Sunday, 11 June 2017 00:00

ድልድዩን ሰበሩት!

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(2 votes)

“አሰፋ ሰርቶ ገንዘብ ያገኘበት ጊዜ የለም፡፡ ቢሰራ ማግኘት ይችላል፣ ፖለቲካው የሚሰራበትን ጊዜ በላው፤ ጨንቻ፣ አርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ አይደለም ንብረት፣ ለእግሩ መቆሚያ የምትሆን ቦታም ቤትም የለውም፡፡ ሕይወቱን በሙሉ እዚህ እስካለ ድረስ የኖረው በኪራይ ቤት ነው፡፡ ባንክ ገንዘብ የለውም፡፡---”
   
        በቀደም እለት ንቁ ከሆኑት የአዲሱ ትውልድ አባላት ጋር ጃፋር መጽሐፍት መደብር ተገናኘን። ስንጨዋወት በርካታ ስራዎችን ለህትመት አብቅተዋል፡፡ እንደ መታደል ሆኖ ከሞላ ጎደል አንብቤያቸዋለሁ፡፡ ጨዋታችን ዘለግ አለና አስደናቂውን ወግ አከሉልኝ፡፡ የጋሼ አሰፋ ጫቦን ቅፅ ሁለት አጠናቅቀዋል፡፡ የጎደላቸው እሱ ወጣት እያለ የፃፋቸው ወጎች ናቸው፡፡ መረጃ ሲለዋወጡ፤ ጋሼ አሰፋ በ1958 የፃፋቸው ወጎች፣ በ1960 መታተማቸውን ተረድተዋል፡፡ በዚህ መቸገራቸውን ሲገልጹልኝ፣ እኔ እንደማግዛቸው ቃል ገባሁላቸው፡፡ ሌላም አስደናቂ ነገር ሰማሁ፡፡ የህይወት ታሪኩን 75% ገደማ አፅፈውታል፡፡ ታዲያ ይህ አዲስ ትውልድ “ልጅ አባቱን ይበልጣል” ቢባል ይበዛበታል፡፡ እንዳሰብኩት የመንግስቱ ለማን ያህል ጥራዝ ይወጣዋል፡፡ በዚህም አሰፋ ጫቦ በአፀደ ሥነ ፅሁፍ አብሮን ይኖራል፡፡
ይህን የወጣቶቹን ጥረት በሂደት እናየዋለን፡፡ እንዴት አፃፉት? ቀኑ ሲደርስ ሁሉን ይገልፅልናል፡፡ ዛሬ ግን ከታላቅ ወንድሙ ሻምበል ሐብተ ገብርኤል ጫቦ ጋር አርባ ምንጭ ተገናኝተን የተጨዋወትነውን እነሆ!
“ሻምበል ሐብተ ገብርኤል ጫቦ እባላለሁ። የተወለድኩት በ1928 ዓ.ም ሲሆን፤ አሁን 81 ዓመት ሞልቶኛል፡፡ ወላጅ አባቴ ጫቦ ሰዴ ሰናኬ የተወለዱት በጋሞ ጎፋ ደራ ማሎ ወረዳ፤ ደራ በሚባል ቀበሌ ነው፡፡ አያት ቅድም አያቶቻችን የደራ ሰዎች ናቸው፡፡ ጫቦ- ሰዴ- ሳንኬ -ሐማ -ያሬ -ወይራ እያለ --- ዘራችን እስከ ሰባት ቤት ድረስ በእንዲህ አይነት ይቆጠራል፡፡
ሰው መቼም መነሻው ከተለያየ አካባቢ ይሆናል። መድረሻውን ነው መነሻዬ ብሎ የሚቆጥረው። የእኛ ዘር አያቶቻችን ከዛላና ከአንድሮ አካባቢ መነሳታቸውን እናውቃለን፡፡ የእኛ አባት ዳና ጫቦ ሰዴ ከአብራካቸው እኔን፣ አቶ አሰፋ ጫቦን፣ ግንብነሽ ጫቦን፣ እሸቱ ጫቦን አፍርተዋል፡፡ ሁለት ተጨማሪ ልጆች ቢወለዱም በሞት ተነጥለዋል፡፡
“አባታችን ፋኖ ነበሩ፡፡ በኋላ ነፃነት እንደመጣ መሳሪያቸውን ታጥቀው 1933 ዓ.ም የፀጥታ ሰራዊት አባል ሆነው እዚህ ጋሞ ጎፋ አገልግለዋል። አባታችን እኔና ወንድሜን አሰፋን በግራና በቀኝ እጃቸው ይዘውን ሄደው፣ ለመሪ ጌታ ብቅአለ ክበቡ ለሚባሉ መምህር እንዲያስተምሩን ሰጡን፡፡ መሪ ጌታ አይነስውር ነበሩ፡፡ እሳቸውም ዘንድ የቤተ ክህነቱን ትምህርት እስከ ድቁና ድረስ ገበየን፡፡ አሰፋ ጫቦ፤ ጨንቻ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቀደሰ፡፡ በኋላም ደጃች ወልደ ማርያም ትምህርት ቤት ገባን፡፡ እኔ እስከ አራተኛ ክፍል ተምሬ፣ የፖሊስ ሰራዊት አባል ስሆን እሱ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማረ፡፡ በ1952 ዓ.ም ላይ መሰለኝ ከአንድ ተማሪ ጋር ተጣላ፡፡ የተጣላው የትምህርት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ከሆኑት ከአቶ ቦጋለ ዋለሉ ልጅ ጋር ነው፡፡ ልጅ ሰለሞን ቦጋለ ይባላል። በፀቡ ምክንያት አሰፋ፣ ሰለሞንን ፈነከተው፡፡ አቶ ቦጋለ አሰፋ እንዲያዝ ያዛሉ፡፡ ተማሪዎች ሲያሳድዱት እሱ ሮጦ አመለጠ። ልጆቹም አሳደውት ተመለሱ። አሰፋም አልማርም ይልና ችግሩን ለእናታችን ይነግራታል፡፡
“አሁን እሱን ለማሸሽ ገንዘብ ያስፈልጋል። በወቅቱ እኔ የማገኘው ደሞዜ 23 ብር ነው፡፡ እሷም ወር ካልደረሰ አትገኝም፡፡ አባታችን በወቅቱ ውትድርናውን ተሰናብተው ነጋዴ ሆነዋል፡፡ በጊዜው የሚገኙት ሻሸመኔ ነበር፡፡ ለንግድ ገዝተው ያስቀመጧቸው ስምንት ጊደሮች አንድሮ አካባቢ ዘመድ ቤት በአደራ ነበሩን፡፡ እናታችንም ለመጓጓዣ የሚሆነውን ገንዘብ ከእነዚህ ጊደሮች መካከል አንድ ሁለቱን ከ12 እስከ 15 ብር ድረስ ሸጣ መጣች፡፡ በሁለተኛው ይሁን በሶስተኛው ቀን ወደ ሻሸመኔ ይሄዳል፡፡ በዚያን ጊዜ በነበረው ገበያ ከጨንቻ አዲስ አበባ የትራንስፖርት ወጪ 7 ብር ነበር፡፡ ሻሸመኔ ከሶስት እስከ አራት ብር ነበር፡፡ ሾፌሩ ቱፋ ይባሉ ነበር፡፡ ስለዚህም የትልቁ መኪና ስያሜ ቱፋ ነበር፡፡ ሰዎች ቱፋ መጣ፣ ቱፋ ሄደ ይላሉ፡፡ ቱፋ እየነዱ እኔ ትኬት ቆርጬ ተቀመጥኩ፡፡ መኪናው ከከተማው ክልል ወጣ እንዳለ እንዲቆም ጠየኩ፡፡ ቆሞ ከአጠገባችን የገብስ ማሳ ነበር፤እዚያ ውስጥ ወንድሜ አሰፋ ተደብቆ እየጠበቀኝ ነበር፡፡
“ለምን አቆማለሁ አለኝ ሾፌሩ”
“ከእናንተ ጋር ሻሸመኔ የሚሄደው ልጅ ይኸውና፤እሱ ነው ከእናንተ ጋር የሚሄደው” ብዬ አመላከትኩኝ፡፡
“ሽፍታ ነው የምጭነው!” አለኝ ሾፌሩ፡፡
ወሬው ተዛምቶ በድፍን ጨንቻ ተሰምቷል። በወቅቱ አሰፋ ልጅ ነው፡፡ ሲያየው እራራለትና መኪናው ላይ አሳፈረው፡፡ በዚያን ጊዜ ከጨንቻ ሻሸመኔ በአንድ ቀን አይገባም፡፡ ወላይታ አድሮ በሁለተኛው ቀን ሻሸመኔ ገባ፡፡ በሰላም መድረሱን የሰው መልዕክት ላከብን፡፡ አባታችንም ኩየራ ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡ በኋላም አዲስ አበባ መጥቶ ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ገብቶ ተማረ፡፡ በኋላም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ፣ በ1959 ዓ.ም በህግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀበለ፡፡
 “አሰፋ በባህሪው ችኩል አይደለም፡፡ ረጋ ያለ ነው፡፡ ግን አትንኩኝ ባይ ነበር፡፡ ይሄንን ስል ፀበኛ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ከደረሱበት ግን አይመለስም፡፡ አሰፋ ትምህርት ጎበዝ ነው፤ሁሌም ከክፍል ጓደኞቹ ልቆ ይገኛል፡፡ ቤተ ክነትም ሆነ በዘመናዊ ትምህርት አብረን በነበርንበት ዓመታት ሁሌም ልቆ ይገኝ ነበር፡፡ አስተማሪ ሁሌም ጎበዝ ተማሪውን ይወደዋል፡፡ በዚህም መሪ ጌታ ከልብ ያፈቅሩት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
“ሲናገርም፣ የሚናገረውን ያውቃል፡፡ ፍሬ ያለውን ሀሳብ መሰንዘር ይችልበታል፡፡ ይህንን ሀሳብ በቅጡ መግለፅ በባህሪው ያዳበረው ከልጅነቱ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም በሚያገለግልበት ደብር ያሉ ካህናት ይወዱት ነበር፡፡ ገብርኤል ያገለግላል እንጂ ማርያምም መድሀኒዓለምም፣ ስላሴዎችም፣ ሚካኤልም እየተዘዋወረ ይቀድስ ነበር፡፡ የግዕዝ እውቀቱ መሰረቱ ከዚህ ነው፡፡ አንዳንድ ፅሁፎቹም ላይ የግዕዝ ጥቅስ ይጠቅሳል፡፡ እውቀቱ ስላለው እንጂ አጠቃቀሙ ጥራዝ ነጠቅ አይደለም፡፡ መሰረታዊው እውቀት አለው፡፡
“የትዝታ ፈለግ” መፅሐፉ ላይ አሰፋ ከእኔ ጋር ከጨንቻ እስከ ደራ የተጓዝነውን መንገድ ይተርከዋል። ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፤ የዘር ማንዘራችን ግንድ የሚጀምረው ከደራ ነው። ቤተሰባችን ደራ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ርስት አለን፡፡ አንድሮ ውስጥም በሶስት አካባቢዎች ርስት ነበረን፡፡ አዝዕርትም ሆነ የስራ ስር ውጤቶች ይመረትባቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ ዘመዶቻችን ቤት ውስጥ በአደራ የምኖርባቸው ከብቶችም አሉን፡፡ ስለዚህ እኔና አሰፋ አንድም እህል ለመጫን፣ ወይም ቅቤ ወደ ጨንቻ ለማምጣት እንላካለን፡፡
“በዚያን ጊዜ ጤፍ በእህልነት ጋሞ ጎፋ ውስጥ አይታወቅም፡፡ አመጋገባችን ብዙ ጊዜ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ የስራ ስር ውጤቶች (ቦይና፣ ቦዬ፣ ድንች) ነበር የምንመገበው፡፡ በከብቶች ጭነን ወደ ጨንቻ እናመጣለን፡፡ እኛ ቤት ፈረስ፣ በቅሎ ምን ጊዜም አለ፡፡ እነዚህን ከብቶች ይዘን ሄደን እንጭንና ጉዞ እንጀምራለን፡፡ በወቅቱ ሁለታችንም ልጆች ነን፤ ስለዚህ ጭነቱ ከመነሻው በደንብ ይጫናል፡፡ ካጋደለም እያስተካከልን እንሄዳለን፡፡
“አንድ ጊዜ መርከብ በሚባል ፈረሳችን እህል ተጭኖ፤ እኔና አሰፋ እየነዳነው ከደራ ወደ ጨንቻ ጉዞ ጀመርን፡፡ መርከብ ጠንካራ፣ብዙ ጊዜ ቤታችን የቆየ ፈረስ ሲሆን የጫኑትን ተሸክሞ መንገዱን እንኳን ሳይሰሩት ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያደርሳል፡፡ ሌሊት ከደራ ተነስተን ሶስት ነው አራት ሰዓት ከሄድን በኋላ ወሎቆሬ በምትባል ቦታ ደረስን፡፡ እዚህ ጋ መንገዱ ተንዷል፡፡ እንደምታውቀው አገሩ ተራራማ ነው፡፡ ይህ ናዳ መንገዱን አፍርሶት ሰው በእግሩ የሚያልፍበት ቦታ ብቻ ነው ያለቻት፡፡ አሰፋ ከፊት ከፊት እየሄደ በዚያች መንገድ ያልፍና ይመራዋል። መርከብ ይከተለዋል፡፡ እኔ ከኋላ አለሁ፡፡ ፈረሱ ገደሉ አጠገብ ሲደርስ እግሩ ሳተ፤ከዚያ ቁልቁል ወደ ገደሉ ወርዶ ወደቀ፡፡ ግፋ ቢል ከአራት እስከ አምስት ሜትር ይሆናል ገደሉ፡፡ ተንፏቀን ወርደን ስናየው ፈረሱ ሞቷል፡፡ በዚህ ደንግጠን ሁለታችንም ጮህን፤ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ደረሱልን፡፡ የእኛ አገር ሰው ሩህሩህ ነው፤ አፅናኑን፡፡
“የማን ልጆች ናችሁ?” አሉን፡፡
“የዳና ጫቦ ልጆች ነን” አልናቸው፡፡
“ድሮ ፋኖ የነበረው?”
“ኡ!ኡ! እሱኮ ጥሩ ሰው ነበር፡፡ አሁን ምን እናድርግ? እህሉን ከዚህ ጨንቻ ማድረስ አይቻልም” ሲሉ እኔ አንድ መላ ተናገርኩ፡፡
“አንድ ፈረስ ደራ አለን፡፡ እኔ ሄጄ ይዤ ልምጣ፤ በእሱ ወደ ጨንቻ እናጓጉዘዋለን” አልኩኝ። “ሂድና አምጣ፤ እህሉ ከወንድምህ ጋር እዚህ ይቀመጥ” አሉኝ፡፡
ከገደል ውስጥ እህሉ ወጣ፡፡ ሰዎቹ ቤት አደራ ሰጥቼ ጉዞ ልጀምር ስል እሱ ፈራ፡፡ ካንተ ጋር እሄዳለሁ አለ፡፡ ሁለታችንም ከምንደክም አንዳችን መሄዳችንን ተስማምተን፣ አግባብቼው ወደ ኋላ ጉዞ ጀመርኩ። ቢፈራም አፅናንቼው እሱ እዚያው እንዲጠብቀኝ አድርጌ መሮጥ ጀመርኩ፡፡ እንደማይደረስ የለም፤ ደርሼ ለአባቴ ነገርኳቸው፡፡
“ልጄስ የት ነው?” አሉኝ፤ ነገርኳቸው፡፡
“ለምን ካንተ ጋር አልመጣም” ብለው በፍጥነት ፈረሱን ጭነው ሰጡኝ፡፡ የበሰለም ምግብ ነበር፤ እርሱን በኮባ ቋጥረው፤ “በል በአስቸኳይ ልጄ ጋ ድረስ” ብለው ሸኙኝ፡፡
 “እኔ ስደርስ እርሱ ሰዎቹን ተጠራጥሮ፣ ከዋናው ቤት ራቅ ብሎ እኔ ወደ ሄድኩበት መንገድ ቋጥኝ ላይ ቆሞ ይጣራል፡፡ ድምፁ ተዘግቷል፡፡ በወቅቱ ከጣሊያን መምጣትም ጋር ተያይዞ እኛም አገር መጨካከን ነበር፡፡ ጋሞ ጋሞን ገድሎ ይፎክር ነበር። ይህንን እየሰማን ነው ያደግነው፡፡ ይህ እርሱን አስፈርቶት ነው ሰዎቹ ቤት ያልገባው፡፡ ሳየው ሁለታችንም ተቃቅፈን ተላቀስን፡፡ መሽቶ ስለነበር ሰዎቹ ቤት አደርን፡፡
በበነጋታው፤ ”አጭሩን መንገድ መርጣችሁ በዚህ በገደላማው መጣችሁ እንጂ ታቹን የመኪና መንገዱ አለ አይደለም እንዴ? በሉ አሁን በእሱ ሂዱ” ብለው በዚያ እንድንሄድ መሩን፡፡   ጣሊያን ያወጣው መንገድ አለ፡፡    
“ሌሊት ተነስተን ገስግሰን እንደማይደርስ የለም ማምሻውን ጨንቻ ገባን፡፡ የደረሰብንን ለእናታችን ስንነግራት እንደገና ለቅሶ ሆነ፡፡ የመርከብ መሞትና መጉላላታችን አሳዝኖዋት፣ ምነው ባይበላ በቀረ ብላ በጣም አዘነች፡፡ ይህንን ቦታ አሁን እርሱ ጎልምሶ በትዝታ ፈለግ ሲቃኘው ውብ አደርጎ ገልፆታል፡፡ እኛ ልጆች ሆነን ይህ ፈተና ካጋጠመን በስተቀር በዚህ መንገድ በወር አንዴ እንጓዝ ነበር፡፡ ውበቱ አሁን እንደገለጠው ነው፡፡
“ፖለቲከኛው አሰፋ ሕይወቱን ላመነበት ሰጥቷል። እኔ የፖሊስ ሰራዊት አባል መሆኔ ተፈጥሮዬም ሆነ፤ ፖለቲካ ቀልቤን አይስበውም፡፡ ግን ወንድሜ ስለሆነ ታናሼም ስለሆነ ፈተና ውስጥ ሲወድቅ ዝም ብዬ አላየውም፡፡ መከራ ላይ ወድቆ እንዳንቸገር የአቅሜን አግዘው ነበር፡፡ ኢጭአትን ሲያደራጁ የአገሩንም ልጆች ሆነ የእምነቱን ተጋሪዎች ሲያሳትፍ አውቃለሁ፡፡ የፖለቲከኝነት ፍላጎቱ በኋላ የመጣ ሳይሆን ከልጅነቱ ነው የሚጀምረው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ አቋም ይዞ ይንቀሳቀስ ጀመር፡፡ በሕግ ክርክር አሜሪካን ደርሶም ተሸልሞ መጣ፡፡ ይህንን ያጫውተናል፡፡ ንጉሱንም በዚህ ሽልማቱ አማካኝነት አግኝቷቸው አናግረውታል፡፡ ሸልመውታል፡፡ ቢሸልሙትም ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ያድም ነበር፡፡
“በ1966 አብዮት ተሹሞ ጋሞ ጎፋ መጣ፡፡ አሰፋ የጋርዱላ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆኖ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የጠቅላይ ግዛቱ አስተዳዳሪ ጄኔራል መብራቱ ፍስሀ ነበሩ፡፡ አሰፋ አንድ ሁለት አመት እንደሰራ የጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር የህዝብ ድርጅት አስተዳዳሪ ሆኗል። ከ1968 እስከ 1969 መጨረሻ ድረስ ሰርቷል፡፡ ቀይ ሽብር ሲፋፋም እሱ ብዙ ሰው አድኗል፡፡ ቀይ ሽብር በጋሞ ጎፋ ውስጥ አልተካሄደም፡፡ አዲስ አበባም ሆነ ሲዳሞ እንደምንሰማው ሁሉ ይሄንን ያህል ሰው ሞተ፣ ይሄንን ያህል ታጎረ ሲባል፣ ጋሞ ጎፋ ላይ ቀይ ሽብር አልተካሄደም፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ በአንዳንድ አወራጃዎች ሊገድሉ ሲሉ፣ እሱ እየተዘዋወረ “ከሕግ ውጪ ሰው አይገደልም” እያለ ነፃ አድርጓቸዋል፡፡ “ቀይ ሽብር ምንድነው? ነጭ ሽብርስ? በማያውቀው ህዝብ መካከል ይህ እልቂት መፈጠር የለበትም” እያለ አራቱንም አውራጃ እየተዘዋወረ የታሰሩትን ሰዎች ሁሉ እንዳይሞቱ አድርጓል፡፡ እኔ እንደማውቀው ቀይ ሽብር ጋሞ ጎፋ ውስጥ አልተካሄደም፡፡ ከማስታውሰው ተማሪዎችና አስተማሪዎች ታስረው ለአደጋ ተጋልጠው በነበረ ጊዜ ደርሶ እንዲፈቱ አድርጓል፡፡----
“የኦሞቲክ ፓርቲ መስራችና መሪ ነበር፡፡ እሱ እኮ በእድሜው ከፖለቲካ ጨዋታ ውጪ ኖሮ አያውቅም፡፡ እኛ ደግሞ ሳንለያይ እንዲሁ እስከ መጨረሻው እንድንኖር በማሰብ፣ እኔ ባለቤቱ ወ/ሮ አሰገደች ወንድሙ፣ ኤፍሬም አሰፋ፣ እመቤት አሰፋ ተሰባስበን፤”እባክህን ይህን የፖለቲካ ዓለም ተሰናብተህ ኑር፡፡ እባክህን እኛን አስበን፣ ይህ አጀንዳህ አንድ ቀን ለዘለአለሙ ያለያየናል” እያልን ተማጽነነዋል። “አንተ እኮ በሙያህ ብትሰራ ለእኛ አይደለም ለሌላም የምትተርፍ ነህ፤ ይህንን የፖለቲካ ጨዋታ ለምን አትተውም” ስንለው እሺ ይለናል። ይሁን እንጂ መንፈሱ በምንም ተአምር ከፖለቲካ አይወጣም፤ እርሱ በአቋሙ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅርና ትግል ሲል እኛን በፖለቲካው ለወጠን። ይህንን ፍቅር ሚያዝያ 27 ቀን ስላሴ አፈር ሲቀምስ አየነው። እኩዮቹ የስራ ባልደረቦቹ ብቻ አይደሉም፤ አዲሱ ትውልድም አልቅሶ ሸኘው፡፡
“ሰርቶ ገንዘብ ያገኘበት ጊዜ የለም፡፡ ቢሰራ ማግኘት ይችላል፣ ፖለቲካው የሚሰራበትን ጊዜ በላው፤ ጨንቻ፣ አርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ አይደለም ንብረት፣ ለእግሩ መቆሚያ የምትሆን ቦታም ቤትም የለውም፡፡ ሕይወቱን በሙሉ እዚህ እስካለ የኖረው በኪራይ ቤት ነው፡፡ ባንክ ገንዘብ የለውም፡፡ እኔ ከአስመራ መጥቼ ለአጭር ጊዜ አብሬው ኖሬያለሁ (ቅድስት ማሪያም አምስት ኪሎ) ውስጥ አፓርታማ ላይ ነበር የሚኖረው፤ ግንቦት 1983 እዚያው ነበርኩኝ። እስከ ሰኔ 20 ድረስ አብሬው ነበርኩ፤ ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም በመንግስት ምስረታ ወቅት ተሳትፎ ነበረው፡፡ ይከራከር ነበር፡፡ ውይይታቸው ሕገ መንግስቱ ላይ ነበር፤ይሄንን ስታይ ባለቤቱ አሳየችኝ፡፡
‹‹ይኸውልህ ሐብቴ፤ ወንድምህ ትላንትና ስመክረው አድሬ ዛሬ ሄዶ ገባበት እየው›› አለችኝ፤ ቴሌቪዥን ላይ ሲናገር እናያለን፡፡ ማታ ሲመጣ፤ ‹‹ባክሽ እኔ ዝም ብዬ ነው›› እያለ እኛን ያታልለናል። ተሳትፎው ቀጥሎ አገር እንዲያረጋጋ፣መንግስት መመስረቱን ለሕዝብ እንዲያበስር ተላከ፡፡ ነሐሴ አምስት 1983 ዓ.ም ወደ ደቡብ መጥቶ አንዳንድ መስሪያ ቤት እየሰበሰበ ሲናገር ነበር፡፡ ጨንቻ ነሐሴ ዘጠኝ 1983 ዓ.ም ድሮ በተማረበት ደጃዝማች ወልደ ማሪያም ትምህርት ቤት ሽማግሌዎችን፣ የመንግስት ሰራተኞችን፣ ተማሪዎችን ሰብስቦ የማረጋጋት ስራ ሰርቷል፡፡
“እኔ እዚያ አልነበርኩም፡፡ በወቅቱ የነበሩ ሲነግሩን፤ ከአንዱ ታጋይ ጋር ስላልተጣጣመ ሽጉጥ መዘዘበት፡፡ ሽጉጥ መዝዞ ከመድረክ ውረድ ይለዋል። እሱ “አልወርድም፤ እኔ የመንግስት ምክር ቤት አባል ነኝ” አለ፡፡ እዚህም እንዲህ አይነት ፈተና ገጥሞታል። ከእርሱ ጋር የነበሩት የኦሞቲክ አባላትን ሰብስበው አሰሯቸው፡፡ ማታ ቤት መጥቶ ‹‹ይህ ነገር አላማረኝም፤ መሄዴ ነው›› አለኝ፡፡ እኔም ሶዶ ድረስ ሸኘሁት፡፡ ከምሽቱ 5 ሰአት ስንደርስ፣ ኬላ ጠባቂዎች አቆሙንና ወደ ወላይታ ፖሊስ ጣቢያ አደረሱን፡፡ ጠዋት ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ በሕዝብ ትራንስፖርት ተሳፍሮ ተጓዘ። ሻሸመኔ ላይ መኪና ቀይሮ፣ አዲስ አበባ በሰላም መግባቱን ሰማሁ፡፡ አዝማሚያው ጥሩ ስላልነበረ የደረሰበትን ሁኔታ በወቅቱ ፕሬዚደንት ለነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ሪፖርት አቅርቦ፣ በ1984 ዓ.ም በሕዳር ወር ጀርመን ተጓዘ፡፡ ከ25 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ፣ ሚያዚያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም አፈር ቀመሰ፡፡ መጽሐፉ ላይ እንዳለው ነው የሆነው፤ ‹‹አገሬን እወድ ነበር፤እንዳልመለስ ድልድዩ ተሰበረ”  
“ወ/ሮ አሰገደች ወንድሙን “እመቤቴ” ነው የሚላት፤ እውነትም እመቤቱ ነች፡፡ እናቱም ነች፡፡ እኔ እራሴ በውል አውቃለሁ፡፡ ከአብራኩ ልጅ ከማፍራት ጀምሮ ለዘር ማብቃትን ጨምሮ፣ ለ10 ዓመታት ከስድስት ወራት፣እስር ቤት እለት ተእለት ትኩስ ምግብ ነበር የሚቀርብለት፡፡ አንድም ቀን ሳይጓደል ጠይቃዋለች፡፡ እሱ ሲታሰር ዓለማየሁን ነብሰ ጡር ነበረች፡፡ ይህ ልጅ ነው ለአቅመ አዳም ደርሶ የአባቱን አስከሬን ተረክቦ ለአገሩ ያበቃው፡፡ አሰገደች አይደለም ለእርሱ ለእኛ ለስጋ ዘመዶቹ ትልቅ ሰው ነች፡፡ ወ/ሮ አሰገደች ወንድሙ ክብር ይገባታል፡፡
“አቶ አሰፋ ጫቦን ከልጅነት እስከ እውቀት የሚያውቁት ወዳጆቹ፣ አብሮ አደጎቹ፣ የስራ ባልደረቦቹ፣ የቅርብ ጎደኞቹ ሀዘናችንን ተጋርተውናል። ባህር ማዶም አሜሪካን የሚገኙ ወገኖቻችን፤ አስከሬኑን በወግ ገንዘው፣ ለአገሩ አፈር እንዲበቃ አድርገዋል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ ወዳጅ ዘመዶች፤ አስከሬኑን ተቀብለው፣በሽኝቱ ላይ ከልብ አዝነው ሸኝተዋል፡፡ ጋሞ ውስጥ በአርባ ምንጭ ወይም ጨንቻ ይቀበራል ብለው በአገራችን ባህል ለመሸኘት በወግ ተዘጋጅተው ነበር፤ ይሁንና ትልቁ ነገር ለአገሩ አፈር መብቃቱ ስለሆነ፣ በሀዘናችን ላፅናኑን ሁሉ፣በዓለም ብድር መላሽ ያርገን፡፡››

Read 4592 times