Sunday, 04 June 2017 00:00

የኢትዮጵያ የተስፋ መስኮቶች በግጥም

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(21 votes)

 አንቺም ስሚኝ ፍቅሬ!
  እምዬ ሃገሬ
መመኪያዬ ክብሬ አትበይኝ አስሬ!
ክልል፤ ጎሳ፤ ብሔር ስም ሆኖ መለያ
ለዘር ግጥም፤ ዜማ ከተሰራ ወዲያ
ወዴት ነች አንድ ሃገር፣ ወዴት ነች ኢትዮጵያ?
         
   የሀገር ጉዳይ የነፍስ ጉዳይ ነውና በልቤ ሲደልቅ ቢከርምብኝ፤ ወደ ኋላ ተመልሼ ገጣሚያን ምን ተስፋ አጭረው ይሆን? ምን ትንቢት ተናግረው ይሆን? ብዬ ሰነድ ፍተሻ ገባሁ፡፡ መቸም ሀገር ባንድ ቀን ተጠፍጥፋ የምትሠራ ቂጣ አይደለችም። ደግሞም ባንድ አፍታ የምትፈርሥ የጭቃ ብይም ያህል አንገምታትም፡፡ ይልቅስ በጊዜ ሂደት ውስጥ ተጥዳ ቅርፅ እየያዘች፣ እየበሠለች፣ የብዙ ሰዎች ዕውቀት፣ ጉልበትና ህይወት ወሥዳ፣ የምታድግና የምትበለፅግ፤ ማህበራዊ፣ ሥነልቡናዊ፣ ባህላዊና ሌሎችም መልኮችዋን የምታወጣ፣ የህዝቦችዋ ሀብትና ክብር ናት፡፡
በየዘመኑ ሁሉም ይኖሩባታል፤ ሁሉም ይኖሩላታል፡፡… ያለሟታል፣ ያጠፉዋታል፡፡ ከያንያን ደግሞ እንደየ ዓተያያቸው፣ እንደየ ዝንባሌያቸው ያዜሙለታል፤ ይቀኙለታል፡፡ ቀን ከከፋ ደግሞ እንባ ይረጩላታል፡፡.. የእኛ ሀገር ከያኒያን ብዕርና ብሩሽ ከዚህ የዘለለ ዕጣ አይኖረውም፡፡.. ስደተኞቹ እንደነ ኢቫንቱር ጌኔቭ፤ ያገሬ አፈር ሽታው ናፈቀኝ፣ ሊሉ ይችላሉ፡…. እንደ ቶልስቶይ… ሊነጫነጩ! አንዳንዶቹ እልም ያለ ጨለማ ውስጥ ሆነው፤ ብርሃን ሊያዩ… አድማሱን አበባ አልብሰው… ሙሾውን፣ በሣቅ ሊያቀልሙት ይችላሉ… እንደየ ህልማቸው፡፡
እኔም ወደ ኋላ ሄጄ፤ የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ሻምበል ክፍሌ አቦቸር ስለ ሀገር የጻፈውን ግጥም ሳሥሥ፤ የወጣቱ ገጣሚ ዮናስ ኪዳኔ፣ ግጥም በጆሮዬ አቃጨለ፡፡ ግጥሙ ረጅም ነው፤ ርዕሱ ግን ቀሽምና ርዕሰ ጉዳዩን የማይመጥን ነው፤ ‹‹አትበይኝ›› ይላል፡፡ ለመንደርደሪያ ያህል ከዚህ ግጥም ጥቂት ስንኞች እዋሳለሁ፡-
አንቺም ስሚኝ ፍቅሬ!
እምዬ ሃገሬ
መመኪያዬ ክብሬ አትበይኝ አስሬ!
ክልል፤ ጎሳ፤ ብሔር ስም ሆኖ መለያ
ለዘር ግጥም፤ ዜማ ከተሰራ ወዲያ
ወዴት ነች አንድ ሃገር፣ ወዴት ነች ኢትዮጵያ?
እውነት ነው፤ የአንድነት ነገር እንደ ሰማይ እየራቀን ሄድዋል፡፡ በተለይ ከኢሕአዴግ ሥልጣን  መያዝ  በኋላ ብሔራዊ ስሜት እየቀዘቀዘ፣ አንድነታችን እየላላ፣ ልዩነታችን እየጠበቀ መጥቷል፡፡ ሰዎችን በግለሰባዊ ማንነታቸው ከማሰብ ይልቅ፣ ዘር ወደ መፈተሽ ዝቅ ብለናል፡፡… እውነት ነው፤ በአንድ ሀገር፤ በአንድ ባንዲራ ሥር፣ አንዱ ጌታ፣ ሌላው ሎሌ ሆኖ ይኑር! የሚል እምነት በጎ አይደለም፡፡… ግን ደግሞ የአንድነትን ቋንቋ ደባልቆ፣ እልፍ መንገድ እየተጓዙ ወደ አንድ ግብ መድረስ አይቻልም፡፡ (ቋንቋ የምለው፣ የሀሳብ ልዩነትና አለመግባባትን ነው፡፡)
ከሁሉ የሚያሣዝነው ደግሞ፣ ሆነ ተብሎ ቂም የመቆስቆስ ጉዳቱ ነው፡፡ አንዱን ከአንድ ጋር ማባላት… ይልቅስ ቀና ልብ ቢኖረንና በጋራ ለማደግ ብናስብ፣ ልዩነታችንን እያከበርን፣ የተበታተነ ልዩነታችንን ይዘን፣ እንደ ችቦ አንድ ላይ ወገባችን ቢታሠር፣ ብርሃናችን ደምቆ ጨለማችንን ያበራው ነበር፡፡… አሁን ያለው ሁኔታ ግን በእጅጉ የተለየ ነው። ጥቂት ንፋሳት እንደ ትቢያ ሊበትኑት የሚችሉትን ያህል ገለባ ሆነናል፡፡ መንደርተኝነት ተጠናውቶናል፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና ስልጤ ወዘተ ብለን የጎሪጥ መተያየት ጀምረናል፡፡ ኑሯችን የጥርጣሬና የጥላቻ ሆኗል፡፡ ቂም ቋጣሪ፣ በደል መንዛሪ ሆነናል።… ቂምን መተው፣ ይቅርታ! ማድረግ የሚባል ነገር ጠፍቶብናል…. ለዚህ ነው ገጣሚው ዮናስ ኪዳኔ፤ ‹‹…ሃገር ወዴት አለች?›› ያለን... ያሣዝናል!
ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ በበኩሉ፤ አሁን ስላለንበት ሁኔታ ‹‹ላም ሀገር›› በሚል ግጥሙ እንዲህ ይላል፡-
ወተቷን ለማግኘት
እናትና ልጅን- እየነጣጠለ
አላቢ ማንነት- ‹‹አርቢ›› ከተባለ
ለልጇ የማይሆን-ግት ያጋተች ሀገር
ስሟ ላም ይባላል
እሷ እየታለበች- ጥጃዋ ሲታሰር፡፡
የጋራ የሆነች ሀገር ለጥቂቶች ጥቅም ውላለች፡፡ ጥጆች ወተት አይቀምሱም፤ ሹሞች ግን እየጠቡዋት ነው፤ ወደሚል ሀሣብ ይወሥደናል፡፡ በተለይ ሙስና ጣሪያ ነክቷል፡፡ ህዝቡ በየሠፈሩ እያነባ ነው፤ እያለቀሰ ነው፡፡ እንደ ሞት ቀን ድንኳን ቢተከል፣ ሀገሩ በሙሉ ልቅሶ ነው፡፡ የመንግሥት ጆሮ ደግሞ ወደ ራሱ መዝሙር ነው፡፡ ለምተናል… አድገናል… ጠግበናል!... የዛሬዋ ሀገር ይህቺ ናት፡፡… አዎ ጥቂት ኑሮ የተሻሻለላቸው፤…. መኪና የቀያየሩ.. ቤት ላይ ቤት የገነቡ አሉ፡፡ ግን በፍትሃዊ መንገድ አይደለም ነው፤ ነገሩ፡፡
ብአዴን በ1985 ዓ.ም ያሣተመው ‹‹ሶረኔ›› የግጥሞች ስብስብ ውስጥ “የአርሶ አደሮች እንጉርጉሮ” በሚል ከተፃፈው ግጥም ጥቂት  ስንኞች፡-
የጭቆና ቀንበር ከብዶ በላያችን
በግብር በጉቦ አልቆ ጉልበታችን
በጦር በሰፈራ አልቆ ወገናችን
መጣልን ኢሕአዴግ የነፍስ አባታችን፡፡
ይህም አንጓ በዘመኑ የነበረ ተስፋ ነው፡፡ ደርግ እንባ ሲያሥረጫቸው ከርሞ ኢሕአዴግ ሲመጣ፤ ነፍሳችንን ያድናል፣ ቀንበራችንን ይሰብራል… ብለው ዘመሩ፡፡ ግጥም ከስሜት እሣት ውስጥ የሚወረወር ትንታግ ነውና - ያንን ነው የተቀኙት! ነገር ግን አሁንስ?... ጉቦ ቀርቷል?... የጭቆና ቀንበር ተሰብሯል?... መልሱን ለራሱ ለባለ ግጥሙ፣ ለባለ መጽሐፉ መተው ነው፡፡.. ሀገራችን ለምን የመንግስታት መፈራረቂያ ብቻ እንደሆነች፣ ወደ ኋላ ሄዶ መፈተሽ ደግ ሣይሆን አይቀርም። የአድርባይነትና የመጨቋቆናችን ሥነ ልቡናዊ መነሾና ዳራስ ምን ይሆን? ዘሩ ያለው እላይ ባለው መንግስት ላይ ብቻ ነው፡፡ ወይስ ለእኛ ልብ ውስጥ የበቀለ መረራ ሥር ነው?..
ግጥሞች ብዙ ነገር የምናይባቸው መስተዋቶች ናቸው፡፡ መዐዛቸው የሚያውድ አበባዎች፣ ሣቃቸው የሚያንሳፍፍ ርግቦች ናቸው፡፡ ነበልባላቸው እሳት ሆኖም የሚለበልብበት ቀን ብዙ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ለሀገር ከሁሉም ይልቅ ፍቅርና አንድነት ይቀድማል፡፡ ሀገር ማለት፣ ጥሩ ሰፈር ላደጋችሁ፣ ፍቅር ለነበራችሁ ሁሉ ምስሉ ቅርብ ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ … እናቶችን አስቡ፡፡ … ሰርግ ላይ፣ ሽክ ብለው፣ ሲዘፍኑ ሲዘምሩ፣ … ልቅሶ ላይ ደረት ጥለው ሲያለቅሱ፣ … የራበህ ቀን እንጀራ የሚያጎርሱህ፣ ብትወድቅ “እኔን ድፍት ያድርገኝ!” ብለው፣ እንባህን ጠርገው የሚያነሱህ፣ … እነርሱ ናቸው፤ ያገርህ ሰዎች! … ከነዚያ አንዱን መነጠል፣ ከነዚያ አንዱን መግፋት አያምም? ስጋህን ቆርጠህ ትጥላለህ? … ትግሬ ሆነ ኦሮሞ?... አማራ ሆነ ጉራጌ? … መበታተን ህመም ነው፤የህሊናም ሥቃይ! …
“እንዲህ አልነበርንም” ሲል ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ይነግረናል፡፡
ሁሉም የናት ልጅ ነው፣
ሁሉም ያባት ልጅ ነው፣
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር
ባላጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ” ሲቸገር፡፡
እንግዲህ ሀገር ይህቺ ናት፡፡ የተጣላ እንኳ አይጨካከንም፡፡ ሁሉም ወንድም ነው፤ እንደኔ ላለው፣ ቡቡ፣ እኔን ለመሰሉ ባከናዎች ገጣሚ ነቢይ መኮንን ግጥም ፅፏል-”ሀገር ናት በቃ” ብሎ።
ይቺው ናት ኢትዮጵያ
ሀገርህ ናት በቃ!
በዚች ንፍቀ ክበብ፣
አይምሽ እንጂ መሽቶ፣ ማታው ከጠረቃ
የነቃም አይተኛ የተኛም አይነቃ፡፡
ይቺው ናት ዓለምህ፣ ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ!
አኪሯ ቀዝቅዞ፣ “ያንቀላፋች ውቢት” ያንተው የክት ዕቃ!
ምን ትሆን እንግዲህ ሀገርህ ናት እሷ!
ልቧን አታውልቃት አትጨቅጭቃት በቃ!
አብረህ አንቀላፋ፣ ወይ አብረሃት ንቃ!---
ምንም ትሁን፣ በምንም ሁኔታ ትኑር! … ሀገርህ ናት! ሌላ ሀገር የለህም፡፡ ከተኛች ተኛ!... ከነቃች ደግሞ ንቃ!... ነው የሚለን ነቢይ፡፡
ወደ ሻምበል ክፍሌ አቦቸር ግጥም ልመለስ፡-
ንጋትሽ - እንደ - አደይ!
ምሽትሽ እንደ ጨረቃ!
ተራራሽ እንደ - ሰንደቅ!
ፏፏቴሽ እንደ ሙዚቃ!
ልብ ይሰርቃል!
*  *  *  
እስከዚያው ግና!
አትከፊ - ይከፋናል
አይጭነቅሽ - ይጨንቀናል
ያልፋል! - ሁሉም ያልፋል!
የማያ-ልፍ፣ አንድም የለም
“ቸል” ባትይ “ቻል” አድርጊው
የማይቻል አይኖርም መቼም
እና … ግድ የለም!
ግድ የለም፣ አልኩሽ - ግድ የለም
የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እንጂ፣
ሰቆቃሽ የ“ዕድል” አይደለም፡፡
ሁሉም ስለ ሀገር፣ በየራሳቸው ተስፋ ክንፍ፣ በየራሳቸው ጭቃ ጡብ የተመኙትን ቀርፀዋል፤ የወደዱትን ብለዋል፡፡ እኛም አንብበን አይተናል፡፡ በየመስኮቶቹ አንገታችንን ብቅ አድርገን ቃኝተናል። … ግና ተስፋ አንቆርጥም፡፡ … አሁንም በጎነትን እንጠብቃለን! … አሁንም ከዘር የጸዳ አንድነትን ----- በመከባበር የታጀበ ኢትዮጵያዊነትን እናልማለን፡፡
ጠቢብ ቤት ሳይኖረው፣ መስኮት ይከራያል
ግድግዳ ሳያቆም፣ ሽንቁር ይከራያል
ያጮለቀ ብቻ ሁሉን ነገር ያያል፡፡
---- ከሚለው የበዕውቀቱ ስዩም ግጥም ጋር ነፍሴን አስራለሁ፣ ልቤን አስጠጋለሁ፡፡

Read 8075 times