Saturday, 27 May 2017 13:34

የራፕ አልበሙን ለመመረቂያ ያቀረበው የሃርቫርድ ተማሪ በማዕረግ ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በዩኒቨርሲቲው የ81 አመታት ታሪክ በዚህ መልኩ የተመረቀ የመጀመሪያው ተማሪ ነው
     በታዋቂው ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተመራቂ የሆነውና ለመመረቂያ ጽሁፍ የራፕ ሙዚቃ አልበም ሰርቶ ያቀረበው የሃያ አመቱ ወጣት ኦባሲ ሻው፣ በትምህርት ክፍሉ ተቀባይነት በማግኘት በማዕረግ መመረቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የ81 አመታት ታሪክ የሙዚቃ አልበምን በመመረቂያ ጽሁፍነት አቅርቦ በማዕረግ በመመረቅ የመጀመሪያው ተማሪ የሆነው ኦባሲ ሻው፣ በራፕ ስልት የተቀነቀኑ 11 ሙዚቃዎቹን ያካተተበትንና “ሊሚናል ማይንድስ” የሚል ስያሜ የሰጠውን አልበሙን ለመመረቂያ ጽሁፍነት እንዲያቀርብ ሃሳብ የሰጡት እናቱ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡
ወጣቱ የራፕ የሙዚቃ አልበም በመመረቂያ ጽሁፍነት የማቅረብ ሃሳቡ በዩኒቨርሲቲው ተቀባይነት ያገኛል ብሎ በፍጹም ባይገምትም፣ የእናቱን ሃሳብ ተከትሎ የመመረቂያ ፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን ለትምህርት ክፍሉ ሃላፊዎች ሲያቀርብ ያገኘው በጎ ምላሽ ግን በሃሳቡ እንዲገፋበት እንዳበረታታው ይናገራል፡፡
“ኤ” ውጤት ያስገኘለትንና በማዕረግ ያስመረቀውን ይህንን የራፕ ሙዚቃ አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ አመት ያህል እንደወሰደበት የጠቆመው ዘገባው፣ ወጣቱ በአልበሙ ባካተታቸው ሙዚቃዎቹ የጥቁሮችን ህይወት፣ የቀለም ልዩነትንና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን መዳሰሱንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1013 times