Sunday, 11 June 2017 00:00

እንኳንስ ነጠላ አግኝታ ዱሮም ዘዋሪ እግር አላት

Written by 
Rate this item
(10 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ክንዱ ላይ ክርኑን በጣም ያመውና ለጓደኛው “.ምን ባደርግ ይሻለኛል?..” ይልና ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም “..አንድ ዋሻ ውስጥ የሚኖር አዋቂ ሰው አለ፡፡ እሱ ጋ ሄደህ ችግርህን ብታስረዳው መፍትሔ ይፈልግልሃል..” አለው፡፡
“ስንት ያስከፍለኛል?”
“አስር ብር ብቻ፡፡”
“ምን ምን ዓይነት ምርመራ ያደርግልኛል?” ሲል ጠየቀ ታማሚው፡፡
“የሽንት ምርመራ ብቻ ነው የሚያደርግልህ፡፡ ዋሻው በራፍ ላይ በዕቃ ሽንትህን ታስቀምጣለህ፡፡ እሱ ይደግምበታል፡፡ ይመሰጥበታል፡፡ ከዚያ መድኃኒቱን ይነግርሃል፡፡ አለቀ፡፡”
ታማሚው ጓደኛው እንዳለው ዋሻው ደጃፍ ላይ ሽንቱን በዕቃ ያኖርና አብሮ አስር ብር ያስቀምጣል፡፡
በሚቀጥለው ቀን ወደ ዋሻው ደጃፍ ሲሄድ አንድ ማስታወሻ ተጽፎለት ያገኛል፡፡ እንዲህ
.. በሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ምክንያት ክንድህ ላይ ክርንህን ተጎድተሃል፡፡ ስለዚህ ክንድህን ለብ ያለ ውኃ ውስጥ ከተህ ታቆየዋለህ፡፡ ከባድ ዕቃ አታንሳ፡፡ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይሻልሃል ..
ታማሚው ማታ ቤቱ ገብቶ ነገሩን ሲያስበው፤ “የገዛ ጓደኛዬ ቢሆንስ ማስታወሻውን የጻፈው? ከዚያ አስር ብሬን ወስዶ አታሎኝ ቢሆንስ?” ደጋግሞ አሰበበትና በሚቀጥለው ቀን ወደ ዋሻው ደጃፍ ይሄዳል፡፡ አሁን ግን የራሱን የሽንት ዕቃ ሳይሆን የሚስቱንና የወንድ ልጁን የሽንት ምርመራ ናሙና፣ የውሻውን ፀጉርና የቧምቧ ውሃ ደባልቆ፤ በአንድ ዕቃ ዋሻው ደጃፍ ላይ ከአስር ብር ጋር ያስቀምጣል፡፡
ከዚያም ወደ ጓደኛው ይሄድና እንደገና ወደ ዋሻው ደጃፍ ሄዶ፣ የሽንት ናሙና በትልቅ ብልቃጥ እንዳስቀመጠ ይነግረዋል፡፡ ጓደኛውም፤ “አሁን ደግሞ ለምን አስቀመጥክ?”. ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
“ጤንነት አይሰማኝምና እንዳለፈው ጊዜ መፍትሔ እንዲሰጠኝ ፈልጌ ነው” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም፤ “ጥሩ፡፡ እንግዲያው ነገ ሄደህ የምርመራውን መልስ ካወቅህ በኋላ እናወራለን..” ብሎት ይለያያሉ፡፡
በነጋታው ታማሚው ሰው ወደ ዋሻው ደጃፍ ሲሄድ እንደጠበቀው ሌላ ማስታወሻ ያገኛል፡፡ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ፡- .. “የቧምቧህ ውሃ በጣም ወፍራምና ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያቀጥነውና የሚያሳሳው ኬሚካል ግዛ፡፡
ውሻህ የሚያሳክክ ቅንቅን አለበት፡፡ ስለዚህ ቪታሚን ገዝተህ ስጠው፡፡ ወንድ ልጅህ የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቂ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አባዜ እንዲላቀቅ ወደ ማገገሚያ ማዕከል ወስደህ ለተወሰነ ጊዜ እዚያ እንዲቆይ አድርገው፡፡ ሚስትህ አርግዛለች፡፡ ያውም መንታ ልጆች ነው ያረገዘችው፡፡ ልጆቹ ግን ያንተ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ጠበቃ ግዛ፡፡ እንዲህ ስትጠራጠርና በራስህ ስትቀልድ የክርንህ ህመም እየባሰብህ ነው የሚሄደው፡”
*    *    *
በአጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ መኖርና ኮስተር ብሎ ጉዳይን አለመጨበጥ ሌላ ጉድ ያሰማል፡፡ ..አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል.. እንዲሉ፡፡
በአጠራጣሪ ዓለም እየኖርን ዕቅዶች ስናወጣ፣ ዕቅዶችም አጠራጣሪ ይሆናሉ፡፡ ለዚያውም ነገን በማናውቅበት ዓለም፡፡ ውዲ አለን የተባለው ኮሜዲያን “..ሰው ሲያቅድ እግዚሃር ይስቃል..” (when man plans God laughs እንዲል) ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አነስታይን ደግሞ “በተጨባጭ ዓለም ውስጥ እየኖረ ..ዕውነትና ዕውቀት ላይ ፍርድ ሰጪ ዳኛ ነኝ የሚል ሰው፤ መርከቡ፤ አማልክቱ ሲስቁ ትንኮታኮታለች.”. ይለናል፡፡ ማንም ፍፁም ነኝ አይበል ነው ነገሩ፡፡ በገዢና በተገዢ መካከል ያለው ግንኙነት ፍፁምና ንፁህ ስምምነትና መተማመን መሆን አለበት ብሎ ግትር ማለት ቢያዳግትም፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይ ..እናቱ የሞተችበትም፣ እናቱ ወንዝ የወረደችበትም እኩል የሚያለቅስበት አገር.. ከሆነ አለመተማመንና መጠራጠር የታከለበት እንደሆነ በቡሃ ላይ ቆረቆር ይሆናል፡፡ ከዚህ ይሰውረን፡፡
ቲ ኤስ ኢሊየት ያለንን አለመርሳት ነው ፡- Oh my soul…be prepared for him Who knows how to ask questions ..ነብሴ ሆይ  ተዘጋጂ አደራ አውጪኝ ከዛ ጣጣ  ጥያቄ መጠየቅ የሚችል ሲመጣ.. እንደማለት ነው፡፡)
ዛሬ በሀገራችን ስለተጠያቂነት ብዙ ይነገራል፡፡ ከዚህ ተነጣጥሎ የማይታይ ግን ቸል የተባለው ጉዳይ  ..ጠያቂውስ ማነው?.. የሚለው ነው፡፡ ታሪክ፣ ጊዜና ህዝብ ናቸው ቢባል መልሱን ይጠቀልለዋል፡፡ እንጠየቃለን ብለ አለመስጋት ማናለብኝን ያስከትላል፡፡ ማናለብኝ ደሞ ኢ - ዲሞክራሲያዊና ኢ- ፍትሐዊ ነው፡፡
ጥርጣሬ አገር ጐጂ እክል ነው፡፡ እርስ በርስ አለመተማመንና ኑሮን አለማመን ያስከትላልና፡፡ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም መረጋጋትን ያጫጫል፡፡ የሩሲያው መሪ ጆሴፍ ስታሊን፤ የጥርጣሬ መናኸሪያ ነበር ይባላል። ሁሉንም ሰው ሌባና አጭበርባሪ፤ ሁሉንም ሰው ክፉና መጥፎ አድርጐ የማየት ባህሪ ነበረው፡፡ ሁሉን በመጥፎ ስለሚፈርድም ራሱን ጥሩ አድርጐ ይደመድማል፡፡ መጥፎዎቹ ሁሉ በእኔ ላይ ይነሳሉ የሚል ጥርጣሬ ይወርረዋል፡፡ ስለዚህም ብዙ ሰው ላይ ግፍ እንዲፈጽም ይገደዳል፡፡ ፀረ - ዲሞክራሲ ተግባራቱ በይፋ ታይተዋል፡፡ ሩሲያ ለሆነችው ሁሉ ትልቅ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡
አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤  ..ዕድገት ማለት ለውጥ ማለት ነው፡፡ ለውጥ ቢያዋጣም ባያዋጣም ደፍሮ መግባትን ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት ከሚታወቀው በመነሳት ወደማይታወቀው ዕመር ብሎ እንደመግባት ነው.. ለውጥ ለማምጣት አያሌ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስዋዕቶችን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው ለውጥ በተግባር እንጂ በአፍ አይገባም፤ የሚባለው፡፡ በተጨባጭ ከየት ተነስተን የት ደርሰናል? የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ የትምህርት ጉዳይ፣ የጤና ጉዳይ፣ የፍትህ ጉዳይ፣ የግንባታ ጉዳይ፣ የንግድና የግብር ጉዳይ፣ የዚህ ሁሉ ድምር የኑሮ ጉዳይ የት ደርሷል መባል አለበት፡፡
ጭቦ አትናገሩ ይላሉ አበው፡፡ ነገ በራሳችሁ ይደርስባችኋል ለማለት ነው፡፡
የሌለውን አለ፣ ያላደገውን አድጓል፣ የደረቀውን አልደረቀም በማለት ልንከላከለው ብንሞክር ..ሆድን በጐመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል.. ነው ውጤቱ፡፡ የዕውነቱ ለት ማነከሳችን ይታያልና። በሀገራችን በተደጋጋሚ የምናየው ሌላው አባዜ ተቻችሎ አለመኖር ነው፡፡ አለመቻቻልን ለመሸፈን የምናደርገው ጥረትም ሌላው ተጨማሪ አባዜ ነው፡፡ እኔ ፃድቅ ነኝ ለማለት ሌላውን መኮነን የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ተግባብቶ ሳይጠላለፉ መኖር የሚያቅተውም ለዚህ ነው፡፡
ሔንሪ ቫን ዳይክ እንዲህ ይለናል፤ ..ኤደን ገነት ዳግመኛ ብትሰጠን እንኳ በትክክል አንኖርም፣ ተስማምተን አንዝናናባትም ወይም ለዘለዓለም አንቆይባትም.. ይህ አባባል በእኛም ሳይሠራ አይቀርም፡፡ እንዲህ ኢኮኖሚያችን ቆርቁዞ፣ አስከፊ ድርቅ መትቶን፣ የኑሮ ውድነት ናጥጦብን ቀርቶ ..ለምለሟን..፣ ..የዳቦ ቅርጫቷን..፣ ..የአፍሪካ ኩራቷን.. ኢትዮጵያን ብናገኝ በትክክል አንኖርባትም፣ ተስማምተን አንዝናናባትም፤ አንቻቻልባትም እንደማለት ነው፡፡
በታሪክ እንደሚነገረው፤ ታሊያርድ የተባለው የፈረንሳይ ዲፕሎማት በየስብሰባው ላይ “..ቢዝነስ የምትሠሩ ሰዎች እጃችሁ ንፁህ መሆን አለበት..” ይል ነበር አሉ፡፡ ንፁህ ያልነበረው እጅ ግን የሱ የራሱ ነው። ያንን በመናገሩ ሌሎች ንፁህ እንዳልሆኑ ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ አለመተማመንን ያሰፍናል፡፡ መፈራራትንና ሥጋትን ያሰለጥናል፡፡ ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ እሱ ግን ከጥርጣሬው በላይ ተረጋግቶ ይቀመጣል፡፡ በጥርጣሬ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለፍርሃት፣ ላለመረጋጋት፣ በዕቅድ ላለመኖር፣ ለሙስና፣ ምሬትን ለማመቅ፣ በኑሮ ተስፋ ለመቁረጥ እጅግ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ይሄን ሁኔታ የሚፈጥሩ ወገኖች ደሞ በአጋጣሚው ለመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ወትሮም ሰበብ ይፈልጋሉና ባገኙት ቀዳዳ ይገለገላሉ፡፡ ሙስናቸውን ያስፋፋሉ፡፡ ያለገንዘብ ንቅንቅ የማይሉ ቢሮክራቶችን ይፈለፍላሉ፡፡ እየቦረበሩ ስለ ድል ያወራሉ፡፡ በአሸበረቁ ፖሊሲዎች ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ ብዙ ግብረ አበሮችን በመረብ ያደራጃሉ፡፡ የማይቀለበስ ደረጃ ደረስን ይላሉ፤ ከአጋጣሚ አጋጣሚን ይወልዳሉ፡፡ እንኳንስ ነጠላ አግኝታ ዱሮም ዘዋሪ እግር አላት ይሏል እኒህ ናቸው፡፡

Read 6831 times