Sunday, 04 June 2017 00:00

ሰመጉ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይፋ አደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት መስከረም መጨረሻ አንስቶ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመሩን ያስታወቀው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፤ 19 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውንና ከ22 ሺህ በላይ ለእስር መዳረጋቸውን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ተቋሙ ባወጣው ሪፖርቱ፤ ”አዋጁ ከታወጀ በኋላ በርካታ ሰዎች ከህግ አግባብ ውጪ ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ለእስር ተዳርገዋል፣ የደረሱበት የማይታወቅም በርካታ ናቸው” ብሏል፡፡
ከበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመብት ጥሰት ጥቆማዎች ቀርበውለት እንደነበር የጠቆመው ሠመጉ፤ አቅሙ ፈቅዶ ማጣራት የቻለው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልል እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ 18 ዞኖች እና 42 ወረዳዎች መሆኑን አስታውቋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአይነትም ሆነ በመጠን ከተገለፁትም በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስታወቀው መግለጫው፤ የአስገድዶ መድፈር፣ የንብረት ዘረፋ፣ የጅምላ እስራት እንዲሁም የዜጎች መፈናቀል ጥቆማዎችም እንደቀረቡለትና በቀጣይ ጉዳዮቹን እንደሚያጣራ ተቋሙ አመልክቷል፡፡
መንግስት በየአካባቢዎቹ ቀደም ሲል የወሰደው አላስፈላጊ የኃይል እርምጃ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ፍርሃት መፍጠሩን እንደተገነዘበ የጠቆመው ሠመጉ፤ በዚህም ምክንያት ምርመራና ማጣራት በሚያደርግበት ወቅት ከህብረተሰቡ በቂ መረጃ ለማግኘት መቸገሩን አመልክቷል፡፡  
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ከ18 ዓመት ወጣት እስከ 64 ዓመት አዛውንት ድረስ በፀጥታ ኃይሎች በጥይት መገደላቸውን በፎቶግራፍ አስደግፎ በስም ዝርዝር የጠቆመው የተቋሙ መግለጫ፤ አብዛኞቹ በመንገድ ላይ ሲሄዱና በመኖሪያ ቤታቸው እያሉ መገደላቸውን  አስታውቋል፡፡ በአርሲ ዞን ሸርካ ወረዳ፣ ከአንድ ቤት 3 ወንድማማቾች በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ፣ በአንድ ላይ መገደላቸውን የሚጠቁመው መግለጫው፤አቶ ምክሩ ቸኮል የተባሉ የ64 ዓመት አዛውንትም በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ጭስ አባይ ቀበሌ፣ “ሠላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳትፈሃል” በሚል በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአርሲ ሶስት ልጆቻቸው ሲገደሉ የተመለከቱ እናት መታመማቸውን፣ ወንድሞቿ ሲገደሉ የተመለከተች እህትም ለአዕምሮ መታወክ ህመም መዳረጓን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡  
በአጠቃላይ በኦሮሚያ 15 ሰዎች መገደላቸውን፤ ከእነዚህ አስራ አንዱ የወለጋ፣ አራቱ የአርሲ ነዋሪዎች እንደነበሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በኮንሶ ቀደም ሲል ከተነሳው የኮንሶ “የዞን እንሁን” ጥያቄ ጋር በተገናኘ የፖሊስ ባልደረባውን ዋና ሳጅን ገመዳ ሮባን ጨምሮ 3 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
አዋጁ በታወጀ በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ 22 ሺህ 507 ሰዎች መታሰራቸውንና አብዛኞቹ ክስ ሳይመሰረትባቸው ከህግ አግባብ ውጭ ለእንግልት መዳረጋቸውን የሚጠቁመው ሠመጉ፤ ከእነዚህ ውስጥ 102 የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮችና አባላት፣ 15 የሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም 11 የመኢአድ አመራርና አባላት መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ “የታሰሩ የኦፌኮ አመራር አባላት ከዚህም ይልቃሉ፤ ያገኘሁት ከፊሎቹን ነው” ብሏል - ተቋሙ በሪፖርቱ፡፡
በተጨማሪም ከመምህራን የደሞዝ ጥያቄ ጋር በተገናኘ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም 30 ሰዎች፤ “መንግስት ለሰራተኞች ያደረገው የደመወዝ እርከን ማስተካከያ መምህራንን ያላካተተ ነው በሚል የስራ ማቆም አድማ ላይ ተዋናይ ሆናችኋል” በሚል ታስረው መፈታታቸውንና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲም ህዳር 29 የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች በአል፣ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ይከበር አይከበር በሚል አለመግባባት ፈጥረዋል የተባሉ 15 ተማሪዎች ታስረው ከ4 ወር በኋላ እንደተለቀቁ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ተቋሙ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ፈቃድ አግኝቶ፤ የደብረ ታቦርና የፍኖተ ሰላም ማረሚያ ቤቶችን በመጎብኘት የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት፤ በአንድ ክፍል ማለትም 10 በ 4 በሆነ ክፍል ውስጥ ከ80 እስከ 100 የሚደርሱ እስረኞች ተጨናንቀው እንደሚኖሩና እጅግ ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመኖሩ እስረኞች በሳምንት 1 ቀን ብቻ ውስን ውሃ እንደሚያገኙ፣ በዚህ የተነሳም የንፅህና ችግር እንዳለ መታዘቡንም ገልጧል፡፡ በዚሁ ማረሚያ ቤት በኮማንድ ፖስቱ የቃል ትዕዛዝ ብቻ ክስ ሳይቀርብባቸው ታስረው የሚገኙ ዜጎች እንዳሉ ተመልክቻለሁ ብሏል - ሠመጉ፡፡
በፍኖተ ሰላም ማረሚያ ቤት ምንም ክስ ያልተመሰረተባቸው ከ250 በላይ ወጣቶች እንደሚገኙና እስረኞች ሽንት ውስጥ ጭምር እየተዘፈዘፉ እንደሚሰቃዩ ታሳሪዎች ነግረውኛል የሚለው ተቋሙ፤ ድብደባ እንደሚፈፀምባቸውም ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ሰመጉ በተለያዩ እስር ቤቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ 28 ምስክሮችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን ጠቅሶ፣ ባጠናቀረው ሪፖርቱ፤ በእስረኞች ላይ የማቁሰል፣ ድብደባና የማሰቃየት ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል ብሏል፡፡ እስከ 114 የሚደርሱ እስረኞችም በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው እንዲኖሩ መደረጋቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡  ተቋሙ በሪፖርቱ ማጠቃለያ፤ ህዝቡ ጥያቄዎቹን ለመንግስት የሚያቀርብበት መድረክ ማጣቱ፣ መንግስትም በማናቸውም መንገዶች የቀረቡለትን ጥያቄዎች ለማስተናገድ አለመቻሉና የኃይል እርምጃን በመፍትሄነት መምረጡ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ቀውስ አስከትሏል ብሏል፡፡
ህገ ወጥ ግድያና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎችና ቤተሰቦች ተገቢው ካሳ እንዲከፈል፤ የህግ ጥሰት የፈፀሙና ያስፈፀሙ የመንግስት አካላት በህግ እንዲጠየቁ ያሳሰበው ሰመጉ፤ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም በተባበሩት መንግስታትና በሌሎች አለማቀፍ ተቋማት እንዲጣራ ጠይቋል፡፡





Read 1492 times