Print this page
Sunday, 04 June 2017 00:00

የ17ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች 44 ሺህ ይሆናሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ምዝገባው ሰኞ በ10 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ይጀመራል

     ህዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው 17ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ 44 ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት ተገለፀ፡፡ የተሳታፊዎቹ ብዛት ካለፈው ዓመት በ2000 የጨመረ ሲሆን ይህም በውድድሩ ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት በየዓመቱ እያደገ መሆኑን ያሳያል፡፡  በሌላ በኩል ከውድድሩ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ መሮጫ ቲሸርቶችን በህግወጥ መንገድ በመስራት የሚፈፀሙ ተግባራትን ለመከላከል ታላቁ ሩጫ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ባር ኮድ የተለጠፈበት የመሮጫ ቁጥር እንደሚሰጥ ያስታወቀ ሲሆን ባለፈው ዓመት በነበረው የቀይ እና የአረንጓዴ መሮጫ ቲሸርቶች ላይ ለውጥ መደረጉንም አመልክቷል፡፡ በዚህ መሰረት በ17ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ1 ሰዓት በታች ለሚገቡ አረንጓዴ የመሮጫ ቲሸርት እንዲሁም ከ1 ሰዓት በላይ ለሚገቡት ደግሞ ቀይ የመሮጫ ቲሸርት መዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡
በትናንትናው ዕለት በሂልተን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው  “ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላ የሚደረግ መሆኑ የዘንድሮውን ታላቁ ሩጫ  ልዩ ያደርገዋል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫው የለንደን ማራቶን በለንደን ከተማ የሚፈጥረውን ድምቀት ያህል ትኩረት ስለሚስብ ሁሌም ድጋፋችንን እንሰጠዋለን” ሲሉ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የቶታል ኢትዮጵያ ተወካይ ላሴይ ቱሬ በሰጡት አስተያየት ‹‹የአፍሪካ ትልቁን የጎዳና ላይ ሩጫ የምንደግፈው በሙሉ አጋርነት ነው፡፡ ከ17 ዓመታት በፊት የጀመርነው  ድጋፍ በመቀጠሉ ደስተኞች ነን ›› ብለዋል፡፡ በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች የጎዳና ላይ ሩጫው 17 ዓመታት ጉዞ በተለያየ መንገድ የገለፁ ሲሆን፤ ስፖርት አድማስ በክብር እንግድነት መድረኩ ላይ ተጋብዞ በሰጠው አስተያየት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ባለፉት 17 ዓመታት ውድድሩን በታላላቅ የዓለማችን አትሌቶች የክብር እንግድነት ማሞቁን ሲጠቅስ እነ ሶንያ ኦሱሊቫን፤ ጋሬላ ዛቦ፤ ፖል ቴርጋት፤ ፓውላ ራድክሊፍ፤ ኤሊውድ ኪፕቾጌ…ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከሚዲያው ጋር የተገናኙበትን እድል በአድናቆት አንስቶ፤ የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን በማቀራረብ የጎዳና ላይ ሩጫው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልጿል፡፡
ከ6 ወር በኋላ ለሚካሄደው የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫው ምዝገባው የፊታችን ሰኞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10 ቅርንጫፎች የሚጀመር ሲሆን፤ የውድድሩ አዘጋጆች እንደገለፁት ከውጭ ሀገራት በመምጣት የሚሳተፉት ብዛታቸው ከወዲሁ 750 መድረሱን ነው፡፡   

Read 1933 times