Sunday, 11 June 2017 00:00

ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ሃገራቸው ላይ ተፈፅሟል ላሉት በደል ካሣ እንዲከፈላቸው ተማፀኑ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ፤ በሃገራቸው ላይ ተፈፅሟል ላሉት በደል፣ ሃገራት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ግፊት በማድረግ፣ ካሣ እንዲያስከፍሏቸው መማጸናቸው ተዘግቧል፡፡  
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ ለበርካታ የአገራት መሪዎች ልከውታል በተባለው ደብዳቤያቸው፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብና ግጭት ከተንኮል የመነጨ መሆኑን በመግለጽ፣ አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለመቆጣጠር ባላት ፍላጎት ሳቢያ የታሪክ ትስስርና እስትራቴጂያዊ አንድነት ባላቸው አገራት መካከል ቅራኔ ፈጥራለች ሲሉ ከስሰዋል፡፡   
በቅኝ አገዛዝ ዘመን የነበረው ድንበር በግልፅ ይታወቃል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት፤ ህጋዊ ሃላፊነቱን በመወጣት፣ መሬታችንን ያስለቅቅልን ብለዋል። በአገራቸው ላይ ያለ አግባብ ተጥሏል ያሉትን ማዕቀብ የማንሣትና በኤርትራ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት የማስቆም ግዴታ የፀጥታው ምክር ቤት እንዳለበት በመልዕክታቸው መግለጻቸውን  ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ”ኤርትራ ሽብርተኞችን እያሰለጠነች የሃገሬን ሰላም ለማደፍረስ እየሠራች ነው” የሚል ክስ በተደጋጋሚ የሚያቀርብ ሲሆን በቅርቡም ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ መንግስታቸው በኤርትራ ላይ ሊከተለው ያቀደውን አዲስ ፖሊሲ እያዘጋጀ መሆኑን መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡

Read 4136 times