Sunday, 04 June 2017 00:00

መፍትሄ የሚሹ የአክስዮን ማኅበራት ችግሮች (ከጥናት ዕፍታ የቀረበ ማስታወሻ)

Written by  በሺፈራው ተስፋዬ
Rate this item
(0 votes)

     ከዕፍታው የቀረበ ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ በአገር አቀፍ ደረጃ በአክስዮን ማህበራት ላይ ሊሰራ ለታሰበው ጥናት፤ የመነሻ መሰረት እንዲሆን እየተሰራ ካለው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት (preliminary study) ግኝቶች ውስጥ፤ ጊዜ የማይሰጡና አስቸኳይ መፍትሔዎች የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ የአክስዮን ማህበራት ችግሮችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ነቅሶ በማውጣትና በማሳየት፣ የሚመለከታቸው ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት በሙሉ፤ እስካሁን ከታየው ወይም ከደረሰው በላይ ከባድ ጉዳት ከመድረሱና ከፍተኛ የዜጎችና የአገር ሐብትም ከመባከኑ ወይም ከመውደሙ በፊት ተገቢውን ወቅታዊ እርምጃ እንዲወስዱ ለማስታወስ ወይም ለማሳሰብ የቀረበ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ዕፍታ ነው፡፡
ደረጃውን የሰቀለው የ1952 ንግድ ሕግና አዲሶቹ ሙከራዎች፡- የአክስዮን ማህበራትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በ1952 ዓ.ም በታወጀው የንግድ ሕግ ውስጥ በአንቀጽ 6 ሥር የተካተቱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ሕጉ ሳይሻሻል፣ የአፈጻጸም ደንብ እና መመሪያ ሳይወጣለት በመጪው መስከረም 57ኛ ዓመቱን ያከብራል፡፡ በእርግጥ ቀደም ሲልም ሆነ በቅርብ የንግድ ሕጉን በተለይም የአክስዮን ማህበራትን ድንጋጌዎች ለማሻሻል ጥረቶች እንደነበሩ ይነገራል፣ እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የተደረጉትን የማሻሻያ ረቂቆች ለጊዜው ማግኘት ያልተቻለ ሲሆን፤ በቅርቡ በፍትሕ ሚኒስቴርና በንግድ ሚኒስቴር የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቆች ለማየት ተችሏል፡፡ ሁለቱም ጥረቶች በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያነሱና የያዙ ቢሆንም፤ ከዚህች አጭር ጽሑፍና ከትኩረቱ ውሱንነት አንፃር ጥቂት ጉዳዮችን ብቻ በማሳየት ለማለፍ ተመርጧል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር አመራር ከተለያዩ መ/ቤቶች በተውጣጡ የሕግ ባለሙያዎች ተረቆ የቀረበው ረቂቅ፤ ቀደም ሲል ከተሰሩት ጥናቶች ላይ ትምህርት አልወሰደም፡፡ የራሱም የሆነ መሠረታዊ ጥናት የለውም፡፡ እስከ ዛሬ ያጋጠሙትንና ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከግንዛቤ ሳያስገቡ፤ በአጠቃላይ ሁኔታዎች ግምገማ (General Situational Analysis) ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ አንዳንድ ረቂቅ ሐሳቦች ያሉትን ችግሮች የሚያባብሱና ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን እንደሚችል በቀላሉ መረዳት ይቻላል። የመነሻ ሀሳቦቹ ግምታዊ፣ ንድፈ ሐሳባዊና በግል ገጠመኝም ከችግሮቹ ጋር የመተዋወቅ ዕድል ያልነበረ ስለሚመስል፤ በችግሩ ለቆሰለ ሰው፤ በሰው ቁስል እንጨት እንደ መስደድ ዓይነት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገቡት አክስዮን ማህበራት በተግባር (defacto) በአንድ ሰው ተመስርተው፤ ምንም ዓይነት ትርጉም ያለው ተሳትፎና ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ሆኖ እያለ፤ አክስዮን ማህበራት በአንድ ግለሰብ ይደራጁ የሚል ሕግ ተረቆ ቢፀድቅ ምን ውጤት እንደሚኖረው በጉዳዩ ላይ ትንሽ ቅርበት ያለው ሰው ወይም ትንሽ ማሰላሰል የሚችል ውጤቱን በጥልቀት መረዳት ይችላል፡፡ የአክስዮን ማህበራት አባላት ያልሆኑ ሰዎች፣ የቦርድ አባል እንዲሆኑ የሚለውም ሐሳብ ዓላማ፣ ግብና ውጤት ምን እንደሆነ ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ባለሙያ ካስፈለገ በቅጥር ወይም በአማካሪነት ወይም በአክስዮኑ ማስገባት እየተቻለ ማለት ነው፡፡ የመተዳደሪያ ደንብ እንዳይቀርብ ማለት በፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም እንኳን ደንብ ሳይቀርብ ቀርቶ፤ ደንቡ ቀርቦም በስውር የሚሰራው ተገቢ ያልሆነና ሕገወጥ ሥራ ዓይነቱና ይዘቱ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ስለሆነም ግለሰብ የራሱን የግል ተቋም እንጂ የሕዝብ ኩባንያ ማቋቋም የለበትም፡፡
 በአንድ በኩል ከላይ የተገለጡት ዓይነት ከባድ ችግሮችን የሚፈጥሩ ረቂቅ ድንጋጌዎች ሲኖሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማሻሻያ ተብሎ የቀረበው የአርትኦት (editing) ሥራ  ይመስላል፡፡ የንግድ ሕግ ማሻሻል በሕግ ባለሙያዎች ብቻ የሚሠራ ቢሆንም ስፋትና ጥልቀት ባለው አገራዊ ጥናት ላይ ለምን እንዳልተመሠረተ ግልጽ አይደለም፡፡ ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት አቋራጭ መንገድ ያለ አይመስልም። መሰራት ያለበትን ወሳኝ ሥራ መሥራት ግድ ነው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ አክስዮን ማህበራትን በተመለከተ የንግድ ሕጉን በሚገባ መረዳትና፤ ካለው ተጨባጭ ችግሮች አንፃር ያለውን ትርጉምና አንድምታ በመመርመር፤ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው መራመድ ያቃታቸውንና፤ ሐብታቸው፣ ዕድላቸው፣ ድርጅታቸው እየወደመ ያሉትን ለመታደግ የሚያስችል መመሪያ በማዘጋጀት፣ በዘመቻ መልክም ቢሆን ጥረት ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው በመሆኑ በአስቸኳይ መሥራት ሁለገብ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የተረቀቀው ረቂቅ የተሻለ ለችግሮቹ ቅርበት ያለውና መፍትሔም ለመስጠት የሞከረ ነው፡፡ ይኽም መ/ቤቱ ለችግሩ ካለው ቅርበት የተነሳ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ቢሆንም ረቂቁ ብዙ መዳበር አለበት፡፡ ችግሮቹን ለይቶ ከዚያ አንፃር የሕግ መፍትሔ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን የችግሮቹን መነሻ መሠረትና አማራጭ መፍትሔዎችን፤ በአክስዮን የውስጥ ሥርዓትና በሕግ አስከባሪ አካላት መካከል፤ በሚዛናዊነት ማከፋፈልና አፈጻጸሙን ማሳለጥ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ረቂቅ ትልቁ ፈተና፤ የንግድ ሕጉ የአፈጻጸም ደንብ ይሁን ወይስ ይኽን እንደ አዋጅ ወስዶ ሌላ የአፈጻጸም ደንብና መመሪያ ይዘጋጅ የሚለው ነው፡፡ ውሳኔው የመ/ቤቱ ሲሆን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የግል አስተያየት ቀደም ሲል የቀረበው ነው፡፡
በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን የተረቀቁት የንግድ ሕጉን የመሳሰሉት፣ በተለይ አክስዮን ማህበራትን የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ከ57 ዓመታት በኋላ እንኳ ሕጉን በአግባቡ ማዳበርና ማሻሻል ቀርቶ፤ በአግባቡ ለመረዳትና ለመተግበር አለመቻላችን፤ የሕጉ ጥራትና ደረጃ የላቀ እንደነበረ ያሣያል፡፡ በእርግጥም በዚያን ዘመንም ሕጉ አገሪቱ ከነበረችበት በመቶ ዓመት የቀደመ ነው ሲባል እንደነበረ ይነገራል፡፡ ቢሆንም በዘመናዊ ሕግ አገሪቱን የማዘመኑ ሕልም የተሣካ አይመስልም፡፡
የአክስዮን ማህበራት የላቀ ሚና በልማት ውስጥ በመርሕ ደረጃ የልማት አከናዋኝ አካላት በሆኑት በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በሕብረት ሥራ ማህበራት፣ በግል፣ በሕብረተሰብ ምስረታ ድርጅት፣ በልማት ድርጅቶች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ወዘተ በሁሉም የሚቻለው ሁሉ መሠራት አለበት፡፡ ነገር ግን በትክክል ከተሰራ በዘላቂነት፣ በተደራሽነት፣ መሠረታዊ ለውጥ በመምጣት፣ ከፍተኛ ካፒታል በመፍጠር፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ግብር በአግባቡ በመክፈል፣ በግልጽ አሠራር፣ የሌሎችን የልማት አከናዋኞች ሥራ በማገዝና በማመቻቸት፣ ለዲሞክራሲያዊ ቢዝነስና ተቋም አመራር በማለማመድና በማሰልጠን፣ ትርጉም ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣት ወዘተ በመሳሰሉት መመዘኛዎች ማወዳደር ከተቻለ የአክስዮን ማህበራት ሚና የላቀ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በተለይ በምዕራባውያን አገሮች እስከ 10 ሚሊዮን ባለአክስዮን ዜጎችን በአንድ አክስዮን ውስጥ ብቻ በማሳተፍ ተጽእኖና ልዩነት ፈጣሪ የቢዝነስ ተቋም መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሕንድን የመሳሰሉ እየተመነደጉ ያሉ አገሮች የአክስዮን ማህበራትን ዕምቅ ሐብት አሟጦ ለመጠቀም corporate ministry የሚባል የመንግሥት ተቋም መሥርተው እየሠሩ ነው፡፡ ከአፍሪካም፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ የመሳሰሉት ይኽን ተቋም በሚገባ እየተጠቀሙ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። በእኛ አገር በዚህ ረገድ ሕጉ ከተደነገገ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ቢሆንም፤ በተግባር የሚታየው ገና ጅምር ሲሆን፤ የችግሩ ውጥንቅጥነት እጅግ ያስደነግጣል፤ ያስፈራራልም፡፡ የደርግ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ለአክስዮን የማያመች እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፉት 26 ዓመታትም አክስዮን ማህበራት ተገቢ ቦታቸውን አግኝተዋል፣ ምቹ ሁኔታዎችም ተፈጥሮላቸዋል፣ መሥራት የሚችሉትን ያህልም ሠርተዋል ማለት አይቻልም፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ለጥቃቅንና አነስተኛ የዕድገት ግብ ሲቀመጥላቸው፤ አክስዮን ማህበራት ግን ስማቸውም እንኳን ሊጠቀስ አልበቃም፡፡ በሌላ በኩል ዜጎች አክስዮን ማህበራት አመቺ ሆነው ስላገኙዋቸው፤ በራሳቸው ተነሳሽነት ያለውን ሕግ በመጠቀም በሺ የሚቆጠሩ አክስዮን ማህበራትን አቋቁመዋል፡፡ ቢሆንም አመቺ የመንግሥት ፖሊሲ፣ እስትራቴጂና ወቅታዊ ሕግና አፈጻጸም ባለመኖሩ እና ከሁሉም በላይ ከተወሰኑ አክስዮን ማህበራት መሥራቾች፣ ቦርድና ማኔጅመንት በሚመነጩ ችግሮች የተነሳ በዜጎችና በአገር ሐብት፣ የዕድገት ዕድልና ተስፋ ላይ ወደር የሌለው ወንጀል ተፈጽሟል፡፡
ከአክስዮን ማህበራት ልማትና ጥፋት ጋር ተያይዞ የሚወደሱና የሚከሰሱ አካላት፡- ቀደም ሲል እንደተመለከተው አክስዮን ማህበራት ለአጠቃላይ አገራዊ ልማትና ብልጽግና ትልቅ ሚና ስለሚጫወቱ፤ መሥራቾች ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። ክብርና ምሥጋናም ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚም መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ ምሥረታው የሚጠይቀው ትግልና መስዋዕትነት በአግባቡ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ለሕዝብ ቃል ገብተው፣ በሕግ መሠረት ተቋቁመው፣ የሕዝብ ሐብት ከሰበሰቡ በኋላ፤ በትክክል ሥራውን ሠርተው ሁሉንም ተጠቃሚ እንደማድረግ ፈንታ የራሳቸውን አሻንጉሊት ተላላኪና አቀባባይ ቦርድና ማኔጅመንት በስውር ወይም በግልጽ ሰይመው፤ ሁሉን ነገር ለራስ በማድረግ ስግብግብነትና እንዳረጀች ድመት የፈጠሩትን ሁሉ እንብላ ካሉ፤ ወደር የሌለው ጥፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ጊዜ መሥራቾች የቦርድ ሰብሳቢና የማኔጅመንት አመራርም በመሆን ሥርዓቱንና ሥራውንም ያበላሹታል፣ ሐብቱንም ይዘርፉታል፡፡ ይኽ በጊዜያዊና በትንሽ ጥቅም ታውሮ እራስን እንደ ማጥፋት ይቆጠራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው ሁሉንም ቦታ ባይዙም ደካማ ተወካዮቻቸውን ሥልጣን ላይ ያስቀምጡና፤ በሕግና በሥርዓት መሥራት ቀርቶ፤ ተቋሙን ማፍረስ፣ ሥራውን ማበላሸት፣ ሐብቱን መዝረፍ፤ ዋና ሥራ ይሆናል፡፡ ይህ ችግር እንዳይጋለጥ በአክስዮን ድምፅ ሽፋን መስጠትና የከፍተኛ ባለአክስዮኖችንም ድምፅ በምሣ ግብዣና በተሳሳተ መረጃ፤ እየጠፋ ባለው ሐብታቸው ላይ የጥፋት ውሳኔ ተባባሪ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ትክክለኛውን የአክስዮን ልማት ሥራ መሥራት የማይችሉ ቦርድና ማኔጅመንት፤ በእንደዚህ ዓይነት የጥፋት ሥራ ላይ በመሠማራት፤ የዜጎችና የአገር ሐብት፣ የልማት ዕድል እንዲባክን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ዓይነት እየወደመ ያለው የአክስዮን ማህበራት ሐብት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል መገመት ያስቸግራል፡፡ ሕግና መንግሥት ባለበት አገር እንደዚህ ዓይነት ወደር የሌለው ጥፋት ለዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በዜጎችና በሕብረተሰቡም ላይ በቀላሉ የማይጠገን ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ስለሆነም ዜጎች ሐብታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን አስተባብረው ልማት እንዲሰሩና እምነትም እንዲያዳብሩ፣ በሕግና በመንግሥት ላይም እምነት እንዲኖራቸው፣ ኩባንያዎችን ተቆጣጥረው ጥፋት የሠሩት መሥራቾች፣ ቦርድና ማኔጅመንት ለጥፋታቸው በሕግ ሊጠየቁና ፍትሕም ሊበየን የግድ ይሆናል፡፡
የቦርድ አባላትና የማኔጅመንት ምርጫ መመዘኛዎች፡- አንዳንድ የዋህ የሚመስሉ ብልጣ ብልጦች፤ ከፋይናንስ ዘርፍ ውጭ ባሉት አክስዮን ማህበራት የቦርድና የማኔጅመንት ምርጫ የቢዝነስ ባለሙያ እንዲሆን ሕጉ አያስገድድምና የሙያ መመዘኛ ማስቀመጥ ሕገወጥ ነው፤ የባለአክስዮኑንም የመመረጥ መብት ይረግጣሉ ይላሉ፡፡ ይኽ የአክስዮን ማህበራትን ሥራና የሕጉን ድንጋጌ ይዘትና ፍላጎት በሚገባ ካለመረዳትና፤ የቦርድና የማኔጅመንት ወንበር ላይ ቁጭ ብለው የሚጠበቅባቸውን ሥራ ሳይሰሩ ወፍራም ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ከሚቋምጡ ወገኖች ወይም ሁኔታውን በጥልቀት ከማይረዱ ወገኖች የሚሰጥ የዋህ አስተያየት ነው። አክስዮን ማህበራት በብዙ ካፒታል፣ በከፍተኛ ድርጅት የላቀ የሙያ ሥራ የሚሠሩ ቦርድና ማኔጅመንት የቢዝነሱ ተቋማትን፤ በከፍተኛ የቢዝነስ ሳይንስና ጥበብ የሚመሩበት ነው፡፡ ከፍተኛው አመራር (top business management) ቦርድ ሲሆን፤ መካከለኛው አመራር (middle management) ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ ሁለቱም ቢዝነስ ፖሊሲ፣ እስትራቴጂ፣ ዕቅድና ቁጥጥር እንዲሁም ምዘናና ግምገማ (business analysis and evaluation) ለመሥራት የላቀ የቢዝነስ ዕውቀት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን፣ ሕግ መደንገግ አይጠበቅበትም፡፡ ምክንያቱም ይኽ ጉዳይ በእንግሊዝኛው it goes without saying እንደሚባለውና በአማርኛው ደግሞ “ሳይታለም የተፈታ ነው” እንደሚባለው በመሆኑ ነው፡፡ ሕግ እንደ ድርሰት ወይም እንደ ታሪክ ዝርዝሩን ሁሉ እንዲጽፍ መጠበቅ የለበትም፡፡ የቢዝነስ ኩባንያን የሚያክል ትልቅ ተቋም መሥርቶ በቢዝነስ መሐይማን (business ignorants) እንዲመራ በማድረግ ሐብቱንና የሥራ ዕድሉን እንዲጠፋ የሚያደርግ፣ ጤናማ አእምሮ ያለው ባለሐብት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ነገር ግን የቢዝነስ ባለሙያና ሙያ አስፈላጊና ጠቃሚ እንጂ በራሱ ብቻውን በቂ አይሆንም። ባለሙያው ቅን፣ የሚታመን፣ ሐቀኛ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ግዴታውን በሚገባ የሚወጣ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ የማህበራዊ ካፒታል እሴቶች ሲሆኑ ችግር ያለባቸው አክስዮን ማህበራት ውስጥ ዶክተር ሳይንቲስቱ፣ የተከበሩ አዛውንቱ፣ ጎልማሳው ባለሙያ ካለምንም ይሉኝታ ነጭ ውሸት ይዋሻሉ፣ የተሰጣቸውን እምነትና አደራ ይበላሉ፣ በኃላፊነት ስሜትና በታማኝነት ከመሥራት ይልቅ እጅግ የወረደ ሥራ ይሰራሉ፡፡ ስለሆነም ለቦርድና ለሥራ አስኪያጅነት የሚመረጡ ሰዎች በጥንቃቄ መመረጥና ውጤት ካላስገኙና ችግር ከፈጠሩ ካለምንም መዘግየት በተሻለ መተካት አለባቸው፡፡ ጥፋት ከሰሩም ሳይዘገይ በሕግ ፊት ማቅረብ እንደሚገባ የንግድ ሕጉ ደንግጓል፡፡
የአክስዮን ማህበራት (public companies) ተወካዮች (ቦርድና ማኔጅመንት) የሥልጣን ገደብና ተጠያቂነት፡- በአክስዮን ማህበራት አሠራር ቦርድ ጠቅላላ ባለሐብቱን በቀጥታ ተወክሎ የቢዝነስ ማኔጅመንቱን በበላይነት የሚመራ ሲሆን፤ ማኔጅመንቱ ደግሞ በቀጥታ በጠቅላላ ባለሐብቱ ባይወከልም፤ ጠቅላላ ባለሐብቱንና ኩባንያውን በመወከል ይዋዋላል፣ ሥራዎችን ያከናውናል። በዚህ ዓይነት አሠራርና ሂደት ማኔጅመንቱ ሥልጣኑን በቀጥታ ከወካዩ ማለት ከጠቅላላው ባለሐብት እንዳገኘው ይቆጠራል፡፡ ይኽ ማለት ማኔጅመንት የቦርዱ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የኩባንያው ወይም የጠቅላላው ባለሐብት ተወካይ ማለት ተተኪ ተወካይ ስለሚሆን፣ ቀጥታ ሕጋዊ ግንኙነትና ውጤት ይኖራል ማለት ነው። ማኔጅመንት በውክልና ሥልጣኑ አማካኝነት የመዋዋል፣ የመሥራትና የማሠራት፣ ሥራዎችን በሚከውንበት ጊዜ በሕግ፣ በውልና የሥራው ፀባይ ከሚጠይቀው ውጭ በመውጣት የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጥፋቶችን በሚሠራበት ወቅት፤ ተጠያቂነቱ በራሱ በማኔጅመንቱ እንጂ ኩባንያውን/ጠቅላላ ባለሐብቱን የሚመለከት አይሆንም ወይም መሆን የለበትም፡፡ በተለይ በጥፋቱ ኩባንያው ወይም ተቋሙ ተጎጂ በሚሆንበት ወቅት (በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል) ተጠያቂነቱን ማኔጅመንቱ በግል መውሰድ አለበት እንጂ ጉዳት ደርሶበት እያለ፤ በተደራራቢ የማኔጅመንቱን ጥፋትና ጉዳት የሚሸከምበት ወይም የሚሸፍንበት ምክንያት አይኖርም፡፡
አሁን እየታየ ያለው ኃላፊነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ፍጹም ሕጋዊና ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ይኽ ጉዳይ በግልጽና በዝርዝር አዲስ በሚሻሻሉት ሕጎችና የአፈጻጸም ደንቦች ውስጥ መካተት ይገባዋል፡፡

Read 1885 times