Saturday, 27 May 2017 14:01

የትዳር መፍረስና የሚያስከትለው ውጤት...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  ጋብቻ በመፍረሱ ምክንያት የሚያስከትለው የጤና፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር ምን መልክ አለው? በሚል ለዚህ እትም ለንባብ ያልነው ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑትን አቶ አበበ አሳመረ የገለጹትንና የአንዲት እናትን ታማኝነት ነው። አቶ አበበ የባልና ሚስት አለመግባባትና የፍቺ ምክንያቶች የሚል መጽሐፍም በ2007 አሳትመዋል። አቶ አበበ በዚህ እትም የፍቺ አስከፊ ውጤቶች የሚባሉትን ይገልጹልናል። አስቀድማችሁ የምታነቡት ግን የአንዲትን እናት እማኝ ነት ነው። ባለታሪኩዋ ቀደም ሲል በመቀሌ ከተማ ይኖሩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በአዲስ አበባ ይኖራሉ።
“...እኔ በእድሜዬ ወደ ሀምሳ አምስት አመት ይሆነኛል። የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ነበርኩ። የዘሬ አምስት አመት ማለትም ሀምሳ አመት ሲሆነኝ ነበር ከባለቤዮጋር የተለያየነው። ታሪኩ ብዙ ቢሆንም ቀንጨብ ላድርግላችሁ። የቅዳሜ ሹር እለት አንድ በግ ነጋዴ በግ አድርስ ተብዬ ነው ብሎ ትልቅ ሙክት በግ አምጥቶ ከግቢዬ ያስራል። እኔም ባለቤዮ ዛሬ እንዴት አሰበና ይህን የሚያህል በግ ገዛ ብዬ ሳስብ አንድ የአስራ አንድ አመት ልጅ እየሮጠ መጣ። ምንድነው ልጄ? ስለው ...አ.አ.ይ እማማ ሰውየው ተሳስቶ ነው በጉን እዚህ ያመጣው አለ። የማንነው በጉ? ብለው በጉማ አባዬ የገዛው ለእኛ ነው አለ። ጥሩ ነው ልጄ ...በል ፍታና ውሰድ...ግን አባትህ ማንነው? የማን ልጅ ነህ? ስለው የእኔን ባለቤት ስም ጠራ። እናትህስ ማንነች? ስለው ነገረኝ። ቤታቸውንም አመላከተኝ እና በጉን እየጎተተ ሄደ። እኔም በጣም አዝኜ ...እቤት ያሉት ልጆች ምን ሊበሉ ነው? ደግሞስ እንዴት ሌላ ልጅ ሲወልድ ሳልሰማ? ብዬ ከእራሴ ጋር ተሟገትኩ። አ.አ.ይ አይሆንም። ይህንንማ ማጣራት አለብኝ ብዬ ለራሴ አሰብኩ። ወደምሽቱ ገደማ አንዲት እዚህ ግቢ የማትባል ትንሽ ፍየል ወደእኔ ቤት እየተጎተተች መጣች። ያመጣውም ያንን ሙክት ያመጣው ነጋዴ እራሱ ነበር። ...ይቅርታ እማማ። ጠዋት ያመጣሁት በግ ለካ በስህተት ነበር። ባለቤትዎ ሲገዙ ልጁ አብሮ ስለነበር መሳሳዮን አውቆ እየሮጠ መጥቶ ወሰደ። እኔ ግን የእርስዎ ባለቤት ሰለሆኑ የገዙት መቼም ለቤታቸው ነው ብዬ ነበር። ለካስ ተልከው ኖሮአል። ይህኛው ግን ለቤታቸው መሆኑን ነግረውኛል... አለ። በጣም ጥሩ እግዚሐር ይስጥልኝ ብዬ ሰውየውን ከሸኘሁ በሁዋላ ያቺን የታሰረች ፍየል እየጎተትኩ ልጁ ከነገረኝ ቤት ሄድኩ። እዛ ስደርስ ቡና ተፈልቶ የእኔም ባለቤት ከአንዲት ማረፊያ ላይ ጋደም ብሎ ይሳሳቃሉ። ቤቶች አልኩና በድንገት ዘው ብዬ ስገባ ሁሉም ደነገጡ። ሴትየዋም ለእኔ አዲስ አልነበረችም። በየገበያው እንገናኛለን። ከዚያ ከተላከው ልጅ በተጨማሪ ሁለት ልጆች አሉ። ምነው ምን ሆንሽ? ለምን መጣሽ? አለ ባለቤዮ....አ.አ.ይ ይ ፍየል የባለቤትህ ናት ብዬ ማምጣዮ ነው። ሙክቱ ለመጀመሪያ ሚስትህ ይቺ ደረቅ ፍየልህ ደግሞ ለሁለተኛዋ ሚስትህ ቢሆን አይሻልም? ከመጀመሪያው ቤትህ ያሉት ልጆችህ ትልልቅ ናቸው ...ይቺ አትበቃም... ብዬ ነዋ...አንተም ቤት አለኝ ብለህ ከእንግዲህ ወደእኛ እንዳትመጣ ...አልኩና ፍየልዋን አስሬላቸው ሙክቱን ከታሰረበት ፍትት አድርጌ ወደቤቮ እየጎተትኩ ሄድኩ። በቃ። በህግ ተፋታን። ከዚያ በሁዋላ ግን ልጄም ትዳርዋ እንደዚሁ ጥሩ አልሆን ብሎ ፍቺ ገጠማት። እኔ ግን የራሴ ትዳር ሲፈርስ ምንም ያልመሰለኝ ሲሆን የእስዋ ሲፈርስ ግን እርር ድብን ነበር ያልኩት። ምክንያቱም ከዘር ነው... እናትዋስ ማን ናትና ነው? የሚል ቅጽል ይሰ ጠኛል ...እንዲሁም በእኔ የደረሰ ችግር በእሱዋም ይደርሳል ብዬ እጅግ ታገልኩ። ለሶስት አመታት ያህል ኑሮዬን ትቼ የእሱዋን ኑሮ ለመጠገን ታግዬ ነገር ግን የሁዋላ ሁዋላ ተሳካልኝ። ዛሬ ጥሩ ኑሮ ትኖራለች። ባለቤትዋም እጅግ ይንከባከበኛል። የልጆች እናትና አባትም ሆነዋል። ዋናው የታገልኩበት ምክንያትም ከስሙም ባሻገር ትዳሬ ከፈረሰ በሁዋላ በአካባቢው፣ በቤተሰቡ፣ በኑሮው ሁሉ ምን ያህል እንደተሰቃየሁና ምነው በቀረብኝ እያልኩ ስለነበር ይሄ ለልጄም እንዳይተርፋት ብዬ ነው። ትዳር ጥሩ ነው። መፍረስ የለበትም። “
ከላይ የትዳር ታሪካቸውን የገለጹት እናት ስማቸው እንዳይገለጽ ነግረውናል። የገጠማቸው ታሪክ ግን በአይነቱ ቢለያይም የብዙዎች እናቶች ገጠመኝ ይሆናል ብለን እናስባለን። አቶ አበበ አሳመረ የህግ ባለሙያ እንደሚገልጹት ፍቺ የተለያዩ መሰረታዊ ውጤቶች አሉት። የፍቺ ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
የሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ አንዱ ለትዳር መፍረስ መንገድ ከፋች ነው ተብሎ ይታሰባል። ምክንያቱም ሴትዋ ትዳር ከፈረሰ በሁዋላ በምን እኖራለሁ? የሚለውን ጭንቀት ገንዘብ ስለአላት ማስተናገድ አትፈልግም። ስለዚህም በጥገኝነት ሳይሆን መኖር የምትፈልገው በትዳር ውስጥ ፍቅር ሲኖር ብቻ ይሆናል።
ትዳር ለዘለአለም ይቆያል የሚለው ብሂል በሰዎች ዘንድ የተለመደ እና የሚታሰብ ሆኖ የቆየ ስለነበረ የተፋቱ ሰዎችን ማግለል የተለመደ ነበር። ነገር ግን ይህ ብሒል በመቅረቱ የተፋቱ ሰዎችን ማግለሉም አብሮ የቀረ በመሆኑ ሰዎች የፍቺን ጉዳት እንዳያዩ አድርጎ አቸዋል።
አማካኝ የኑሮ እድሜ መጨመር...ከጊዜ ወደጊዜ የጤና ችግሮችን አስቀድሞ መፍታት በመለመዱ አማካኝ የኑሮ እድሜን በተለያዩ የአለም አገራት እንዲጨምር አድርጎታል። ስለሆነም ወንዶቹ ከፊትለፊታቸው እረጅም እድሜ እንዳለ ስለሚያስቡ እና ያ እረጅም እድሜ ደግሞ መውለድ ወይም እንደገና ትዳር መያዝ ላይ ምንም ተጽእኖ እንደማያስ ከትል ስለሚረዱ አንደኛውን የትዳር አጋር ትቶ ወደሌላው የትዳር አጋር የመሄድ ነገር ይስተዋላል።
ሌላው ስለትዳሩ የጋራ ስሜት ማጣት ነው። ባለትዳሮች እንደተጋቡ ቤት የማጠናከር ልጆች ወልዶ የማሳደግ የመሳሰለው የጋራ ስሜታቸው ኑሮ በገፋ እና በተለይም ልጆች አድገው ከእጃቸው ሲወጡ የጋራ አላማቸውን ማጣት ስለሚኖር አንዳቸው ለአንዳቸው ወይንም ለትዳሩ ያላቸው ስሜት ይቀዘቅዛል። ስለዚህም ፍቺ ይከተላል።
የትዳር መፍረስ ቀላል አይደለም የሚባልበት ምክንያት ከፍቺ በሁዋላ ያለው ውጤት በጣም ውስብ ስብ መሆኑን በርካታ ጥናቶች ስለሚያረጋግጡ ነው አቶ አበበ እንደገለጹት። በሀገራችን ባይለመድም በውጭው አለም አንድ ቤተሰብ በፍቺ ትዳሩን ካፈረሰ በሁዋላ ለረጅም አመታት ጥናት አድራጊዎች ባልና ሚስት የነበሩትን ሰዎች ሕይወት ይከታተላሉ። በዚህም አኑዋኑዋራ ቸውን፣ ስነልቡናቸውን፣ የጤ ንነታቸ ውን ሁኔታ፣ ከልጆቻቸው ጋር ያለቸውን ግንኙነት፣ አስቀድመው ይኖሩበት ከነበረው ማህበረሰብና አሁን እየኖሩበት ካለው ማህበረሰብ፣ በመስሪያ ቤታቸው፣ በቤተሰባቸው የነበራቸውንና አሁን ያላቸውን ግንኙነት የመሳሰሉትን ሁሉ ለረጅም ጊዜ ጥናት አጥኚዎች ይከታተሉዋቸዋል። በዚህም መሰረት ውጤቱ የተረጋገጠባቸው ጥናቶች በርካታ ናቸው።
የትዳር መፍረስ በሴቶችም ይሁን በወንዶች ላይ የጤና ችግር ያስከትላል።
በሴቶች ጤና ላይ፡-
ሴቶች ትዳራቸው ሲፈርስ ስር የሰደደ የብቸኝነት ስሜት ያድርባቸዋል። ይህ ብቸኝነት ደግሞ ጭንቀትን ማስከተሉ አይቀርም። ጭንቀት ደግሞ በራሱ ለሌሎች የጤና ችግሮች እንደሚያጋ ልጥ እሙን ነው። ብስጭት፣ ግራ መጋባት፣ ከልጆች ጋር መጋጨት፣ከሰዎች ጋር ሰላማዊ የነበረውን ግንኙነት ማሻከር፣ በትንሽ ነገር መቆጣት፣ ማኩረፍ፣ ማልቀስ፣ እራስን እንደእድ ለቢስ መቁጠር የመሳሰሉት ስሜቶች ይስተዋሉባቸዋል። ይህ ደግሞ ለእንቅልፍ ማጣት፣ ለአእ ምሮ መታወክ፣ ለደም ግፊት፣ ለስኩዋር፣ ለልብ፣ ለመሳሰሉት ሕመ ሞች ሊያጋልጥ እንደሚ ችል በጥናት ተረጋግጦአል። ይህ በጥናት ብቻም ሳይሆን በአገራችንም ወደተለያዩ ማለትም ወደሕክምናውም ይሁን ወደሕግ አማካሪው ሲቀርቡ የሚሰጡት መረጃ መሆኑ እሙን ነው።
በወንዶች ጤና ላይ ፡-
ወንዶች በፍቺ ምክንያት የሚደርስባቸው የጤና ችግር እንደሴቶቹም ባይሆን ቀላል የሚባል አይደለም። በተለይም የፍቺ ምክንያቱ ወንድየው ከሆነ በከፍተኛ ሁኔታ የመጸጸት ችግር ይደር ስባቸዋል። በራስ የመተማመን ስሜትንም ያጣሉ። መጀመሪያ ምንም ባይመስላቸውም እየዋለ ሲያ ድር ግን የጥፋተኝነት ስሜት ያድርባቸዋል። ከዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ቀድሞ ወዳልነበ ራቸው ባህርይ ይገባሉ። ለምሳሌም ...ጫት መቃም፣ መጠጥ መጠጣት፣ ሴሰኝነት፣ ሲጋራ ማጤስ፣ የመሳሰሉትን ለጤና ጠንቅ ወደሆኑ ነገሮች የሚመሩዋቸውን ነገሮች ይጀምራሉ። ወንዶች በተለይም ወደመጠጥ ሱስ ከገቡ የሴት አስተናጋጆች በሌሉበት ቦታ መጠጣት ስለማይወዱ ያንን ተከትሎ እንደ ኤችአይቪ፣ በግብረስጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች፣ ለተለያዩ የውስጥ ደዌ በሽታዎች ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች አረጋግጠዋል።
የብቸኝነት ስሜት ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ይጠነክራል። ምክንያቱም በገሀዱ አለም እንደ ሚታየው ወንድየው ትዳሩ ሲፈርስ በፍጥነት ትዳር መመስረት እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች የሚያገኛቸውን ጉዋደኞች ማፈላለግ ከሰዎች ጋር በውጭ ምናልባትም ከመዝናኛ ቦታዎች አምሽቶ መግባት የመሳሰሉት ነገሮችን ስለሚጠቀሙ ብቸኝነቱ ብዙም ወንዶችን አይጎዳም። ሴቶች ግን ትዳራቸው ከፈረሰ በሁዋላ ትዳር መመስረትም አይፈልጉም። እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ሴቶቹ እንደወንዶቹ ከውጭ ማምሸት ወይንም መዝናናት ስለማያደርጉ በብቸኝነት በጣም ይጎዳሉ። ይሄ የአኑዋኑዋር ዘይቤ በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ተመሳሳይ ባይሆ ንም እንኩዋን በሌሎችም አገራት መኖሩን ጥናቶች ያስረዳሉ እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ።

Read 2585 times