Print this page
Sunday, 28 May 2017 00:00

የመጽሐፍ ሂስ ጉባዔ እና ዓውደ-ርዕይ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 “ሀሳብን በሃሳብ መፈተን” የሚል መሪ ቃል ያነገበው ወርሃዊው የመጽሐፍ ሂስ ጉባዔ እና ዓውደ-ርዕይ፤ በመጪው ቅዳሜና እሁድ ከጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ፊትለፊት በሚገኘው ትራኮን ህንጻ ላይ ይካሄዳል፡፡
አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ እንዳሉት፣ በታዋቂው የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በተጻፈውና “ሀብቴ አባ መላ - ከጦር ምርኮኛነት እስከ አገር መሪነት” በተሰኘው የታሪክ መጽሃፍ ላይ በመጪው ቅዳሜ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆነው ብርሃኑ ደቦጭ፤ በመጽሐፉ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የመጽሐፍ ሂስ ጉባዔ እና ዓውደ-ርዕይ ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቤተ-መጽሃፍት ማደራጃና መገልገያ የሚሆኑ መጽሐፍት የሚሰባሰቡበት የልገሳ ፕሮግራም የሚጀመር ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ለቀጣዮቹ ሶስት ተከታታይ ወራት እንደሚቀጥልም ተነግሯል፡፡
በሊትማን ቡክስ፣ ክብሩ መጽሐፍ እና እነሆ መጻሕፍት የጋራ ትብብር በሚዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም ላይ፤ የመጽሐፍ ዕቁብን ጨምሮ እስከ 50 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የሚደረግበት የመጽሐፍተ ዐውደ-ርዕይን ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶችም የሚካተቱ ሲሆን፣ አንባቢያንና የቡና ስፖርት ክለብን ቤተ-መጽሐፍት ለመደገፍ የሚፈልጉ ሁሉ በነጻ እንዲታደሙና ልገሳ እንዲያደርጉ አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Read 1845 times