Sunday, 04 June 2017 00:00

ለዓፄ ሠርፀ ድንግል ጀግንነት የተበረከቱ ዕጣነ ሞገሮች

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋዬ (ዶ/ር)
Rate this item
(4 votes)

   ዓፄ ሠርፀ ድንግል በኢትዮጵያ ከነገሡና ከውጭ ወራሪዎች ጋር በከፍተኛ ደረጃ እየተዋደቁ የሀገራችንን ዳር ድንበሯንና ወሰኗን አስከብረው ከኖሩ ጀግኖች ነገሥታት ተርታ የሚመደቡና ልክ እንደ ዓፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ኩራት የሆኑ ንጉሥ ናቸው፡፡ የዓፄ ሚናስና የንግሥት አድማስ ሞገሳ ልጅ የሆኑት ዓፄ ሠርፀ ድንግል ጎንደር ላይ ሲነግሡ የ13 ዓመት ልጅ ነበሩ። ዴኒስ ኖዝኒሶቭ  እንደጻፈው፤ የተወለዱት እ.ኤ.አ  በ1550  ሲሆን የሞቱት ጥቅምት 4 ቀን 1597 ነው። የገዙበት ዘመን ደግሞ ከ1563 እስከ 1597 ነው፡፡ ዓፄ ሚናስ  የዓፄ  ልብነ ድንግል (ድንግል ያበራችለት ለማለት ነው) ልጅ ሲሆኑ በአህመድ ግራኝ ጦርነት ወቅት በቱርኮች ተማርከውና ታሥረው ቱርክ የቆዩ፤ በኋላም በእሥረኛ ልውውጥ (በምርኮኛው በአህመድ ግራኝ ልጅ በመሐመድ) ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሰው ናቸው፡፡ የእሥረኛ ልውውጡም በተለይ ሁለቱን እናቶች የዓፄ  ልብነ ድንግልን ባለቤት እቴጌ ሰብለ ወንጌልንና የአህመድ ግራኝን ባለቤት ድል ወንበራን  በእጅጉ አስደስቷቸዋል፡፡   
ዓፄ  ልብነ ድንግልና እቴጌ ሰብለ ወንጌል ዐራት ወንዶችንና አራት ሴት ልጆችን  ወልደዋል፡፡ ወንዶቹ ፊቅጦር፤ ያዕቆብ፤ ገላውዴዎስና ሚናስ (የዓፄ ሠርፀ ድንግል አባት) ሲሆኑ ሴቶቹ ደግሞ ታዖድራ፤ ወለተ ቅዱሳን፤ ሰበነ ጊዮርጊስ፤ አመተ ጊዮርጊስ ይባላሉ። ቅዱስ ራጉኤል አስቀድሞ የወንዶች ልጆቻቸው የወደፊት እጣ ፈንታ፤ እድል ተርታ  እንዴት እንደሆነ በራዕይ ለዓፄ ልብነ ድንግል የነገራቸው መሆኑም በገድለ ራጉኤል ላይ ሠፍሮ ይገኛል፡፡ ይኸውም ፊ ይመውት (ፊቅጦር ይሞታል) የሚል ሲሆን እንደ ትንቢቱ ፊቅጦር በአህመድ ግራኝ ጦር ተገድለዋል። ገ ይነግሥ (ገላውዴዎስ ይነግሣል) እንደተባለው ዓፄ ገላውዴዎስ ተብለው ነግሠዋል፡፡ ሚ ይሠየጥ (ሚናስ ወደ ውጭ አገር ይሸጣል) እንደተባለው ሚናስ ተማርከው ወደ ቱርክ እንደ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ልጅ እንደ ምንትዋብ  ተግዘዋል፡፡ ያ ይነብር (ያዕቆብ ይኖራል ) ተብሎ እንደተነገረው አቤቶ ያዕቆብ ብዙም ችግር ሳያገኛቸው ኖረዋል፡፡
በጀርመን የሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኢትዮጵያ የጥንት ሥነጽሑፍ ታሪክ ተመራማሪ የሆነው ሩሲያዊው ዶክተር ዴኒስ ኖዝኒሶቭ  (2010) በኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ ቅጽ 4 ገጽ 544 ላይ፣ ስለ ዓፄ ሠርፀ ድንግል የዘውድ አወራረስ  እንደጻፈው፤ አባታቸው ዓፄ ሚናስ  በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ወራሴ መንግሥታቸው ማን መሆን እንዳለበት ስለአልወሰኑ በድንገት ሲያርፉ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡
ከዚህም የተነሣ በወቅቱ ዘውዱን ማን መውረስ እንዳለበት የሚወስን ምክር ቤት በአስቸኳይ ተመሠረተ፡፡ ወላጅ እናታቸው ንግሥት አድማስ ሞገሳ በአሉበት የምክር ቤቱ አባላት በከፍተኛ ደረጃ ከተመካከሩ በኋላ፣ የ13 ዓመቱ ልጅ ሠርፀ ድንግልን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አድርገው  አነገሡዋቸው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ እውቁ ጸሐፌ ታሪክ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓፄ ልብነ ድንግል እስከ ዓፄ ቴዎድሮስ (2000፡ 83) በሚለው መጽሐፋቸው ዘርዘር በአለ መልኩ በአሰፈሩት ጽሑፍ፤ “የዓፄ ሠርፀ ድንግል አባት ዓፄ ሚናስ በ1556 ዓ፡ም ሲሞቱ እንደተለመደው መኳንንቱ ለምክር ተሰባሰቡ፡፡ በጉባኤውም ማን እንደሚነግሥ ብዙ ክርክር ተደረገ፡፡ ግማሾቹ የዓፄ ሚናስ ትልቁ ልጅ ይንገሥ አሉ፡፡ ከፊሎቹ  የዓፄ  ልብነ ድንግል እኅት የወይዘሮ ሮማነ ወርቅ ልጅ ሐመልማል ይንገሥ አሉ፡፡ በዚህ ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ዋና ዋናዎቹ አለቆች አዛዥ ቁሞ፤ሊቀ ሊቃውንት ክፍለ ማርያም፤ኣባ አጽቀ ድንግል፤ ሊቀ ስብሐት ለአብ አናንያ፤የዘበኞች አለቃ ትንሹ ማር ሠርፀ ድንግል ይንገሥ ብለው ስለወሰኑሥርዓተ መንግሥት አድርገው አነገሡዋቸው፡፡ ይኽንንም አደባባይ ወጥተው ዓፄ ሚናስ ስለሞቱ ልጃቸውን ማር  ሠርፀ ድንግልን ስማቸውን መለክ ሰገድ ብለን አንግሠናል” በማለት በአዋጅና በነጋሪት ለሕዝቡና ለወታደሩ አስታወቁ፡፡ ከዚህ በኋላ ለዓፄ ሚናስ በገሐድ ለዐርባ ቀን ኀዘን ተደረገላቸው” ይላሉ፡፡
ቀስ በቀስ በአካል እየጠነከሩና በአእምሮም እየበሰሉ የመጡት ዓፄ ሠርፀ ድንግል  ቤተ መንግሥታቸውን ጎንደር ጉዛራ ላይ አድርገው  በንግሥና ላይ በቆዩባቸው 34 ዓመታት የተነሡባቸውን የውጭ ጠላቶቻቸውንና የውስጥ ተቀናቃኞቻቸውን ድል እየነሱ የሀገራችንን ዳር ድንበር ጠብቀው፤ ወሰኗን አስፋፍተው  ኖረዋል፡፡ ከሰሜን ወደ ሸዋ፤እናሪያና ወደ ጉራጌ፤ ወደ ሐረር --- ከሠራዊታቸው ጋር እንደ አንድ ተራ ወታደር እየተጓዙ፣ ሕዝቡ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖና  አንድ ሆኖ  እንዲኖር  አድርገዋል፡፡
በኋላም በተለይ በቀይ ባሕር ዙሪያ  አሰፍስፎና ተሰልፎ ከመጣባቸው ከቱርክ ዘመናዊ ጦር ሠራዊትና ከጠላት ጋር አብሮ ከከዳቸውና ከሸፈተባቸው ባሕር ነጋሽ ይስሐቅ  ጋር በአደረጉት መራራ ትግል  በለስ ቀንቷቸውና ቱርኮችንና ግብፆችን  አጥፍተው ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡ በግእዝ ከተጻፈውና ዓለሙ ኃይሌ ወደ አማርኛ ከተረጎሙት  ዜና መዋዕላቸው ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው ( 1999 :121 እና 136)፤ ዓፄ ሠርፀ ድንግል በቱርኮች፤ በግብፆችና በከሐዲው ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅ ላይ ድል የተቀዳጁት በዘመነ ፋሲካ ነው፡፡ ከጀግኖቻቸው ውስጥ ዕቁበ ሚካኤል አንደኛውና ዋነኛው ሲሆን ውድዙም ደግሞ  በጦርነቱ የተደመሰሰ የውጭ  ጠላት   ነው፡፡ ይኽንኑ የድል ብሥራት መሠረት አድርጎ ዕጣነ ሞገሮችን  የተቀኘው ጰራቅሊጦስ የተባለና ከተዋጊው ሠራዊት ጋር አብሮ የነበረ ደብተራ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዕጣነ ሞገር የሚከተለው ነው፡፡       
ገባሬ፡ መንክራት፡ ሙሴ፡አመ፡ በዐለ፡ናእት፡ወጠነ።
ውስተ፡ ባሕረ፡ ሱፍ፡ አስጠመ፡ ግብጻውያነ፡፡\
ወለአግብርተ፡ ፈርዖን ወሀቦሙ፡እምግብርናት፡ግዕዛነ፡፡
ክርስቶስ፡ ቤዛ፡ ኵልነ፡፡
በኵረ፡ ምውታን፡ ሕይወቱ፡ አስተጻንዓ፡ ተስፋነ፡፡
ወመልአከ፡ ሞት፡ ታሕተ፡ ሲኦል ኮነ፡፡
ሠርፀ ድንግል፡ ተጸጎ፡ በእንተዝ፡ሰርጎ  ፋሲካሁ፡ብርሃነ፡፡
ወአምሳለ፡ ሳሚ፡ መስተቃርነ፡፡
ዘአፍቀረ፡ ዕብነ፡ ከደንዎ ዕብነ፡፡
ወለዕብንኒ፡ረሰዮ፡ ፀወነ::
ትርጉም ተአምረኛው ሙሴ የቂጣ በዓልን በአከበረበት ጊዜ  ግብጻውያንን  በቀይ ባሕር ውስጥ አሰመጣቸው፡፡ እስራኤሎችንም ከፈርዖን ባርነት ነፃ አወጣቸው፡፡ ነገር ግን  አዳኛችን፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ  ለሙታን ሁሉ ሕይወትን ሰጥቶ ተስፋችንን አለመለመው፡፡ መልአከ ሞትም ከሲኦል በታች ኾነ፡፡ ሠርፀ ድንግል በጌታ ትንሣኤ  ብርሃን ያሸበረቀውን የድል ልብስ ልበስ፡፡ በሳሙኤል ረድፍ በተቃርኖ ያለው ደንጋይን የሚወድድ ነው፡፡ ደንጋይን ያፈቀረ ደንጋይ ይዘጉበታልና ፡፡ ደንጋይም መጠለያው፤መዝጊያው ይሆናል፡፡
ምሥጢር የዚህ ዕጣነ ሞገር ይዘት በኢትዮጵያ የትንሣኤ በዓል ዕለት የውጭና የሀገር ውስጥ ጠላቶቹን በቀይ ባሕር ዙሪያ አሸንፎ ከፍተኛ ድል የተቀዳጀውን  ዓፄ ሠርፀ ድንግል  የሚያወድስና የሚያሞግስ ነው፡፡ ከዚህ ድርሰት የምንረዳው  የቅኔው  ደራሲው የጠለቀ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያለው መሆኑን ነው፡፡ ደራሲው ዓፄ ሠርፀ ድንግልን የሚያነጻጽራቸው ከነቢዩ ሙሴ ጋር ነው፡፡ ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ኃይል፣ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዳወጣቸው፣ ዓፄ ሠርፀ ድንግልም  መንግሥታቸውን ለማወክ፤ የሕዝባቸውን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣልና ኢትዮጵያን በቱርክና በግብጻውያን የባርነት ቀንበር ሥር ለመዋል የመጣውን  ውድዙምን   መክተው  ከነሠራዊቱ እንደፈጁት ቅኔው ያስረዳል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ዋናው የቱርክ ጦር መሪ የነበረው ውድዙም በዓፄ ሠርፀ ድንግል ጦር አዝማች  በጀግናው ዕቁበ ሚካኤል በዕለተ ፋሲካ በተገደለ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረው ደስታ ወሰን አልነበረውም፡፡ ባለቅኔው ደብተራ ጰራቅሊጦስም የድሉን ዜና ለማድመቅ  አስቦ፣ ክርስቶስ በሞቱ በዕለተ ትንሣኤ ነጻ እንዳወጣን ዓፄ ሠርፀ ድንግልም  በዕለተ ፋሲካ መሥዋዕትነት ከፍለው ነጻነት ያቀዳጁን መሆናቸውን ነግሮናል፡፡ የዓፄ ሠርፀ ድንግልን የጀግንነት ታሪክና የሀገራችንን የጥንት ሁኔታ  እንድንረዳም  አድርጎናል፡፡              
የዓፄ ሠርፀ ድንግልን ድል አድራጊነት የሚያወድሰው ሌላው ዕጣነ ሞገርም የሚከተለው ነው፡፡
ዐረባውያን ዕደው በበማዕርግ   ወክፍል፡፡
ለቀዊም፡ ቅድሜከ፡ ሠርፀ፡ ድንግል፡፡
እምኀበ፡ እንድርያስ፡ ተጸውዑ፡ በጽዋዔ፡ ንባብ፡ወቃል፡፡
እምዝኒ፡ዘይትሌዓል፡
በኵለንታከ፡ ተተክለ፡ ሥርወ፡ መድኃኒት፡ መስቀል፡፡
በኵለንታከ፡ ተጽሕፈ፡ ወንጌል፡፡
ኦ፡በጽድቅ፡ ፈጻሚ፡ጸዋትወ፡ ኵሉ፡ አምሳል፡፡
እንዘ፡ ለሊከ፡ ተሐውር  መንገለ፡ ኃይል፡ እምኃይል
ታበቁል፡ ቀርነ፡ ለእስራኤል፡፡
ምስለ፡ ሠራዊትከ፡ ኑኀ መዋዕል::
እስከ፡ ጊዜ፡ ወርሥአን፡ጥ ሉል፡፡
ይኽ ዕጣነ ሞገር እንደ  መጽፊያና እንደ ወረብ ሆኖ በየበዓላት ቀኖች በየቤተክርስቲያኑ    ሲዘመር መኖሩም ተመልክቷል፡፡
ትርጉም ሠርፀ ድንግል ሆይ! የዐረብ ሰዎች ደረጃቸውና ማዕርጋቸው በሚፈቅድላቸው መሠረት፣ ለአንተ ክብር  ይሰለፉና ይቆሙ ዘንድ  በእንድርያስ አማካይነት  በቃልና በጽሑፍ ተጠሩ። በተጨማሪም ከዚህ የሚበልጠው በሁለመናህ የመድኃኒት መስቀል ሥር ተተክሏል፡፡ ይህም ወንጌል በሁለመናህ እንደተጻፈ  ይቆጠራል፡፡ ሁሉንም በእውነት ምሳሌ ሆነህ ታደርጋለህና  በራስህ በኃይል ላይ ኃይል ጨምረህ ትሔዳለህ፡፡ ለእስራኤልም ቀንድ ታበቅላለህ፡፡ ከሠራዊትህ ጋር ለምን ጊዜም  አብረህ ለመኖር ያብቃህ፡፡
ምሥጢር ሐዋርያው እንድርያስ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተጠራ፣ዓፄ ሠርፀ ድንግልም   ዐረቦችን በቀይ ባሕር ጠረፍ  ዙሪያ እንዲወጉዋቸው ለእውነተኛው የመስቀል ጦርነት በእግዚአብሔር የተጠሩ፤ እውነተኛው የመስቀልና የወንጌል አማኝ መሆናቸውን
ያመለክታል፡፡ በቀይ ባሕር ጠረፍ  ዙሪያ ያካሄዱት ጦርነት  የክርስትና እምነትን  ከወረራ እንዳዳነውም ቅኔው ያመሠጥራል፡፡ የሚከተለው መልክዐ ሥላሴ የቅኔው መነሻ ምንጭ  ሆኖ ማገልገሉንም ልብ ይሏል።  
ሰላም ለኩልያቲክሙ፡እለ ዕሩያን በአካል፡፡
ዓለመክሙ ሥላሴ አመ ሐወጸ ለሣህል፡፡
እምኔክሙ አሐዱ እግዚአብሔር ቃል፡፡
ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፡
ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል፡፡ (ተስፋ 1987.3)  
ትርጉም በተመረጠው ሰውነት ላይ ለሚገኙት ለኩላሊቶቻችሁ ሰላም ይሁን፡፡ ሥላሴ ዓለማችሁን በምሕረት በጎበኛችሁ ጊዜ  ከእናንተ ውስጥ አንዱ የእግዚብሔር ቃል ይሆናል፡፡ በማርያም ድንግል የአባቶቻችን ተስፋ ተፈጽሟል፡፡ በቀራንዮም መድኃኒቱ መስቀል ተተክሏል፡፡  

Read 3992 times