Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 10:15

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ምነው አልፈራ ልጄ?” የተገረሙ የሚመስሉ አዛውንቱ ቀስ ብለው ጀመሩና ጎላ ባለ ድምፅ ቀጠሉ፡፡ “በስልጣኔ ሰማየ ሰማያት በደረሰች፣ በሀብት በናጠጠች አገር ላይ ሆኜ እጄን ለምፅዋት ስዘረጋ ምነው አልፈራ ልጄ? ድህነትን ሳይሆን ድሀን ለማጥፋት ታጥቀው በተነሱ ደግ መሪዎች መዳፍ ውስጥ ሆኜ ምነው አልፈራ? እነሱ በመጥገባቸው፣ ሁሉ የጠገበ በሚመስላቸው የነፃነት ሃዋርያት መሀል ሆኜ ምነው አልፈራ ልጄ?”

መላ ሰውነታቸውን በስሜት አከው ሲያበቁ “ፍርሃት ብቻ አይደለም የሚሠማኝ” አሉት “አፍራለሁም! ኤርትራዊም ሆኜ ለማኝ ስሆን አፍራለሁ፤ አንድ ሰው ኤርትራዊ ሆኖ በኤርትራ ምድር እየኖረ እንዴት “ራበኝ” ብሎ ይለምናል? ለሚሠማው ግራ ነው፤ እንቆቅልሽ ነው፤ እንደዚህ አይነቱ ኤርትራዊ አገሩን ከማሰደብ፣ ወገኖቹን ከማሳፈር  ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ቀድሞውኑ ባይፈጠር ይሻለዋል፡፡ ምክንያቱም ኤርትራ የበለፀገች፣ የምድር ላይ ገነት ስለሆነች አንድን ቁራጭ ደሀ ማየት አትሻምና፡፡

እናም ለማኝ የተባለ ሁሉ ወንጀለኛ ስለሆነ ከከርሰ ምድር ገፅ ማጥፋት ይኖርበታል፡፡ መሪዎቻችን እንዲህ ቁም ስቅላችንን ቢያሳዩን ቢያሳድዱን፣ ከዕብዶች ጋር አንድ ላይ ቢያጉሩን … ጥፋታቸው ምኑ ላይ ነው? እብድና ደሀ አንድ ነው! ድሀ ምን ክብር አለው? እኔ በእውነቱ መሪዎቻችን አልተሳሳቱም ነው የምለው” ዞር ብለው አዩት፤ ሳሙኤል በሚሠማው ህመም ሳቢያ እየተዳከመ ነው “ታዲያ ልጄ! ኤርትራዊ መሆን አያኮራም ትላለህ? የትም ብትሄድ እግርህ ይቀጥናታል እንጂ እንደ ኤርትራ ያለች ለማኝ ዞር የማይልባት ሀገር በፍፁም አታገኝም! ያቺ ጉረኛ አሜሪካም “በአለም አንደኛ ነኝ” ብላ በባዶ ሜዳ  ብትኮፈስም እሷም በአቅሟ ለማኝ ዜጐች አሏት፡፡

አንዳንዴ ሳስበው ኤርትራ አገሬን ከማሰደብ ምነው አሜሪካዊ ሆኜ በተፈጠርኩ እላለሁ፡፡ በነፃነት እየዞሩ መለመን ቅንጦት አይደል?”

ክፉኛ የሚፈልጠውን ራሱን በሁለት እጆቹ ግጥም አድርጐ ያዘና በርትኡ አንደበታቸው ስለተደነቀ “ትምህርት ተምረዋል እንዴ አባቴ?” ብሎ ጠየቃቸው “ምነው ልጄ፤ እንደኔ አበድክ? ኤርትራዊ ምን ትምህርት ያስፈልገዋል? አንተ ኤርትራዊ ከሆንክ ገና ስትፈጠር ጀምሮ ምሁር ነህ፤ ዶ/ር ነህ፤ ፕሮፌሰር ነህ፤ ሊቅ!” በተሰበረ ድምፀት ቀጠሉ “ኤርትራዊ ሊያስብለኝ የሚችል የቀረኝ ምልክት ቢኖር ሳልማር ምሁር መምሰሌ ብቻ ነው፤ ግና ምን ዋጋ አለው? ድሀ ነኝና ኤርትራዊ አይደለሁም”

(“የነፃነት ባሮች” ከሚለው የደራሲ አቤል ሠይፈ መፅሃፍ፣ በአበባዬ አሰፋ የተቀነጨበ (ገፅ 73-74) 1992)

 

 

Read 5361 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:21