Wednesday, 04 April 2012 10:25

“ማግኔዥየም ሰልፌት በዘላቂነት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

“...የማስታውሰው የአንዲት እናት ሁኔታ አለ፡፡ ሴትየዋ የደረሰች እርጉዝ ነች፡፡ በድንገት ያንቀጠቅጣታል፡፡ ቤተሰብም ወደ ጸበል እንውሰድ ብሎ ሲሰናዳ በድንገት ደም በልብሱዋ ላይ ይመለከታሉ፡፡ አ...አ...ይ ... እንግዲህ መጀመሪያ ወደሐኪም ትሂድና ከዚያ በሁዋላ ባይሆን ወደ ጸበል ትሄዳለች በሚል ተስማምተው ወደሐኪም ቤት ሲያመጡአት ነገሩ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት የሚያስከትለው ኢክላምፕስያ የተሰኘው ሕመም ሆኖ ተገኘ...”

ቦታው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ ሴትየዋ የሰባት ወር እርጉዝ ነች፡፡ በድግፍግፍ ተቀምጣለች፡፡ በግራ  እጅዋ ላይ የመድሀኒትግሉኮስ  መስጫ ከረጢት ተቀጥሎላታል፡፡ በገመዱ ውስጥ ደም አዘል ፈሳሽ ይታያል፡፡ ይህች እርጉዝ ሴት ሰውነቷ ቀጭን የሚባል ነው፡፡ ሰውን ለማየት አይኑዋን የምትገልጠው በግድ ነው፡፡ አይኑዋ ለማየት የደከመው ይመስላል፡፡ ንግግርዋም በዝግታ ነው፡፡ ምን ሆነሻል? የአምዱ ሪፖርተር ጥያቄ ነበር፡፡

“እኔ እዚህ ሆስፒታል የመጣሁት ከወለ አዲስ አበባአካባቢ ሲሆን ምክንያቱም የደም ግፊት ነው፡፡ በእርግጥ ይህን ሕመም ቀደም ሲል ጭርሱንም አላውቀውም፡፡ በእርግዝና ጊዜ ይከሰታል ቢባልም ከአሁን ቀደም ከሁለት አመት በፊት  ልጅ የወለድኩ ሲሆን ይህ ግን አልገጠመኝም፡፡ እኔ ሰርቼ አዳሪ ነኝ፡፡ የተመቸኝ ...ኑሮ የደላኝም አይደለሁም፡፡ ከባለቤ ጋር ተጋግዘን አናሳ ስራዎችን ሰርተን ነው የምንተዳደረው፡፡ እናም ባላሰብኩት ሁኔታ ድንገት አይኔ ዝብርቅርቅ አለብኝ፡፡ ልቤን ደከመኝ፡፡ ሰውነ ሁሉ ታመመ፡፡ ባለቤን አስጠርቼ ተረዳድተው ወደሆስፒታል ሲወስዱኝ እኔ ሁኔታው ምን እንደነበረ ማስታወስ ያቅተኛል፡፡ ደንዝዣለሁ፡፡ ትንሽ ትንሽ እንቅስቃሴ ይሰማኛል እንጂ ምን እንደሚናገሩ ወደየት እንደሚወስዱኝ ጭራሽ አላውቅም ነበር፡፡ አሁንማ ተመስገን ድኛለሁ፡”

የደም ግፊት ታማሚዋ እርጉዝ ሴት ከላይ ያነበባችሁትን መልስ የሰጠችን በጣም በዝግታ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳ ነው፡፡ ይህች ታማሚ ስለልጅዋ እና ስለኑሮዋ አጥብቀን ስንጠይቃት እንባ እየተናነቃት መልስ መስጠት አልቻለችም፡፡ እሱዋን ትተን ወደባለቤትዋ መለስ አልን፡፡

“...እኔ እንዲህ ያለ በሽታ አይቼም አላውቅም ፡፡ አሁንማ ድና እራስዋን ችላ ተቀምጣለች፡፡የታመመች እለት በየሆስፒታሉ ስንዞር እሱዋ እራስዋን ስታ ምንም አታውቅም ነበር፡፡ ልቤ ላይ ተወተፈብኝ... እራሴን አመመኝ ...ትል ነበር፡፡ በአንድ ቀን ነው ሕመሙ የጣላት፡፡ መጀመሪያ ጤና ጣቢያ ከዚያም ጳውሎስ ሆስፒታል እንደገናም ዘውዲቱ ድረስ ...እዛ ሂዱ... እዛ ሂዱ እየተባልም ተዘዋውረናል፡፡ አልጋ የለም የመሳሰሉትን ምክንያቶች እየሰጡን ማለት ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ከዘውዲቱ ሆስፒታል ወደቤትዋ እንዳትመልሱዋት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውሰዱአት ተባልን፡፡ እዚህም በመምጣታችን  ይህውና ነብስዋን አድነውልናል፡፡ እኔስ የሁለት አመት ልጅ ጥላብኝ ሞተች ብዬ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውን ድናልኛለች” ብሏል፡፡

በጥቁር አንበሳ ተኝታ ያነጋገርናት ታማሚ አጠገብ በማዋለጃ ክፍሉ ኃላፊ ነርስ የሆነችው ሲ/ር ሮማን እንደምትገልጸው ፡-

“በጥቁር አንበሳ ማዋለጃ ክፍል ያለው ሁለት አልጋ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ታማሚዎች ስለሚበዙ ወደሌላ ክፍል እናስተላልፋለን፡፡ ሆስፒታሉ ከተለያየ አቅጣጫ የሚላኩ ታካሚዎችን በመቀበል ስለሚያገለግል አንዳንድ ጊዜ አልጋ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ያጋጥሙናል፡፡ ቀደም ሲል ያነጋገራችሁዋት ታካሚ የሆነች ነብሰጡር ሴት የደም ግፊቷ በጣም ከፍተኛ ስለነበር ማግኔዥየም ሰልፌት በጣም ፈጣን የሆነ እና መድሀኒትነቱ ቶሎ መፍትሔ የሚሰጥ ስለሆነ በየደረጃው እንደ አስፈላጊነቱ ሰጥተናታል፡፡  ይህች ሴት በእርግዝናዋ ወቅት ብቻ ሳይሆን ምጥ ላይ የደረሰች ብትሆን እንኩዋን ሳይቋረጥ ለ24 ሰአት መድሀኒቱን መውሰድ አለባት፡፡አንዳንድ ጊዜ ግን እርጉዝ ሴቶች በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲታመሙ በፍጥነት ወደህክምና ስለማይመጡ ከእኛ አቅም በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል ፡፡ ነገር ግን ስሜቱ ሲከሰት ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ቢሄዱ የእራሳቸውንም ያረገዙትን ልጅም ሕይወት ማዳን ይቻላል” ብለዋል፡፡

አቶ አለማየሁ ገብረ ጻዲቅ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማዋለጃ ክፍል አዋላጅ ነርስ በበኩላቸው፡-

“ይህ መድሀኒት ከመምጣቱ በፊት ብዙ እናቶች በሕመም ይሰቃዩ እና ምናልባትም በህይወታቸው ላይ አደጋ እስከማስከተል ድረስ ሊጎዱ ይችሉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ማግኔዥየም ሰልፌት የተባለው መድሀኒት ከመጣ ወዲህ ግን ብዙ እናቶችን ማዳን ችለናል፡፡ ይህንን ሕመም በሚመለከት ህብረተሰቡ ዘንድ መድረስና ማስተማር በጣም ይጠበቅብናል፡፡ ብዙ ጊዜ በተለይም ወደገጠርማ አካባቢዎች የሚኖሩ እንዲሁም በከተማም አልፎ አልፎ የማንቀ ጥቀጥና የመሳሰሉት በሽታዎች በእርጉዝ ሴት ላይ ሲከሰት ሰዎች የሚገምቱት ከባእድ አምልኮ ጋር በማያያዝ ስለሆነ በፍጥነት ወደሆስፒታል አይመጡም፡፡ በሆስፒታል ደረጃ በእርግዝና ክትትል ጊዜ ሁልጊዜ ምክር እንሰጣለን፡፡ የህመሙን ምልክት በመንገር... እንደዚህ ያለ ነገር ሲታያችሁ ቶሎ ወደ ሆስፒታል ሂዱ እንላለን፡፡ በአሁን ጊዜ ብዙ እናቶች ይህንን ምክር ተግባራዊ ስለሚያደርጉ በዚህ ሕመም ምክንያት እራሳቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ተጎጂ አይሆኑም ማለት ይቻላል”

በእርግዝና ወቅት በሚከሰት የደም ግፊት ሳቢያ ታማሚ እናቶችን ለማየት በየካቲት 12 ሆስፒታልም ተገኝተናል፡፡ በየካቲት 12 ሆስፒታል ያገኘናት እርጉዝ ሴት የመውለጃ ጊዜዋ ደርሶአል፡፡ ነገር ግን ድንገት በተከሰተ የደም ግፊት ሳቢያ ፊቷ አባብጦአል፡፡ እግሩዋም እጁዋም አብጦአል፡፡ የሚያሳዝን ድምጽ ከማሰማት ባለፈ ለሰው የሚሰማ ነገር አትናገርም፡፡ ...የማቃሰት ድምጽ ብቻ ታሰማለች፡፡ የህክምናውን ሂደት ትረዳት የነበረችው ነርስ እንደምትለው...

“ኢክላምፕሲያ የተባለው በእርግዝና ጊዜ የሚከሰተው የደም ግፊት ነው እንደዚህ መልክዋን ሁሉ የለዋወጣት እና መናገር እንዲያቅታት ያደረገው፡፡ በእርግጥ  ማግኔዥየም ሰልፔት የተሰኘውን መድሀኒት ስለሰጠናት ሁኔታዋ እየተሸሻለ መጥቶአል፡፡ አሁን በመጠባበቅ ላይ ያለነው የመውለጃዋን ሰአት ነው” ብላለች፡፡

ማግኔዥየም ሰልፌት የተሰኘውን መድሀኒት ዩኒሴፍ ወደአገር ውስጥ በሚያስ ገባበት ወቅት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኢሶግ ክኒካል እግዛ እንዲያደርግ በመወሰኑ ከማህበሩ አባላት መካከል በየካቲት 12 ሆስፒታል በመስራት  ላይ ያሉት ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ በአገር አቀፍ ደረጃ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ በመሆን በመስ ራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ስለሁኔታው ቀጣዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

“... በእርግዝና ወቅት የሚመጣው ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት የእናቶችን ሕይወት በመቅጠፉ ረገድ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ ማግኔዥየም ሰልፌት በሌሎች የአለማችን ክፍሎች በስራ ላይ ከዋለ ወደ ስድሳ አመት ያለፈው ሲሆን በእኛ አገር ግን ካለፈው አመት ጀምሮ ወደ 113 የመንግስት ሆስፒታሎችና 40 ወደሚ ሆኑ የግል የህክምና ተቋማት ውስጥ እርጉዝ ለሆኑና በደም ግፊት ምክንያት ለሚታመሙ እናቶች ይህ መድሀኒት በመሰጠት ላይ ነው”

“እስከአሁን የተሰጠውን አገልግሎት በሚመለከት ወደ 23 በሚደርሱ  ሆስፒታሎች በተደረ ገው ዳሰሳ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑ እናቶች የመድሀኒቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በአጠቃላይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ የሚሆን ሰፋ ያለ ጥናት በመሰራት ላይ ሲሆን ያም ጥናት የእናቶችን ሕይወት በማዳን እንዲሁም በልጆች ሁኔታ ላይ የተገኘውን መሻሻል የሚያሳይ ይሆናል፡፡ የመድሀኒቱን ስር ጭት በሚመለከት እስከአሁን ባለው አሰራር ስራውን የሚሰሩ ሆስፒታሎች ምን ያህል መድሀኒት እንደሚያስፈልጋቸው በመነጋገር የሚታደል ሲሆን ይህ ሁኔታ ግን በወደፊቱ አሰራር ቀጣይነት ወዳለው አሰራር እንዲለወጥ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ በወደፊቱ አሰራር የሚጠበቀው የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ይህ ንን መድሀኒት እንደሌሎች አስፈላጊ መድሀኒቶች ዝርዝር ውስጥ አስገብቶ ለሁ ሉም ሆስፒታሎች በተገቢው መንገድ መዳረስ እንዳለበት ይታመናል”

“በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት በወሊድ ጊዜ በሚከሰት ደም መፍሰስ ምክንያት ከሚከሰተው ሞት በመቀጠል እናቶችን ለህልፈት የሚዳ ርግ ነው፡፡ ስለዚህ ከምእተ አመቱ የልማት ግብ አንጻር 3/4ኛውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ እቅድ የተነደፈ ሲሆን እቅዱን ተፈጻሚ ለማድረግ የማግኔዥየም ሰል ፌት ተግባር ላይ መዋል አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በተቻለ መጠን በሁሉም መንግስት ሆስፒታሎች እና የተወሰኑ የግል የህክምና ተቋማት ውስጥ መድሀነቱ እየተሰጠ ቢሆንም ባገኘነው አለም አቀፋዊ ልምድ መሰረት እስከ ጤና ጣቢያዎች ድረስ ለመውረድ እቅድ ነድፈን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ማግኔዥየም ሰልፌት የተሰኘውን መድሀኒት በደም ግፊት ለሚሰቃዩ እርጉዝ እናቶች በመላ ሀገሪቱ ከሆስፒታል እስከጤና ጣቢያ ድረስ ለመስጠት የሚቻልበት ጊዜ ከሁለት ወይንም ሶስት ወር በላይ አይወስድም” እንደ ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ማብራሪያ፡፡

 

 

Read 1946 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:30