Sunday, 28 May 2017 00:00

በማይንማር በየቀኑ 150 ህጻናት እንደሚሞቱ ተመድ አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የእርስ በእርስ ግጭት እየተስፋፋ በመጣባት ማይንማር በየቀኑ እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ 150 ያህል ህጻናት ለህልፈተ ህይወት በመዳረግ ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ በመጣው የእርስ በእርስ ግጭት፣ በድህነት እና በበሽታ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ያለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ በተለይም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎት በመቋረጡ በርካታ ህጻናት በኒሞኒያና በሌሎች በሽታዎች እየተሰቃዩ፣ ምንም አይነት የህክምና እርዳታ ሳያገኙ ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረጉም አስታውቋል፡፡
በመላ አገሪቱ 2.2 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆመው ድርጅቱ፣ የአገሪቱ መንግስት እየተስፋፋ የመጣው ብጥብጥና የእርስ በእርስ ግጭት ሰለባ ለሆኑት ለእነዚሁ ህጻናት አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ማድረግና በህጻናቱ ላይ የሚፈጸሙ የመብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል፡፡
ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ህጻናት ከድህነት ወለል በታች የሆነ አስከፊ ኑሮ እንደሚመሩ የጠቆመው ዘገባው፣ 30 በመቶ ያህሉ የማይንማር ህጻናት የከፋ የምግብ እጥረት ተጠቂ እንደሆኑም አመልክቷል፡፡

Read 1277 times