መፅሐፉ ይቀጥልና ቁልጭ ያለውን ትርጉም ያስቀምጥልናል፡፡
‹‹አጭር ልብ ወለድ በዝርው የሚቀርብ ነጠላ የፈጠራ ታሪክ ሲሆን፣ በአንድ ቁጭታ ተነብቦ ለማለቅ የሚያስችል ርዝመት ያለው ነው፡፡ አርቲስቱ የተለያዩ ብልሀቶችን በመጠቀም፣ የህይወትን ጥልቅ ገፅታ በጠብታ ውስጥ ወይም ከትንሽ የአጋጣሚ ሰበዝ በመነሳት ማሳየት የሚችልበት ነው፡፡ እነዚህ የአርቲስቱ ጥበባዊ ብልሀቶች፡- (ሀ) ጭብጥ (ለ) ገፀባህሪያት (ሐ) የግጭት እና የሴራ መሰናሰል (መ) መቼት (ሠ) የደራሲው የግል አሻራ (stye) ናቸው። እነዚህን ያሟላ ፅሁፍ አጭር ልብ ወለድ ተብሎ ሊጠራ ይችላል›› ይላል፡፡
እንግዲህ ይሄንን ህግ ይዘን ነው የመሐመድ ኢድሪስን ስራ መጠን ልንለካ የምንመጣው፡፡ በአጭር ልብ ወለድ መለኪያ ስኬታማ ሆነው፣ በውበት ደረጃ ያልተሳኩ ልብ ወለዶች ቢያንስ ‹‹አጭር ወለድ ነኝ›› ብለው በራሳቸው ማንነት መፅናናት ይችላሉ፡፡
ሦስተኛው ዐይን
እንግዲህ ይኼንን መለኪያ ይዘን ስንመጣ፣ ህጉን በደንብ ያሟላ ድርሰት ይዞ መሐመድ መምጣቱ ይገባናል። በ‹‹ሦስተኛው አይን›› መድብል ውስጥ አስር አጫጭር ልብ ወለዶች አሉ፡፡ ሁሉም ልብ ወለዶች በነጠላ ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ፣ የራሳቸው መነሻና መጠናቀቂያ ያላቸው ናቸው፡፡ በጥቅል መፅሐፉን ከተመለከትነው ደግሞ ታሪኮቹ የጭብጥ፤ የገፀባህርይ አሳሳል… እና የመቼት መመሳሰል ይታይባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ነጠላ ልብ ወለድ፤ እንደ ምዕራፍ ይሆንብናል፡፡ ወጥ ልብ ወለድን ያከለም ይመስለናል፡፡ በዚህ ምክንያት በጣም የተለየ ፌቨራይት ከልብ ወለዶቹ መሐል አይሆንም፡፡ ሁሉንም ልብወለዶች አንድ ደራሲ ነው ያሳደጋቸው፡፡ ከልጅ ልጅ መለየት ያቅተናል፡፡… ለነገሩ መሰረታዊውም  ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ በአጭር ልብወለድም እምቅ ቁንፅልነትም ውስጥ ጭብጡ፣ ገፀባህሪያቱ፣ ሴራው ወይንም በአጠቃላይ የትኛውም ግማድ ከሙሉው ጥቅል ጋር ምን ያህል ተዋህዷል? … ነው ጥያቄው” ታሪክን መዋሀድ እና መስተሳሰር (unified narrative) የአጭሩም ሆነ የረጅሙ ልብ ወለድ ዋናው ግብ ነው፡፡ በደንብ የተሳሰረ ከሆነ አንዱን የአጭር ልብ ወለድ ክፍል ከሌላው ነጥለን መውደድ አንችልም፡፡ በአጠቃላይ እንወደዋለን ወይ እናርቀዋለን፡፡
መሐመድ ኢድሪስ እንደ ኦ.ሄንሪ ወይንም ኤደጋር አለን ፖ የሴራ እና የገፀባህርይ መሰረቱ ላይ ጠንካራ ነው፡፡ ሴራ የሚለው ቃል…አሉታዊ ስሜት ቢፈጥርም “plot” የሚለውን ለመግለፅ ማህበረሰባችን የለመደው እሱኑ በመሆኑ ይዘን እንቀጥላለን፡፡ ሴራ ማለት፡- ከእቅድ የሚነሳ ተግባር (motivated action) ነው፡፡
ለምሳሌ ‹‹የእኩለ ሌሊት ወግ›› የሚለው አጭር ልብ ወለድ አርዕስቱን በጣም ወድጀዋለሁኝ። ወግ እንጂ አጭር ልብወለድ አይደለም የሚል ይመስላል። ወጉ ያለው በአጭር ልብወለዱ ውስጥ ነው፡፡ ታሪኩን የሚተርከው ሰው ነው የሚያወጋው። ታሪኩ የኤድጋር አለን ፖን ‹‹six stories of fear›› የሚያስታውስ ነው፡፡ ያላወቀውን እንቆቅልሽ የአእምሯችንን ጓዳ እንደ መጫወቻ ሜዳ ተጠቅሞ፣ ግርታና ፍርሐት አዘል ጥርጣሬን የሚያጎላ የልብ ወለድ አይነት ነው፡፡
ይቅርታ! አሁን ትንሽ እየፃፍኩ ሳስበው ሁለተኛዋን ታሪክ ከሌሎቹ የበለጠ ሳልወዳት እንዳልቀረሁ ማመን ጀመርኩኝ፡፡ ‹‹የጉንዴ ቀለበት›› ትሰኛች፡፡ እቺኛዋን ልብወለድ ደራሲው ከራሱ የህይወት ተሞክሮ በመነሳት እንደፃፋት ይገልፃል። ምናልባት ለዚህ ይሆናል በገፀ ባህሪያት መሀል የሚደረገው ምልልስ እና መቼቱ ከሌሎቹም ታሪኮች በበለጠ ቁልጭ ብሎ ስናነበው በአይናችን ላይ የሚመጣብን፡፡ የምናውቃቸውን ስኬታማ ያልሆኑ ወጣቶች ያስታውሰናል፡፡ በተጨማሪ ከወንዝ እንደተለቀሙ ድንጋዮች የማይቆረቁር የተፍታታ (fresh) የአፃፃፍ ዘይቤው በፍሰቱ ውስጥ ይዞን ጭልጥ ይላል፡፡
ምናልባት የጭብጥ አመራረጥ ላይ አንዱ ደራሲ ብዙ አንባቢ የሚጠራ ሌላው ደራሲ ግን ጥቂት ብቻ ስራውን ለይተው እንዲወዱ ያደርጋቸዋል፡፡ እኔ በበኩሌ በጭብጥ አመራረጥ ብቻ የአንድ ደራሲ አቅም መለካት አደገኛ ነው እላለሁ፡፡ የመሐመድ ጭብጦች የከተማ ነዋሪ ጭብጦች ናቸው፡፡ አንዳንዴ በከተማ ነዋሪ ልብ ውስጥ ገንዘብ ማግኘት ፈጣሪን ከማግኘት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ ሊሆን ይችላል፡፡ መሐመድ የከተማ ልጅ ነው፤ የፃፈውም በከተማ ውስጥ … ከእነሱ …. ከእነ አስተማማኝነት እጦቱ መኖር ምን እንደሚመስል ነው። “አልማዝ” መሸጥ የሚፈልግ ደላላና ገንዘብ ከጣራ ካልዘነበ ራሴን አጠፋለሁ የሚል ወጣት (በመፅሐፉ ውስጥ የሚመላለሱ) ጭብጦች ከነባራዊ የከተማ ህይወት የሚመዘዙ ናቸው፡፡
ምርጥ የሚባሉ የአለማችን የአጭር ልብ ወለድ ፀሐፊዎችም እያንዳንዳችሁ በተለይ የሙጥኝ የምትሉት እንደ አሻራ መለያ የሆናቸውን ጭብጥ ሲያንፀባርቁ ተስተውሏል፡፡ ለምሳሌ፤ ጃክ ለንደን በፅሁፎቹ ሁሉ የዳርዊንን ‹‹Survival of the Fittest›› ሀሊዮት ለማንፀባረቅ ገፀባህሪዎቹን በብዙ ስቃይ ሲጓዙ ማሳየትን ያዘወትር ነበር፡፡ ኦ.ሄንሪም… በልብ ወለድ ጭብጦቹ ሁልጊዜ ለተገፉ (underdog) መወገን ያበዛል፡፡ የሚመርጣቸው ጭብጦች በደራሲና የጥበብ ህይወቱ ዙሪያ ደጋግሞ የሚመራቸው እንደ በአሉ ግርማ የመሰሉ ፀሐፊዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ጭብጥ፤እንደ ደራሲው አኗኗርና ከፍ ሲልም እንደ ደራሲው ምዘና የሚመረጥ ጉዳይ ነው። አርቲስቱ የአጭር ልብ ወለድ ሚዲያውን ተጠቅሞ የመረጠው ጭብጥ እውነት መሆኑን ለመጠራጠር አቅም እስከሚያጥረን ለአለም ያለንን ዓመለካከት  በታሪኩ መነፅር እንድንተረጉም አድርጎናል ወይ? ነው ትልቁ ጥያቄ፡፡ ስለ ጭብጥ ይሄንን ካልኩ፣ አሁን ወደ ‹‹ጉንዴ ቀለበት›› ልሂድ፡፡
ዋነኛው ገፀ ባህርይ የእስኪትዞፍሬኒያ የአዕምሮ ቀውስ ተጠቂ ነው፡፡ አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ ጓደኛው ሊጎበኘው ሲሄድ ነው ልብወለዱ የሚጀምረው፡፡ ሆስፒታሉን ከእነ ህሙማኑ ከመግለፅ ጀምሮ፣ ታማሚው ገፀ ባህርይ ህመሙን የሚያብራራበት መንገድ … ለካ ህመም ራሱ ሊወደድና ሊጠላ የሚችልበት የዕይታ አንፃር አለው እንድንል ያደርገናል፡፡
የሴራ መዋቅር ደራሲው በፈጠራ መልክ የወጠነው ቢሆን እና ባህሪዎቹ ግን በእውን ህይወት ላይ የሚገኙ ከሆኑ ውጤቱ ጥሩ ሊመጣ እንደሚችል ለራሴ መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ሴራውም ገፀ ባህሪያቱም የፈጠራ ከሆኑ ግን ከህይወት እየራቀ ይሄደል፡፡ …. ብዙ ጊዜ ፊልሞች ገና ሲጀምሩ አቅጣጫቻቸውንና ማለቂያቸውን የምገምተው፣ ገፀ ባህሪያቱ ሴራውም ከእውነተኛ ተሞክሮ የተቀዳ ባለመሆኑ ነው፡፡ ህይወት ከደራሲው በፈጠራ ሳትበልጥ አትቀርም። ደራሲው መሐመድ ኢድሪስም ከሚያውቀው ዓለም፣ ከሚኖረው ህይወት የተነሳባቸውን አጭር ልብ ወለዶቹ ክፍሎች ሴራና ልብ ሰቀላውን ተከትለን እንድንሄድ ብቻ ሳይሆን የፈጠራ እውነቱን ፈፅሞ ሳንጠረጥር እንድንሄድ ያስገድዱናል፡፡
በ“ጉንዴ ቀለበት” ላይ ወልዴ የሚባል በአጭር ውልብታ ብቅ ብሎ የሚሰወር ገፀ ባህርይ አለ፡፡ በገንዘብ አብዶ አማኑኤል የገባ ነው፡፡ አንድ ሲጋራ ከተሰጠው ስለ ገንዘብ ትርጉም የገንዘብ ሚኒስቴር ያልገባውን እውቀት በአዕምሮ ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ ይፈላሰፋል፡፡
የልብ ወለድ ታሪኩ ዋና ገፀ ባህርይ መሳይ “ስለ ገንዘብ ንገረን!” ብሎ ያዘዋል፡፡
“ዐሥር ብር ካለህ፤ አንድ የሻይ ቤት ማህበራዊ ትበላለህ፤ ትንሽ ፓስታ፣ ትንሽ መኮሮኒ፣ ትንሽ ጎመን፣ የምስር ወጥና አንድ የተቀቀለ እንቁላል ያለበት፡፡” አለ፤ ሲጋራውን እየማገ፡፡
“ኻያ ብር ካለህስ?” አለ፤ መሳይ፡፡
“ኻያ ብር ካለህ፣ አንድ ማህበራዊ፣ ከአንድ ቡናና ከአራት ሲጋራ ጋር ይኖርኻል፡፡ ሠላሳ ብር ካለህ፤ አንድ ማህበራዊ፣ አንድ ቡና፣ አራት ሲጋራዎች እና እሩብ ጫት ይኖርኻል፡፡ አርባ ብር ካለህ፣ እሩቡ ጫት ግማሽ ጫት ይሆናል፡፡ ሀምሳ ብር ካለህ ጨብሲ ትጨብሳለህ። መቶ ብር ካለህ፣ ምሳህን ጥብስ በልተህ፣ ሙሉ ጫት ከጨብሲ ጋር ይኖርኻል። በቀን መቶ ሀምሳ ብር ካለህ፣ ቁርስህን ዱለት፣ ምሳህን ጥብስ፣ ሁለት ሙሉ ጫት ከጨብሲ ጋር ይኖርሃል። በወር ስድስት ሺ ብር ሲኖርህ፣ ሬዲዮ፣ ሙዚቃና ፊልም ያለው ሞባይል ትገዛለህ፡፡” አለና የሲጋራውን አመድ አራገፈ፡፡
“ከዛስ አታቋርጥ” አለ መሳይ፡፡
“መቶ ሺ ብር ሲኖርህ፤ ሊሊ፣ ኤልሢና ራሄል ስልክህን ያጨናንቁታል፡፡ አምስት መቶ ሺ ብር ሲኖርህ፤ ወሲብ ይሰለችኻል፡፡ አንድ ሚሊዮን ብር ሲኖርህ አንዷን ታገባለህ፡፡ እኔ እዚህ ደረጃ ላይ ነው የደረስኩት” አለና ሲጋራውን ምጎ ወረወረው፡፡
ወደ ላይ ሲወጣ ብቻ ሳይሆን ሲወረድም ምን እንደሚመስል ገፀ ባህሪው ይናገራል፡፡
“ብር በሌለህ ጊዜ፤ ጓደኞችህን ትፈልጣለህ፤ እነሱ ይሰለቹሀል፡፡ ልብስህን ትሸጣለህ፤ እሱም ተሸጦ ያልቃል። የሰው ልብስ እየሰረቅህ መሸጥ ትጀምራለህ፤ እሱም አይቀጥልም፡፡ ከዚያ ደምህን ትሸጣለህ፡፡ ቀይ መስቀል አካባቢ የደም ደላሎች አሉ፤ ገና ስትመጣ በሬው መጣ የሚሉህ፡፡ ደምህን መጥጠው፤ አንድ ሚሪንዳ ይሰጡሀል። ችግሩ እየጠና ሲሄድ፣ ደሙንም መሸጥ አትችልም፤ ምክኒያቱም ደምህ አልቋል፡፡ ከዚያ፣ መሳደብ ትጀምራህ፤ እሱም አይሰራም፡፡ ድንጋይ ስትወረውር፤ ‹አበደ› ይሉና እዚህ ያመጡኻል፡፡” ይላል፤ ወልዴ፡፡
እንግዲህ ይህንን ዓይነት የከተማ ህይወትን ገፅታ ቁልጭ አድርጎ፣ በሁለት ጎኑ ከእነ ሱሰኝነቱ የሚገልፅ እውነተኛ ገፀ ባህርይ አግኝተህ፣ በተጨማሪ ሴራና ልብ የሚሰቅል ከነባራዊው ሀገራዊ ዕውነታ ጋር የሚገጥም ትረካ ካገኘህ ምን ትፈልጋለህ? … በጠብታ ውስጥ ህይወትን ከእነ ግሳንግሷ ማሳየት ማለት ይሄ ካልሆነ እንግዲህ … ትርጉሙን ፍለጋ ወደ ሌላ አማራጭ መሄድ ነው፡፡ ከአጭር ልብ ወለድ ውጭ ያለ ሌላ አማራጭ፡፡
… ግን እንደ ‹ጓንዴ ቀለበት› ሙሉ የሚያሳምን ውጥንና አጨራረስ ያለው ታሪክም በመፅሐፉ ውስጥ አንብቤአለሁኝ፡፡ አንብቤ ንባቤ አልዋጥ ብሎኛል። … “ኑዛዜው” ይሰኛል፡፡ አባት የወጧት ልጁ አባካኝነት ከመሞቱ አስቀድሞ ታውቆት ጣራው ውስጥ ያስቀመጠለት የውርስ ገንዘብ መጨረሻ ላይ እንደታቀደው ልጁ ራሱን ሊሰቅል ሲል ይዘረገፍለታል፡፡ …. ይኼ እንኳን ህፃን ልጅን በከረሜላ እንደ ማታለል ነው። የበሰለ የልብ ወለድ አንባቢ በዚህ የታሪኩ አስተላለቅ አይረካም። አለመርካት ብቻ ሳይሆን “አይንህን ጨፍንና ላሞኝህ” የተባለም ሊመስለው ይችላል፡፡ … በሴራ ላይ ብቻ የተመሰረተ ጭብጡ ያልጠነከረ፣ ገፀ ባህርይውን አጎልቶ የማያወጣ የአጭር ልብ ወለድ ትረካ የፈጠረውን ልፋት፣ ጨቅላ ሊያደርገው እንደሚችል አስቀድሞ መገመትና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሌላው፤ በኔ እምነት ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ልብ ወለዶች ዘመን ተሻጋሪ የመሆን አቅማቸው ደካማ ነው። ምክኒያቱም ቴክኖሎጂ እንደ ሰው መሰረታዊ ባህርይ ያለበት የሚቀመጥ አይደለም።  ከዚህ በተረፈ የእኔ አይኖች “ሣልሳዊ ዓይን” በሚለው የመፅሐፉ አውራ ልብ ወለድ የበለጠ አይኔም ብቻ ሳይሆን ቀልቤም በሌሎቹ (ዘጠኙ) ላይ ማረፉን ባልመሰክር እውነተኛ አልሆንም፡፡
የሣልሳዊው አይን ደራሲ ወደፊት ምን ሲሆን ይታየኛል?
መሐመድ በእኔ እይታ Plotter ነው፡፡ ወጣኝ ነው፡፡ መጀመሪያ መፃፍ ከጀመሩ በፊት የታሪኩ የራሱ እጥፋቶች የሚገለፁት ይመስለኛል፡፡ የታሪኩን ውጣ ውረድ በአእምሮው ከወጠነው በኋላ ለተቀየሰው የታሪክ አፈሳሰስ የሚሆኑ ገፀባህሪያትን ከህይወት ተሞክሮ አልበሙ አገላብጦ ይመርጣል። የተመረጠውን በታሪኩ ቅያስ ወሳኝ ቦታ ላይ ቁጭ ቁጭ ያደርጋቸዋል፡፡ … እንዲህ ይመስለኛል የመሐመድ ኢድሪስና እሱን መሰል ደራሲዎች የተፈጥሮ ችሎታቸውና የፈጠራ ሂደታቸው፡፡
ይህ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ለሁሉም የጥበብ ዘርፍ ያስፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ እዚህ ጋር ተዋናይ አለ … ልንል እንችላለን፡፡ ተዋናዩ የግዴታ የሚያስፈልገው ቅድመ ነገር አለ፡፡ … እርግጥ ነው መድረክ፣ ዳይሬክተር … ግን መድረክም ሆነ ዳይሬክተር ሆነ ተዋናዩ የሚመጡት የሚጫወቱት ታሪክ ሲኖር ነው። ዳንሰርም ቢባል ሙዚቃ ያስፈልገዋል፡፡ ሙዚቃም ፀሐፊ ያስፈልገዋል፡፡ መሐመድ በቃላት የሚሰራውን ሙዚቀኛው በኖታ ይሰራዋል፡፡
በአጭሩ ለማለት የፈለኩት፤ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም የሚሞክር ትውልድ … ትያትርን ማበልፀግ የሚፈልግ ትውልድ … ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን በሀገራዊ ጭብጥ ለመስራት የሚፈልግ ትውልድ … የመሐመድ አይነት ፕሎተሮች ያስፈልጉታል፡፡ ወግ እና ገድል ከሚተርኩት በላይ አዲስ ገድል ያውም በምናብ በተፈጠረ ታሪክ በኩል አድርገው የሚናገሩት የበለጠ ለጥበብ ተስፋ ናቸው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ የጥበብ ተስፋ ስል እኔ ጥበብ የምትደርስበትን ጫፍ እንደማውቅ ሆኜ እንዳልሆነ ግልፅ እንዲሆን እፈልጋለሁኝ፡፡ … ጥበብ አስቀድሞ የተዘረጋለት መዳረሻ አላት እያልኩኝ አይደለም። ተስፋና እድገት ስል በህይወት መቆየት ማለቴ ነው፡፡ አጭር ልብ ወለድ በመሐመድ ኢድሪስ ስራ በህልውና መኖሩን አረጋግጧል፡፡  

Read 5158 times