Sunday, 04 June 2017 00:00

ዓለም፣ “በአካባቢ ጥበቃ”፣ ወደ ጨለማ ከመግባቷ በፊት... የአሜሪካ ውለታ እንደገና በዶናልድ ትራምፕ ይደገም ይሆን?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

 • በ“አካባቢ ጥበቃ” ሰበብ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቢሊዮን ብር የድሃ አገር ሃብት እያባከነ ነው። በዚህ ብክነት
የተሳተፉ ባለስልጣናት፣ በሕግ የሚጠየቁበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም! ፈጠነም ዘገየም ይመጣል።
• ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት፣... አንዳንዶቹ በትርምስ እየፈራረሱ ነው። አንዳንዶቹም ገደል አፋፍ ደርሰዋል። የሕዝብ ብዛትና የተመራቂ ወጣቶች ቁጥር ጨምሯል፤ የስራ እድል ግን የለም !

     የነገዋ አፍሪካ፣ ብሩህ አይደለችም። የአፍሪካ የኢንዱስትሪና የፋብሪካ ምርት፣ ገና ብቅ ከማለቱ፣ ተመልሶ እየተደፈቀ ነው።
ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር፣ በኢንዱስትሪ ደህና የገሰገሰ ሌላ አገር፣ በአፍሪካ የለም። በእርግጥ፣ ትንሽ ለመራመድ የሞከሩ ግን አሉ። በተለይ የያኔው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገንን በመሳሰሉ ሰዎች ጥረት፣ የዛሬ 25 ዓመት ገደማ፣ ሶሻሊዝም ተንኮታኩቶ፣ የግል ኢንቨስትመንት መነቃቃት የጀመረ ጊዜ፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ፣ የለውጥ ብርሃን ሲፈነጥቅ ታይቷል። የፋብሪካ ምርት እየጨመረ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ እየጨመረ ነበር።
ከዛሬ 35 ዓመታት በፊት፣ በኢኮኖሚያቸው ውስጥ፣ የፋብሪካ ምርት ድርሻ ወደ 15% ለማድረስ የቻሉ የአፍሪካ አገራት ስንት ነበሩ ብለን መጠየቅ እንችላለን። ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር፣ ሌላ አገር አልነበረም።።
ከ1980 ዓ.ም እስከ 1995 ድረስ ባሉት ዓመታት ግን፣ በአፍሪካ ምድር የለውጥ ብርሃን ፈነጠቀ። የፋብሪካ ምርት ደህና እየጨመረ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከ15% በላይም መሆን ጀመረ። በስንት አገራት? በ15 አገራት!
በዚህን የለውጥ ነፋስ የተነሳም፤ “የአፍሪካ አገራት፣ እንደ ኤስያ አገራት፣ ወደ ብልፅግና መራመድ ይችሉ ይሆናል” የሚል ተስፋ ተፈጥሮ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው? በዚያው አልቀጠለም።
በአጭር የተቀጨ የአፍሪካ ፋብሪካ!
ፋብሪካዎችን እያስፋፉ በእድገት መራመድ የጀመሩት በርካታ የአፍሪካ አገራት፣ ከ1995 ዓ.ም ወዲህ፣ ቁልቁል ወርደዋል። ዛሬ፣ ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ውስጥ፣ 15% ያህሉን የሚሸፍን የፋብሪካ ምርት በምድረ አፍሪካ ብርቅ ሆኗል። ሁሉም አገሮች፣ ወደ ድሮው የኋላቀርነት ድንዛዜ ተመልሰዋል። ሦስት አገራት ብቻ ናቸው የቀሩት - ሞሮኮ፣ ሞሪሼስ፣ ግብፅ። ግን፣ የእነዚህም ቢሆን፣ እየወረደ ነው።
20% ደርሶ የነበረው የግብፅ የፋብሪካ ምርት፣ ዛሬ ወደ 16% ወርዷል።
የሞሪሼስ ደግሞ ከ24% ወደ 16% ቀንሷል።
በአጭሩ፤ ባለፉት 15 ዓመታት፣ የፋብሪካ ምርት ድርሻ በአፍሪካ አሽቆልቁሏል - ገና ማደግ ሳይጀምር እየተቀጨ። በኢኮኖሚ አቅማቸው ደህና ናቸው የሚባሉ 20 መሪ አገራትን መመልከት ይቻላል።  
   የሕዝብ ብዛት እየበረከተ፣ ከዚህም ጋር የተማረና ከኮሌጅ የተመረቀ ወጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ ነው። በፍጥነት የሚጨምረውን የተመራቂ ወጣቶች ቁጥር ማስተናገድ የሚችል፣ ሌላ ተአምር የለም። በኢኮኖሚ ውስጥ የፋብሪካ ድርሻ በፍጥነት መስፋፋት ነበረበት።
ቀደም ሲል፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት በፈርቀዳጅነት የበለፀጉት፣ ባለፉት አርባ ዓመታትም፣ እነ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን የመሳሰሉ የምስራቅ ኤስያ አገራት በፍጥነት ወደብልፅግና የተቀላቀሉት፣ ከዚያም እነ ቻይናን ወደ ብልፅግና መራመድ የጀመሩት፣ በተመሳሳይ መንገድ ነው። የሁሉም አገራት እድገት፣ ከፋብሪካ እድገት ጋር የተሳሰረ ነው። የፋብሪካ ምርት ድርሻ እያደገ ካልመጣ፣ የሚያዛልቅ እድገት አይኖርም፤ ውሎ አድሮም አገሬው ይፍረከረካል። ለምን?
የፋብሪካ ምርት ካልገዘፈ፣ የእርሻ ምርትም ይብረከረካል። ያለከተማ ገበያ፣ የእርሻ ምርት ተስፋ አይኖረውም። የእርሻ ስራ፣ ብዙ ትርፍ ምርት ቢያስገኝ እንኳ ገበያ አጥቶ ይከስራል። ከዚያም ድርቅ ይመጣና ይደቁሰዋል። የእርሻ ስራ እንዲህ፣ ኪሳራና ድርቅ እየተፈራረቁበት፣ ሦስት አራት አመት ከተጎሳቆለ በኋላ፣ ለሺ ዓመታት እንደታየው፣ ቁልቁል ወደ ረሃብ ይወርዳል። የእርሻ ከዚህ የሚድነው፣ የፋብሪካ ምርት ሲስፋፋ ነው። የሌሎቹ መስኮች እጣ ፈንታም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል።
የፋብሪካ ምርት ከሌለ፣... ትምህርት “ከ100% በላይ” ቢትረፈረፍ ዋጋ የለውም - ፍሬ ቢስ ልፋት ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። ትምህርት ለምርታማነት ካልዋለ፣ ፋይዳው ምንድነው? ምንም!
የፋብሪካ ምርት ከሌለ፣ የመንገድ ግንባታ እንኳ፣ ከንቱ ድካም ከመሆን አይድንም። መንገድ ተገንብቶ ምን ሊጓጓዝበት? ...ምናለፋችሁ! ያለ ፋብሪካ ምርት ኑሮን ማሻሻልም ሆነ መበልፀግ አይቻልም። ምን ይሄ ብቻ! ያለ ፋብሪካ ምርት፣ ለዘለቄጣው ከድህነትና ከረሃብ ማምለጥ አይቻልም።
በቃ! የፋብሪካ ምርት የህልውና ጉዳይ ነው።
ለዚህም ነው፤ ዓለማችንን ያጥለቀለቃት “የአካባቢ ጥበቃ” አስተሳሰብና ዘመቻ፣ ምን ያህል አደገኛና አጥፊ መሆኑን ለመገንዘብ ከባድ የማይሆነው።
“አረንጓዴ ልማት” በሚል ስያሜ የሚካሄደው “የአካባቢ ጥበቃ” ዘመቻ፤ የፋብሪካ ምርትን የሚያኮላሽና የሚንድ፣ የዘመናችን ዋነኛ የብልፅግና ጠላት ነው። ፋብሪካን በጠላትነት ፈርጆ ከመዝመትም አልፎ፤ የፋብሪካ የሃይልም ምንጮችን እያደረቀና እየበጣጠሰ፤ ፋብሪካዎችን ኦና እና ጨለማ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ፣ በብዙ አገራት እንደተደረገው፣ በአነስተኛ ወጪ ብዙ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ግድቦች ከተገነቡ፤ ክፉኛ ይቃወማሉ። ብድር ያስከለክላሉ፤ ግንባታ ያጓትታሉ። የጊቤ 3 ግድብ፣ ለአስር ዓመታት የተጓተተውና ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ የደረሰበት፣ በዚህ አይነት የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። በከፍተኛ ወጪ፣ አነሰተኛና አስተማማኝ ያልሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል ለሚያመነጩ ፕሮጀክቶች ብዙ ገንዘብ እንዲባክን ያደርጋሉ። እስካሁን፣ ለነፋስ ተርባይኖች ከፈሰሰው ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ውስጥ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በከንቱ የባከነ ነው - ለዚያውም የድሃ አገር ገንዘብ።
የእንፋሎት ሃይል ማመንጫ እንገነባለን ተብሎም፣ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ በከንቱ ባክኗል - ቅንጣት የኤሌክትሪክ ብልጭታ ሳያመነጭ።
የድሃ አገር ሃብት፣ እንዲህ እንደቀልድ የሚባክነው፣ ከሰማይ የወረደ ሃብት አይደለም። ፋብሪካዎችን ለመክፈት ሊውል ይችል የነበረ የዜጎች ሃብት ነው። ታዲያ፣ የፋብሪካ ምርት ባያድግ ምን ይገርማል? እንደምንም የተተከሉ ፋብሪካዎችም፣ በኤሌክትሪክ እጦት ይከስራሉ። ወጣቶች ደግሞ፣ በስራ እድል እጦት፣ ኑሮ ይጨልምባቸዋል።   
አዎ፣ ለተወሰነ ጊዜ፣ እዚህም እዚያም እድገት ተመዝግቧል። በአገራችንም፣ በሌሎች የአፍሪካ አገራትም። ለተወሰነ ጊዜም፣ “ትምህርት ተስፋፋ”፣ “ቴሌኮሙኒኬሽን ተንሰራፋ”፣ “መንገድ ተዘረጋ” እየተባለ ትልቅ እድገት መመዝገቡን ስናስተጋባ እንቆያለን። ነገር ግን፣ ያለ ፅኑ መሰረት፣ ብዙ አይራመድም። የፋብሪካ ምርት በእድገት የማይገሰግስ ከሆነና የስራ እድል በስፋት የማይፈጠር ከሆነ፤ ብዙም ሳይቆይ፣ የኑሮ ችግር እየገነነና እየበረከተ፣ “ተምሬያለሁ” የሚሉ ሚሊዮን ወጣቶች ዘንድ፣ ምሬት እየተባባሰ፣ አገሬው ሁሉ ለአቀጣጣይና ለለኳሽ የተዘጋጀ የጭድ ክምር ይሆናል። አቀጣጣይ ደግሞ ሞልቷል። ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች ላይ በማነጣጠር ጥፋትን የሚቀሰቅስ አቀጣጣይ፣ በሃይማኖት ወይም በዘር እያቧደነ ትርምስንና እልቂትን እየደገሰ የሚያጋግል ብዙ ነው - አሰፍስፎ የሚጠብቅ። ይህን ደግሞ፣ በእውን አይተነዋል።
በርካታ የአፍሪካና የአረብ አገራት፣ እንዲህ እየተተራመሱ ሲፈራርሱና ሲጋዩ አይተናል። እያየንም ነው። በአገራችንም፣ ከአንድም ሁለት ሦስቴ፣ አሳዛኝ ግጭቶችንና ጥፋቶችን፣ አስፈሪ ትርምሶችን ተመልክተናል።
በአጭሩ፤ የፋብሪካ ምርት፣ ሁነኛ የረሃብ መድሃኒት፣ መሰረታዊው የኑሮ ማሻሻያ፣ የሕይወትና የአገር የህልውና ዋስትና ነው። የፋብሪካ ምርትን የሚነካ ማንኛውም እንቅፋት ደግሞ፣ የረሃብ ድግስ፣ የኑሮ ሳንካ፣ የሕልውና ጠንቅ ይሆናል። “የአካባቢ ጥበቃ” ግን፤ “እንቅፋት” ብቻ አይደለም። ፋብሪካ ላይ ያነጣጠረ ጠላት ነው። ማለትም የሕልውና ጠላት!
ሰሞኑን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ከአለማቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ እንድትወጣ መወሰናቸውን ገልፀዋል። በአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ሳቢያ፣ በርካታ ሚሊዮን አሜሪካዊያን ለስራ አጥነት እንደዳረገ የገለፁት ፕ/ር ትራምፕ፣ በዚያ ላይ ለዘመቻው ብዙ ገንዘብ እንድንመድብ ስንገደድ ቆይተናል ብለዋል። ትራምፕ፣ እስካሁን ከሰሯቸው ነገሮች ሁሉ፣ ይህንን የሚስተካከል ትልቅ ስራ የለም። ይሄ፣ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራትም ትልቅ ውለታ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ፣ ከአሜሪካ የሚያገኘው ገንዘብ ከተቋረጠበት፣ የድሃ አገር ሃብት በከንቱ እንዲባክን የሚገፋፋ ዘመቻም... ባይቋረጥ እንኳ ትንሽ ረገብ ይላል።
ነገር ግን፣ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚቆጠር የድሃ አገር ሃብት እየባከነ የሚገኘው ግን፣ ከውጭ አገር በሚሰማሩ የአካባቢ ጥበቃ ዘማቾች ብቻ አይደለም። በየአገሩ ባለስልጣናት ውሳኔም ጭምር ነው። ባለስልጣናት፣ አንድ ሁለቴ፣ ሳያውቁ በስህተት ሊወስኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ብክነቱን እልፍ ጊዜ እያዩና እየተነገራቸው፣ በተመሳሳይ መንገድ የድሃ አገር ንብረት እንደቀልድ እንዲባክን ተጨማሪ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው - ይሄ እያወቁ በድፍረት የሚፈፀም ጥፋት ነው። ያስቆጫል። በእርግጥ፣ ውሎ አድሮ፣ በሕግ የሚጠየቁበት ጊዜ የሚመጣ ይመስለኛል። ግን፤ ከዚያ በፊት፣ ስራ አጥነት እንደ ጭድ ተከምሮ፣ በዘረኝነትም ሆነ በሃይማኖት ሰበብ ጥላቻን በሚቀሰቅሱ ክፉ ሰዎች ለኳሽነት፣ አገሬው ተተረማምሶ እንዳይፈርስ ያሰጋል።

        “የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ” ሳቢያ፤ በርካታ ሚሊዮን አሜሪካዊያን ስራ አጥ መሆናቸውን ተናግረዋል -
        ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ።
    
     እንግሊዝ      በ25% ቀንሷል       ከ4 ሚሊዮን ወደ 3 ሚሊዮን
     ፈረንሳይ      በ25% ቀንሷል        ከ4 ሚሊዮን ወደ 3 ሚሊዮን
     ጣሊያን       በ20% ቀንሷል        ከ5 ሚሊዮን ወደ 4 ሚሊዮን
     አሜሪካ       በ25% ቀንሷል        ከ20 ሚሊዮን ወደ 15 ሚሊዮን

 
    የፋብሪካ ምርት ድርሻ ባለፉት 15 አመታት ከስንት ወደ ስንት ወረደ? (በ%)
                                  
  የ15                                                        
ዓመታት
የቁልቁለት
ጉዞ (ልዩነት)
ሞሪሼስ             24      ወደ     16          -8
ዛምቢያ             30      ወደ      9          -21
ዚምባብዌ           30      ወደ      12         -18
ደቡብ አፍሪካ       24      ወደ      13          -11
ሞሮኮ               22       ወደ      17          -5
ቱኒዝያ              21        ወደ      14          -7
ግብፅ                20       ወደ      16          -4
ማላዊ                20       ወደ      10          -10
ሴኔጋል               17        ወደ     .13          -4
ቡርኪና ፋሶ          17        ወደ      6            -11
ርዋንዳ                17        ወደ      5           -12
ኮት ዲቯር            17        ወደ      13           -4
ሞዛምቢክ            18         ወደ      10           -8
ኬንያ                 14         ወደ      11            -3
ጋና                   11          ወደ      5            -6
ዩጋንዳ               10          ወደ      8            -2
ናይጄሪያ             10          ወደ      9             -1
ታንዛኒያ              11           ወደ      6             -5
ኢትዮጵያ             8           ወደ     4              -4
ቦትስዋና              7

Read 1892 times