Sunday, 04 June 2017 00:00

በ500 ዶላር በዱባይ ሥራ ጀምራ የተሳካላት ኢትዮጵያዊት ስደተኛ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 በስንት ስቃይና መከራ ነው በሁመራ አድርጋ ሱዳን የገባችው፡፡ እዚያ እንደደረሰች ትንሽ ቤት ተከራይታ ስለማይፈቀድ በድብቅ ምግብ እያዘጋጀች መሸጥ ጀመረች፡፡ በዚህ ሥራ ብዙም ሳትቆይ ወንድሟን ፍለጋ የሄደች ሴት የሠራችውን ምግብ በላች፡፡ በአሠራሯና በሙያዋ ተደንቃ ‹‹አንቺ በጣም ታታሪና ባለሙያ ነሽ፤ በዚህ አሠራርሽና ሙያሽ ዱባይ ብትሄጂ አልፎልሽ፣ ትለወጫለሽ›› አለቻት፡፡
እሷ ግን ወደ ዱባይ እንዴት ተደርጎ እንደሚኬድ አታውቅም ነበር፡፡ ሴትዬዋ ረድታት የትራንዚት ቪዛ አውጥታና 500 ዶላር ይዛ ዱባይ ገባች፡፡ ዱባይ በደረሰች በ15ኛው ቀን ለአንድ ኤርትራዊ 10 ሺህ ድርሃም (የዱባይ ገንዘብ ነው) የ3 ወር የቤት ኪራይ ከፍላ ፍሪጅመራ በተባለ የሱማሊዎች አካባቢ የሠራበት የነበረውን ምግብ ቤት ተከራየች። ኤርትራዊው ገንዘቡን ለቤቱ ባለቤት ሳይከፍል ተሰወረ፡፡ ባለቤቱ፣ ‹‹የቤት ኪራይ ክፈይኝ›› ብለው ጠየቋት፡፡ ‹‹በፊት እዚህ ለተከራየው ሰው የ3 ወር የቤት ኪራይ ከፍያለሁ›› አለቻቸው፡፡ ባለቤቱም፣ ‹‹ለእኔ ምንም አልሰጠኝም፤ የነገረኝም ነገር የለም››፤  አሁን ያለሽ ዕድል የቤት ኪራዩን መክፈል ወይም ቤቱን መልቀቅ ነው›› አሏት፡፡
ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ የነበረችው ስደተኛ ወጣት ሳራ አራጌ፣ በማታውቀው አገር፣ ቤት ‹‹አከራየሁሽ›› ብሎ የተሰወረውን ሰው ፈልጋ ማግኘት እንደማትችል ስለተገነዘበች፣ የቤቱን ኪራይ በድጋሚ ከፍላ ምግብ ቤት ከፈተች፡፡ የመጀመሪያው ምግብ ቤት፣ ዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በደስታም ሆነ በኅዘን መገናኛ፣ ከአገር ቤት የሚሄዱ የተለያዩ ጋዜጦች ማንበቢያ፣ ስለአገር ቤት መረጃ መለዋወጫና መወያያ፣… ስለነበር ስኬታማ እንዳልነበር ወ/ሮ ሳራ ተናግራለች፡፡
የያኔው ስደተኛ የአሁኗ ኢንቨስተር ወ/ሮ ሳራ፣ አንድ ዓመት በዱባይ ከቆየች በኋላ አዲስ አበባ መጣች፡፡ እዚህ እንደመጣች፣ በጣም ጥሩ ሰው ነው በማለት ብዙ ጊዜ ከምትጠራው፣ ከ20 ዓመት በላይ አብረው የኖሩትን ባሏን አቶ ሀብታሙን ተዋወቀችና ተጋቡ፡፡ ከዚያም አብረው ወደ ዱባይና ወደ ሌሎች አገሮች እየተመላለሱ መነገድ ጀመሩ፡፡
ትንሽ ገንዘብ እንደቋጠሩ ምንም ቢሆን በአገር መሥራት ነው የሚሻለው በማለት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የይርዳው ጤና የመጀመሪያው አልበም የታተመበትን ሳራ ቪዲዮና ሙዚቃ ቤት በፒያሳ ከፈቱ፡፡
ወደ ዱባይ ተመልሳ፣ አንድ ትንሽ ቤት ተከራይታ፣ ‹‹አል ሐበሽ›› (የሐበሻ ቤት) የተባለ ምግብ ቤት ስትከፍት የመጀመሪያ ልጇን እርጉዝ ነበረች፡፡ እዚያ አገር የቤት ሠራተኛ እንደ ልብ ማግኘት ይቸግራል፡፡ እህቶቿንና ሌሎችንም ጨምራ፣ ለምግብ የሚሆኑ ግብአቶችን (ዕንቁላል፣ ቅቤ፣ ማር፣ የተለያዩ እህሎችና ቅመማ ቅመሞች፤…) ከኢትዮጵያ እየወሰደች፣ በዱባይ የሚኖሩ፣ ወደ ዱባይ የሚመላለሱ የመርካቶ ልጆችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን እዚያ እየተመገቡ፣ የጎደለውን ነገር እንድታስተካክል እየነገሯትና እየመከሯት፣ አል ሐበሽን አቋቁመው ራሱን እንዲችልና በእግሩ እንዲቆም እንዳደረጉ ወ/ሮ ሳራ በትልቅ አክብሮትና በኩራት ተናግራለች፡፡
አል ሐበሽ ስኬታማ በመሆኑ በተለያዩ የዱባይ ክፍሎች ቅርንጫፎች መከፈት ጀመሩ፡፡ በዱባይ ብቻ የነበረው አል ሐበሽ፣ አሁን አቡዳቢ፣ አድማ በተባሉ አካባቢዎች በአጠቃላይ 10 ቅርንጫፎች የነበሩ ሲሆን፣ አንዱ ስለተዘጋ አሁን ያሉት ዘጠኝ ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ የተዘጋውንም በቅርቡ እከፍታለሁ እያለች ነው ባለሀብቷ፡፡ ሐበሻ ምግብ ቤት የሚያዘጋጃቸው የምግቦች ዓይነቶች 40 ሲሆኑ አንዳንዶቹ ወ/ሮ ሳራ ራሷ የፈጠራቻቸው እንደሆኑ ገልጻለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ  ከቅልጥም የሚሠራው ‹‹ሰቅሰቆሽ›› በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ዱባይ የሄዱ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ይዘውት እንደሚመጡ ባለቤቷ ተናግራለች፡፡፡ ‹‹ካራማራ›› እና ከጎድንና ከድንች የሚሠራው ‹‹ሐበሻ ስፔሻል›› ሌሎች ተወዳጅ ምግቦች እንደሆኑ ገልጻለች፡፡
ባለቤቷ፤ የሁሉንም ቅርንጫፍ ምግብ ቤቶች (ሬስቶራንት) አጠቃላይ ካፒታል በትክክል አታውቀውም፡፡ ነገር ግን የራሷን፣ የልጆቿን የቤተሰቦቿን ወጪ ሳይጨምር ለሠራተኞች ደሞሞዝ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለመንግስት ግብር፣… በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ድርሃም በላይ አስንደምታወጣ ተናግራለች፡፡ ይህ ሁሉ ወጪ የሚወጣው ከትርፉ ስለሆነ፣ በዓመት የምታገኘው የትርፍ ገቢ 6 ሚሊዮን ድርሃም ሊደርስ እንደሚችል ትገምታለች፡፡
ሥራና ኑሮ ዱባይ ውስጥ በጣም ጥሩ ነው፤ የትም አታገኘውም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሰው አገር ሆነህ ሰርተህና ደክመህ ገንዘብ ብታገኝ፣ ኑሮ ቢደላህም፣ አንድ የጎደለህ ነገር እንዳለ ይሰማሃል - የአገር ናፍቆት ሕይወቷን ሙሉ በባዕድ አገር ማሳለፍ አትፈልግም፡፡ አገር ቤት መጥታ ወደ ስደት የሚሄዱ ሴት ወጣቶችን መምከርና ማስተማር፣ በባዕድ አገር ደክማና ሰርታ ባገኘቸው ገንዘብ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን መርዳት እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡
ወ/ሮ ሳራና ባለቤቷ አቶ ሀብታሙ፤ ቀደም ሲል ሩዋንዳ ሚካኤል አካባቢ ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ሰርተው ነበር፡፡ ለማስተዳደር ስላልተመቻቸው ሸጡት፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሸዋ ዳቦ ፊት ለፊት በጌቱ ኮሜርሻል መደዳ ጫፍ ላይ መንትያ ሕንፃዎች፣ ከፊት ለፊት ያለው ባለ 17 ፎቅ ህንፃ አልቆ አንድ የመንግሥት መ/ቤት ተከራይቶታል፡፡ ከኋላ ያለው ባለ 12 ፎቅ ህንጻ እየተገነባ ሲሆን 2ኛ ፎቅ ደርሷል፡፡ የአንደኛው ህንፃ ግንባታ ስላላለቀ ወጪያቸውን በትክክል መናገር አይቻልም፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ ባልሆንም ከ300 ሚሊዮን ብር ሳይበልጥ አይቀርም ብላለች፡፡
እዚህ አገር ምግብ ቤት (ሬስቶራንትና ሆቴል) መክፈት አልፈልግም፤ እኔ በውጭ አገር ሰርቼና ደክሜ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፡፡ አሁን የምፈልገው ሕፃናትን፣ አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩትን ባገኘሁት ገንዘብ መርዳት፤ ሰዎችን ማብላትና ማጠጣት ነው። ዓላማዬ፣ በጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋም ሳይሆን የተቋቋሙትን መርዳት ነው፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች (መቄዶኒያ፣ ሜሪ ጆይ፣…) ተጠልለው ያሉት ብቻ ሳይሆን በየቤቱ ወድቀው ያሉት ነዳያን (አቅመ ደካሞች) እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ እኔ እነሱን መድረስ ብችል ደስታዬ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኼ ነው የባለቤቴና የልጆቼም ሐሳብ፡፡
እኔ ወደ ስደት ለሚሄዱ ወጣት ሴቶች የምመክረው ነገር አለ፡፡ ስደት ጥሩ አይደለም፡፡ እኔ ተሰድጄ ስለተሳካልኝ ሁሉም ይሳካለታል ማለት አይደለም፡፡ በስደት ሞት አለ፣ ችግር አለ፣ ስቃይ አለ፤ ሰው ጠንክሮ ከሠራ እዚህም ሆኖ መቀየር፣ መለወጥና ማደግ ይችላል፡፡ የሚያስፈልገው፣ ዓላማ ኖሮት በጥንካሬና በሐቀኝነት መስራት ነው። እኔ የማስተምረው በመሰደድ ሳይሆን የትም ሆኖ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል ነው… ወደ ውጭ አገር ስለወጣን ሀብታም አንሆንም፣ አገር ውስጥ ስለቀረን ድሃ አንሆንም፡፡ ዋናው ነገር አላማ አድርጎ፣ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡
ሀብት የሚገኘው ውጭ አገር ስለሄዱ ሳይሆን፣ ሀብት ያለው ጭንቅላታችንና አስተሳሰባችን ውስጥ ነው፡፡ የትም ቦታ ሆኖ ሀብት ያለው ጭንቅላታችን ውስጥና በእጃችን ነው ብሎ አስተሳሰብን መለወጥ ነው፡፡ ወደፊት በዚህ ላይ በስፋት አስተምራለሁ በማለት አብራርታለች፡፡

Read 3462 times