Sunday, 28 May 2017 00:00

ዜድቲኢ በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሊሰማራ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  በአለማቀፍ ደረጃ በቴሌኮም ኩባንያነቱ የሚታወቀው ዜድቲኢ፤ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለመሰማራት እቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡
የኩባንያው የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስራ አመራሮች በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ዘርፍ ቢሰማሩ ሊተገብሯቸው ያቀዷቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስራ አመራሮች አስተዋውቀዋል፡፡
ኩባንያው በተለይ ለመብራት በየጊዜው መቆራረጥ እንደምክንያት የሚቀርበውን የኤሌክትሪክ መስመሮች እርጅናን እንዴት በቀላሉ ማደስ እንደሚቻልና የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀሚያ ታሪፍን በተመለከተ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ማዘመን እንደሚቻል አስታውቋል፡፡ በዚህ መስክም በኢትዮጵያ መንግስት ፍቃድ ካገኘ ለመሰማራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
በተለይ በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታና በንኡስ ኃይል ማስፋፊያ ጣቢያዎች ግንባታ ላይ በኢትዮጵያ መሳተፍ እንደሚፈልግና ይህን ለመከወንም በቂ አቅም እንዳለው ጠቁሟል-ኩባንያው፡፡
በገጠር አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚቻል የጠቆሙት የኩባንያው ኃላፊዎች፤ ይህን መሰሉን ፕሮጀክት ከ160 በላይ የዓለም ሀገራት ላይ እየተገበረው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Read 1476 times