Sunday, 04 June 2017 00:00

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩና ዳንኤል ሺበሺ ክስ ተመሰረተባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

     ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ የድርጅቱ ጉዳይ ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ፣ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር በመገናኘትና የተከለከለ ሚዲያን መልዕክት በማስተላለፍ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን በማስረጃነትም በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የተገኙ ፎቶግራፎችና ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡
በእያንዳንዳቸው ላይ ሁለት ሁለት ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን ፖለቲከኛ ዳንኤል ሺበሺ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ይዞት በነበረው ተንቀሳቃሽ ስልኩ ውስጥ “ተማምሏል ጎንደር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ፣ አርማ በሌለው ባንዲራ የተቀነባበረ ቪዲዮና ሌሎች ቪዲዮዎችን፣ የተለያዩ የሽብርተኛ ድርጅቶችን የሚገልፁ ምስሎችንና ፅሁፎችን ይዞ በመገኘት፣ በፈፀመው ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ወንጀል የመጀመርያ ክስ እንደተመሰረተበት ተጠቁሟል፡፡  
ተከሳሹ በተንቀሳቃሽ ስልኩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መከታተል የተከለከለውን የኢሳት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ቪዲዮና ተከሳሹ ለቴሌቪዥን ጣቢያው በስልክ የሰጠውን መግለጫ ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመው የሽብርተኛ ድርጅቶችን ሚዲያ መከታተልና ሪፖርት ማድረግ ወንጀል ተከሷል - ይላል - በአቶ ዳንኤል ላይ የቀረበው ሁለተኛ ክስ፡፡
በጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ላይ የቀረበው የመጀመሪያ ክስ ደግሞ ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግን አስመልክቶ የተጣለውን ክልከላ በመተላለፍ ይዞት በነበረው ተንቀሳቃሽ ስልክ ውስጥ በሽብርተኛነት የተፈረጀውን የግንቦት 7 አመራሮች ምስልና አርማ እንዲሁም የተለያዩ የሽብርተኛ ድርጅቶችን ሃሳብ የሚገልፁ ፅሁፎችንና ምስሎችን ይዞ በመገኘት በፈፀመው ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ወንጀል መከሰሱን ያመላክታል፡፡
ተከሳሹ ይዞት በነበረው ተንቀሳቃሽ ስልክ ውስጥ በህዝቦች መካከል መጠራጠርና ጥላቻን የሚፈጥሩ ንግግሮችን፣ ፅሁፎችንና ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጭቶ፣ ቀሪ ኮፒዎችን ይዞ በመገኘት፣መቻቻልንና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር የመፈፀም ወንጀል መከሰሱን በጋዜጠኛው ላይ የቀረበው 2ኛ ክስ ያስረዳል፡፡
አቃቤ ህግ አንድ የሰው ማስረጃና ከተንቀሳቃሽ ስልክ የተገኙ ምስሎችና ድምፅ እንዲሁም ጽሁፎች በሰነድ ማስረጃነት አቅርቧል፡፡ ህዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ተከሳሾቹ፤ከ7 ወር በኋላ የተመሰረተባቸው ክስ፣ ረቡዕ ግንቦት 23 በፍ/ቤት በንባብ ተሰምቷል፡፡ ተከሳሾቹ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ በፍ/ቤቱ ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን የተከሳሾች ጠበቃ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የአቃቤ ህግን ምላሽ ለመስማት፣ለግንቦት 28 ቀን 2009 ተቀጥሯል፡፡ በተከሳሾች ላይ የቀረቡ ምስክሮች በዝግ ችሎት ይታዩልኝ ብሎ አቃቤ ህግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ ምስክሮች በዝግ ችሎት እንዲሰሙ ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡


Read 874 times