Sunday, 11 June 2017 00:00

ከ16ቱ ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ሹመቱን አልፈልግም አሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአዊ ዞን ሀገረ ስብከት በከፍተኛ ድጋፍ መርጧቸው ነበር

      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ እንዲሾሙ በቅርቡ ከመረጣቸው ቆሞሳት አንዱ፣ “የጀመርኩት ሥራ አለብኝ” በሚል ዕጩነቱን እንዳልተቀበሉት፣ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አስታወቁ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ግንቦት 10 ቀን ባካሔደው ምርጫ ተወዳድረው ካለፉት ዕጩ ቆሞሳት አንዱ የሆኑት፣ አባ ገብረ ሥላሴ ተስፋ፣ በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያኒቱ ገዳማት አገልጋይ እንደሆኑና ከቅዱስ ሲኖዶሱ በደብዳቤና በስልክ ለተላለፈላቸው ጥሪ፣ የጀመሩት ሥራ እንዳለ በመጥቀስ፣ ዕጩነቱን እንደማይቀበሉትና በሹመቱም ለመገኘት እንደማይችሉ ማስታወቃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት የምርጫ ሥርዓት ደንብ መሠረት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ጋራ በምዕራብ ጎጃም - አዊ ዞን ሀገረ ስብከት ለውድድር የቀረቡት አባ ገብረ ሥላሴ፣ ድምፅ ከሰጡት 38 አጠቃላይ የምልአተ ጉባኤው አባላት 31ዱን በማግኘት በከፍተኛ ድጋፍ ተመርጠው እንደነበር ታውቋል፡፡
በቦታቸው ስለሚተኩት ዕጩ፣ ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት በተጨማሪነት ይካሔዳል ከተባለው ምደባ ጋራ ጉዳዩ እንደሚታይ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  የአዊ ዞን ሀገረ ስብከትን በአሁኑ ወቅት ደርበው እየመሩ ያሉት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ሊቃነ ጰጳሳት በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት ምደባ ለማካሔድ፣ ከሀገር ውስጥና ውጭ የተጠቆሙና በቅዱስ ሲኖዶሱ በተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት፥ ዕውቀታቸው፣ የቆየ ታሪካቸውና ሥነ ምግባራቸው ተገምግሞና ተመዝኖ ብልጫ ያገኙ 16 ዕጩ ቆሞሳት በቅዱስ ሲኖዶሱ እንደተመረጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፈው ግንቦት 14 ቀን መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የፊታችን ሐምሌ 9 ቀን ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙት ዕጩ ቆሞሳት፣ ከመጪው ሁለት ሳምንት በኋላ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና፣ ትምህርተ ኖሎት፣ ሕግና ታሪክ፣ አስተዳደር፣ የቅርስ አያያዝ፣ ማኅበራዊ ኑሮና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሴሚናሮች እንደሚሰጣቸውና እስከ ሰኔ 15 ቀን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ተጠቃለው በመግባት ሪፖርት እንዲያደርጉ በቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት መታዘዛቸው ታውቋል፡፡

Read 4228 times