Sunday, 28 May 2017 00:00

አላነሳም እጄን ከቀሚሷ

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(12 votes)

ሰሞኑን የቴዲን ዘፈን መስማት ለእኔ አልተመቸኝም። ሳላስበው ይለውጠኛል፣ ያናውጠኛል፣ ያንገዳግደኛል….ብቻ ምን አለፋችሁ … የማላውቀው ማንነቴ ያሸንፈኛል። ይሰውረን ነው መቼም፤ ከማያውቁት የራስ ማንነት ጋር መጋፈጥ እጅግ ከባድ ነው፡፡‹በሰማዩ ላይ ቢታይ ቀለም፣ የሷ ነው እንጅ ሌላ አይደለም› ይህ የእኔ የእብደት ምንጭ ነው፡፡
‹የፍጥረት በር ነሽ፣
የክብ ዓለም ምዕራፍ፣
ዞሮ መጀመሪያ›
የዓለም ቅርጽ ክብ መሆኑን ካወቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን በመረጃ የሚፎካከር የለም፡፡ ምነው ቢሉ ፊደላቸው ምስክር ነውና፡፡ ዓለም ብለው በዐይኑ ‹ዐ› ይጽፋሉ እንጅ በአልፋው ‹አ› አይጽፉም፡፡ ቴዲም በዘፈኑ ላይ የክቡ ዓለም ምዕራፍ መጀመሪያ ይላታል - ዓለም ሲጀመር አንስቶ መኖሯንና የዓለም ምዕራፍ ማሳረጊያ መሆኗንም እየመሰከረልን፡፡ ካልተሳሳትኩ ገድለ አዳም ብለን የአዳምን ገድል የጻፍን፥ አሊያም የጠበቅን፣ ያስቀመጥን እኛው ብቸኞቹ ነን። ፍካሬ ኢየሱስን፣ ራዕየ ዮሐንስን፣ ከእነትንታኔያቸው እየተረጎምን የምናስተምርና የዓለም ፍጻሜ ምዕራፍን በአቡሻህር እያሰላን የምንጠባበቅ ጉደኞቹ እኛው ነን፡፡
‹ስንት የሞቱልሽ ለክብርሽ ዘብ አድረው፣
አልፎ ሲነኩሽ ባሕርሽን ተሻግረው›
ለኢትዮጵያ ያልሞተ ማን አለ? ኮንሶ፣ወላይታ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሃድያ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ፣ አገው፣ ሃማሴን፣ ብሌን፣ ሱርማ፣ ወይስ ቦዲ አሊያስ ቅማንት….. ለኢትዮጵያ ያልሞተ ማን አለ? የኢትዮጵያ ድንበር ሲነካ ያልሞተ ማን አለ፡፡ ‹ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ›። በእውነት እንደው ስለ እውነት ኢትዮጵያ ሲባል ዝም ያለ ማን ነው?
ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ዛሬ እኛ የደረስንባትን ቅርጽ ይዛለች፤ ይህ ደግሞ በምንም ተዓምር የመጨረሻዋ አይሆንም፡፡ ምነው ቢሉ ታሪኳን ለሚያውቅ ሁሉ ግልጥ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ‹አላነሳም እጄን ከቀሚሷ› የሚለን ቴዲ፡፡ ቀሚስ የክብር፣ የልዕልና ምልክት ነው፡፡ ካህናት፣ እናቶች፣ ሴቶች፣ እንዲሁም መነኮሳት….ቀሚስ የሚለብሱት ክብራቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ ባለ ቀሚሷ ኢትዮጵያ ክብር ናት፡፡ ጨቅላው ቴዲ፤ ቀሚሷን ይዞ እያለቀሰ ነው፡፡
‹የመጪው ዘመን ፊት ናት መሪ፣
ዛሬ ዓለም ቢላት ኋላ ቀሪ›
ዓለም ሲፈጠር የነበረች፣ በማዕከላዊ ዓለም ክርስቶስ ተወልዶ ሲሰቀል ምስክር የነበረች፣ በፍጻሜ ዓለም የምትኖር ሃገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ዛሬ ዓለም ቢላትም ኋላ ቀሪ እርሷግን የተለየች ብጹዕ ናት፡፡ የነቃች የበቃች። የማንም የምዕራብ ፍልስፍና የማያስፈልጋት ‹ምልዑ በኩለዬ›፡፡ ማጥናት፣ መማር ካለብን እኛኑ እራሳችንን እናጥና፣ እንመርምር፡፡ አሊያ የፈረንጅ መጣጥፍና የመንገደኞች ማስታወሻ ከድቡሽት እያነሱ ኢትዮጵያ ማለት እንዲህ ነበረች ቢሉ ከተረት ተረትም እጅግ የራቀ ይሆናል፡፡ ዓለም የማያውቃት እኛ ጨቅሎቹ የምንጫወትባት፣ የዓለም ምስጢራት መክፈቻ ቁልፍ ናት ኢትዮጵያ፡፡
‹የሰማይ መቀነት ቀስተ ደመና›
ቴዲያችን ምንድ ነው የሚለን፡፡ ሰማይ ሰማይ ነው፤ መቀነትም መቀነት፡፡ ሴቶች እንደ ዋዛ ሸብ የሚያደርጉት መቀነት እንዴት ነው ሰማይ የሚታጠቀው? ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ እግዜርና ሰው ተጣሉ፤ ሰው ልክ እንደ ዛሬ ዘመን ሁሉ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ነብይ አይሰማም፤ ያስራል፣ ይገላል፣ ይገርፋል፣ ያሰቃያል…. ታዲያ እግዜር ምን ቸገረው፡፡ ንፍረ ውሃ ለቀቀበት፡፡ ከዓለም ህዝብ ውስጥ ኖህና ቤተሰቦቹ ተረፉ፡፡ ኖህ ተማረረና ከዓምላኩ ጋር ግብ ግብ ገጠመ፤ ልጆቼን ከዚህ በኋላ አልድርም፤ አላዋልድም እነርሱ ከስተት ላይመለሱ አንተም ከመቅጣት ላትታቀብ አለ፡፡ እግዜራችን ተጸፀተ፤ ለኖህ ቃል ገባለት፤ ከእንግዲህ በኋላ ዓለምን አላጠፋም፤ ለዚህም ምልክት እንዲሆንህ ቀስቴን በደመና አስቀምጣለሁ አለው፡፡
‹የተራሮች አናት ዘብ የቆሙልሽ›
ዛሬ ኢትዮጵያ በኛ በጨቅሎቹ እጅ ወደቀችና መሳለቂያ ሆነች እንጅ፤ የተራሮች አናት ዘብ የቆሙላት ሃገር ነበረች፡፡ ኖህ ከሰራው መርከብ ሲወጣ፤ የንፍር ወሃ ጎድሎ የተራሮች አናት ላይ መርከቡ ተጠግታ ነበር። የኖህ መርከብ የመጨረሻ መዳረሻዋ የኛዋ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ኖህ ቁራን፣ እርግብን እየላከ፣ የውሃውን መቀነስ ይከታተል የነበረው በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ሆኖ ነበር። የውሃውን መጉደል ካረጋገጠ በኋላም ከመርከቡ ውጥቶ የመጀመሪያውን መስዋዕት ያቀረበው በኢትዮጵያ ድንበር ነበር፡፡ ቴዲያችን እንደ ዋዛ የተራሮች አናት ዘብ የቆሙልሽ  ይለናል፡፡ ይሄው ነው እንግዲህ እንዲህም ያስባለው፡- ‹በሰማይ ላይ ቢታይ ቀለም፣ የሷነው እንጅ ሌላ አይደለም› ሰማያችን ቀለሙ እንዳማርኛችን ሰማያዊ ነው ቀለም የለውም። በሰማዩ ላይ የሚታይ ቀለም ካለ አንድም የደመናወ ነጭ፣ አሊያም የቀስተ ደመናው ሕብር ነው፡፡ የቀስተ ደመናው ሕብር ደግሞ ያው የኛው  ባንዲራ ነው፡፡ ማረር የሚፈልግ ማረር ይችላል፤ ሰማያዊው ሃቅ ግን ይሄው ነው፡፡
‹ቢጎል እንጀራ ከሞሰቡ ላይ፣
እናት በሌላ ይቀየራል ወይ›
እናቱ ናትና የቀሚሷን ጫፍ ይዞ ጡል ጡል እያለ ይከተላታል እንጅ፤ ዛሬ ሞሰቧ ባዶ ነው ልተዋት አላለም፡፡ የተወለድንባት፣ ያደግንባት፣ የተማርንባት፣ የጎለመስንባትን ኢትዮጵያ በክፉ ቀኗ ልንሸሻት አይገባንም። የቁርጥ ቀን ልጅ ቴዲ፤ ‹ሃገር የማዳን ስራ መስራት አለብን› ይላል፤ በቃለ ምልልሱ ላይ። ‹የጀግኖች ሃገር፣ ያዳም እግር አሻራ›ም ይላታል፤ ውዲቷ ኢትዮጵያውን፡፡ አባቶች በጀግንነት ከጠላት ጋር እየተዋደቁ ያቆዩዋት ሃገር ናትና፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድ ወጥ ቅርጽና ድንበር አልነበራትም፡፡ እንደ ጀግኖቿ ጥንካሬ፣ ከዘመን ዘመን የተለያየ ቅርጽ ነበራት፡፡ ቀይ ባሕርን ተሻግረው የኢትዮጵያን ድንበር እስከ ደቡባዊ አረቢያ ያደረጉበት ዘመን ነበረ፡፡ ወደ ሰሜን ገስግሰው እስከ ታህታይ ምስር ፈርኦኖችን ያስገበሩበት ወቅትም ነበራቸው፡፡ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያም የምናያትን መስላለች፡፡ ‹ቢጎል እንጀራ ከሞሰቡ ላይ፣ እናት በሌላ ይቀየራል ወይ›
‹የሰሎሞን ዕጽ ነሽ፣ የቅዱሳን እንባ ያበቀለሽ ቅጠል›
ጠቢቡ ሶሎሞን ያልተራቀቀበት፣ ያልተጠበበበት ሙያ አልነበረውምና፤ ከጠቢባን ሁሉ ሰሎሞንን መርጦታል ቴዲ፡፡ ንግስተ ሳባ የጥበቡን ልክ ከፈተነችበት እንቆቅልሽ ውስጥ ሰው ሰራሽ ውብ አበባ አሰርታ በአንድ እጇ፤ በሌላ እጇ ደግሞ ትክክለኛ የተፈጥሮ አበባ ይዛ፤ ከሁለቱ የተፈጥሮ የሆነው የትኛው እንደሆነ እንዲነግራት ነበር የጠየቀችው። የዕፅ ጥበብ አይሰወርበትምና ትክክለኛውን ለይቶታል፡፡ ኢትዮጵያ ከሃያላን መንግስታት ጋር ግጭት ውስጥ እየገባች በድል ተወጥታዋለች፡፡ በእራሷ አቅምና የመሣሪያ ብልጫ ኖሯት ሳይሆን የቅዱሳን እንባ ላይ የበቀለች ለምለምና ነበልባል ቅጠል ስለሆነችም ነው፡፡ ‹የቅዱሳን እንባ ያበቀለሽ ቅጠል› ይላታል ቴዲ፡፡
‹ተውኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ፣
ኢትዮጵያ ማለት ለኔ አይደለም ወይ ክብሬ›
የክብሩ መገለጫ፣ መመኪያው፣ የማንነቱ መዋቢያው ናትና ኢትዮጵያ ‹ተውኝ ይውጣልኝ› ይለናል፡፡ በፎቶዎቹ፣ በፖስተሮች፣ በኮንሰርቶቹ በባንዲራዋ ቀለም ደምቆ ነው የሚቀርብ ቴዲያችን፡፡ የተዋለለትን ያባቶቹን ውለታ ሳይረሳ፣ ብድር መላሽ ለመሆን በሙያው ይታትራል፣ ስሟን ደጋግሞ ይጠራል፡፡
‹አንተ የከንፈር ወዳጅ በጊዜ ሳመኝ፣
 ጤፍ አበጥራለሁ የሰው ግዙ ነኝ፤
የሰው ግዙ ሆኖ የሰው ግዙ መውደድ፣
እሳት በገለባ እፍፍ ብሎ ማንደድ› ትል ነበር፤ ጂጂ ሌላዋ አቀንቃኛችን፡፡ ቴዲም የተቸረው ሙያ ማቀንቀን ነውና ለእመቤት ኢትዮጵያ ግዞተኛ ሆኖ ያቀነቅናል፡፡
‹ይዤ አላነሳም እጄን ከቀሚሷ፣
እናት እኮ ናት ተስፋ አልቆርጥም በሷ› የኢትዮጵያችን ቀሚስ እንደ ዘመኑ በረከትና ክፋት ሲያጥር ሲረዝም ኖሯል፡፡ ቀሚሷ ዘርፋፋ ሆኖ ሞገሷ ሲጨምር አለሁልሽ የሚለው ይበዛል፡፡ ቀሚሷ ተቀዳዶ ሲያጥር ያጥፋሽ ይበትንሽ የሚላት ይበዛል። ቴዲያችን ግን እናት እኮ ናት እንዴት በእናት ተስፋ መቁረጥ ይቻለኛል ይላል፡፡
ያጠረ ቀሚሷን ጨምድዶ ይዞ፣ እንደ ብሶተኛ ሕፃን እያለቃቀሰ ይከተላታል፡፡ መቻያውን ይስጠው እንጅ፤ የግዮን ፈለግን ተከትሎ እንዴት በእሱ አቅም ይወጣዋል። የሰው ዘር ሁሉ አባት የሆነው አዳም የተመላለሰባትን ምድር ማን ይመረምራታል? ከአምላኩ ጋር የተያየባትን መንደር ማን ያውቃታል? የአዳምን፣ የሙሴን፣ የመልከ ፀዴቅን፣ የኖኅን፣ የክርስቶስን፣ የእመቤታችንን…እግር አሻራ በታሪኳ አጭቃ የያዘች የእኛው ጉደኛዋ ሃገር ኢትዮጵያችን ናት፡፡ ግዮን አንደበት ቢሰጠው ለዚህ ሁሉ ምስክር ነው፡፡
‹የጀግኖች ሃገር ያዳም እግር አሻራ፣
ፈለገ ግዮን ያንቺ ስም ሲጠራ›

Read 4114 times