Sunday, 11 June 2017 00:00

ለቀጣዩ ዓመት 320.8 ቢ.ብር በጀት ታቅዷል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

  - ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ዳጎስ ያለ በጀት ተይዟል
      - ለድርቅ አደጋው 8.3 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቧል
      - የኮሜርሻል ብድሮች ለተወሰነ ጊዜ ይገደባሉ ተባለ
      - ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 1.95 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው
      - 98.1 ቢሊዮን ብር ከታክስ ተሰብስቧል
      - የመኸር እህል ምርት 290.3 ሚሊዮን ኩንታል ነው
      - ለመንግስት ብቻ በተተዉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች፣ የግሉ ዘርፍም ይሰማራል
      - በመጪው ዓመት ዘጠኝ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራ ይጀምራሉ
         
     የቀጣዩን ዓመት የፌደራል መንግስት በጀት አስመልክቶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከሰተ፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጫና ማብራሪያ ሰጡ። በጀቱ በቋሚ ኮሚቴዎች ታይቶ እንዲፀድቅ ለቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው 38ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባቀረበው የበጀት ዝርዝር መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ በቀጣዩ በጀት ዓመት ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ዳጎስ ያለ በጀት ተይዟል፡፡ ከአጠቃላይ የ2010 በጀት ውስጥ 61.8 በመቶ የሚሆነው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤና እና ለገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች የተመደበ ሲሆን ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድና ለከተማ ልማት ስራዎች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ከፍ ያለ በጀት ተበጅቷል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን መረጃ ጠቅሶ መግለጫው ይፋ እንዳደረገው፤ በዘንድሮው ዓመት ከዋናው የመኸር ምርቶች 290.3 ሚሊዮን ኩንታል እህል ተሰብስቧል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 8.8 በመቶ ብልጫን አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለተከሰተው የድርቅ አደጋም 8.8 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቧል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ በዚሁ ዝርዝር መግለጫቸው ላይ እንደገለፁት፤ በኤክስፖርት ገቢው ላይ የሚታየው ማሽቆልቆል አሳሳቢ ነው። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከኤክስፖርት የተገኘው 1.95 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከተገኘው የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ድክመት አሳይቷል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ ሸቀጣሸቀጦች የተገኘነው የኤክስፖርት ገቢ ለኢምፖርት የተከፈለውን የውጪ ምንዛሬ መሸፈን የቻለው 17 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው፡፡ የኤክስፖርት ገቢው አነስተኛ በመሆኑ አገሪቱ የምትወስዳቸውን ብድሮች መልሶ ለመክፈል የማያስችላት በመሆኑ በአበዳሪ አገራትና በዓለም የገንዘብ ተቋማት ግምገማ አገሪቱ ያለባትን የሥጋት ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጓል ብለዋል፡፡
በቀጣዮቹ ዓመታት በኤክስፖርት ገቢው ላይ መረባረብ እንደሚገባ ያሳሰበው የሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የኤክስፖርት ገቢው አፈፃፀም ተሻሽሎ አገሪቱ በአበዳሪ አገራት ያለባት የሥጋት መጠን እስከሚቀንስ ድረስ የኮሜርሻል ብድር መውሰድ ለተወሰነ ጊዜ መገደብ እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ዘንድሮ ከተሰበሰበው ጠቅላላ አገራዊ ገቢ ውስጥ 98.1 ቢሊዮን ብር ከታክስ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ይህም በበጀት ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ 57.4 በመቶ ብቻ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
መንግስት በሚያደርጋቸው የኢንቨስትመንት ስራዎች የግሉ ዘርፍም ተሳታፊ እንዲሆንና ሁለቱም ወገኖች በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ለማመቻቸት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ መሆኑን የጠቀሰው የሚኒስትሩ መግለጫ፤ የመንግስትና የግል ሽርክና አሰራርን በሥራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ አሰራርም ለመንግስት ብቻ በተተዉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የግሉ ዘርፍም እንዲሰማራ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል፡፡ አፈፃፀሙን የሚያስተካክሉ የአደረጃጀትና የህግ ማዕቀፎች ረቂቅ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
የዜጎች በህይወት የመኖር አማካይ ዕድሜ ወደ 64.2 ዓመት ከፍ ማለቱን የጠቆመው የሚኒስትሩ መግለጫ፤ ይህም በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ የዓለም አገራትና ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት አማካይ የመኖር ዕድሜ በላይ ነው ብሏል። ዘንድሮ በመገንባት ላይ ያሉት ዘጠኝ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣዩ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል። ለቀጣዩ ዓመት የተያዘው የ320.8 ቢሊዮን ብር በጀት፤ በቋሚ ኮሚቴው ታይቶ ሲቀርብ እንደሚፀድቅ በመግለፅ የዕለቱ የምክር ቤት ውሎ ተጠናቋል፡፡ 

Read 4617 times