Print this page
Monday, 12 June 2017 06:27

ዜና እረፍት

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(5 votes)

    ….ሚሊዮን በማለዳ ከእንቅልፉ ነቃ፤ ባለቤቱንና ልጁን እንዳይቀሰቅስ ተጠንቅቆ ኮሽታ ሣያሰማ ከቤት ወጣ፡፡ ……. የመርካቶን ታክሲ ያዘ፤ ዛሬ የሚፈጽማቸውን የዕቃ ግዢ ሰነዶች ገረፍ! ገረፍ! አድርጎ አያቸው፡፡ በጣና ገበያ ቁልቁል ወደ ሲዳሞ ተራ ወረደ፡፡ ገበያተኛው እንደጨረባ ተስካር ይንጫጫሉ፡፡ አማርኛ - ትግርኛ - ኦሮምኛ - ሲዳምኛ - ጉራጊኛ - አገው - አደሬ…… እንደ ባቢሎን ግንበኞች የተደበላለቀ የቋንቋ ቅይጥ ጉራማይሌ…… የባህል ትርዒት የሚታይበት መድረክ - በመርካቶ። አንዱ ሽቅብ ሌላው ቁልቁል ከሚግተለተል የሰው ጅረት መሀል ዓይናለም መኮንንን አያት፤ እሷም አይታው ኖሮ ወደ እሱ መጣች፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጡ፤ ተያይዘው ወደ ምዕራብ ሆቴል ገቡ፤ ሻይ ቡና እያሉ ስላለፉት አመታት ወግ ያዙ……  
2004 ዓ.ም
ከዓይናለም መኮንን ጋር በአንዲት ገጠር ቀመሥ የደቡብ ከተማ፣ አንድ መሥሪያ ቤት ሰርተዋል - ከ5 ዓመት በፊት፡፡ …ልክ እንዳያት አፈቀራት። ቅፅበታዊ ፍቅር፡፡ የዓይን ፍቅር፡፡ የመጀመሪያ ፍቅር። የሚያቃጥል ፍቅር፡፡…. ዓይናለም ከሥራዋ ውጭ ውሏዋ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በመንፈሣዊ ህይወት ጠልቃ ዓለምን የዘነጋች ብዕፅት፡፡ ፅርዕት። ንፅሕት። እንከን አልባ ጭምት፣ ህፀፅ አልባ እንደ ወርቅ ንጥር ሰብዕና የታደለች፡፡ ፍቅር የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ነውና! ሚሊዮን ፍቅር የያዘው ከዚህች እንደ ቅድስት ከምትያይ ለየት ያለች ሴት ነበር፡፡... ዓይናለም ምድር ላይ ምን ጉድ! እንደሚገጥመው ሳያውቅ ከሰማይ እንደ ወረደ መላዕክ ድንግርግር ይላት ነበር፤ አንዳንዴ፡፡….. ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰውን መሸሽ ጀመረች፤ ቤቷ መሽጋ ሰነበተች፡፡ ሚሊዮን በውስጡ የሚከላከለውን የፍቅር ረመጥ ተንፍሶ መገላገልን መረጠ፡፡ ወደ አይናለም ቤት አመራ፤በሩን አንኳኳ፤አይናለም በሩን ለአመል ከፈት አድርጋ ግር ብሏት አፈጠጠችበት፡፡ “ሰላም ነህ ሚሊዮን ግባ”
በርጩማው ላይ አረፍ አለ፡፡… የቤት እቃዎቿንና ልብሶቿን እየሸካከፈች ነበር፡፡
“ሰሞኑን የት ጠፋሽ፤ መ/ቤትም አላየሁሽም ?”
አይናለም እየተንገፈገፈች፤ “በቃኝ! ከዚህ በሴሰኝነት ከተጨማለቀች ነውረኛ ከተማ መውጣት አለብኝ…” ሰንካላው የፍቅሩ ደመራ አመድ ሆነ!
...በማግስቱ ወፍ ሳይንጫጫ ከተማዋን ለቃ ወጣች….
አያሌ ሀሣቦች ብልጭ ድርግም እያሉ ወደ አእምሮው እየመጡ ያስጨነቁት ጀመር፤ የቅድሥቷ ሴት በሃጢያት አድፋ የተጨማለቀችውን ከተማ ለቆ መውጣትን ተከትሎ፣ ምን መርገምት ይወረድ ይሆን? ሎጥ ትዝ አለው፡፡ ፃድቁ ሎጥ፡፡ በሀጢያት የዘቀጠችውን ከተማ ለቆ በወጣበት ቅፅበት ዶግ አመድ የሆነችው ሶዶምና ጎሞራ፡፡ አይናለም ጥላት የሄደችው ከተማ ዶግ አመድ መሆን አይደለም አንዲት የበረዶ ፍሬ ጠብ! ሳትል ዓመታት አለፉ። ከወር በኋላ ሚሊዮን ወደ አዲስ አበባ በዝውውር ገባ። ዓይናለምን ላፉት 5 ዓመታት አየኋት የሚል ሰው አላጋጠመውም፤ ደብዛዋ ጠፋ፡፡ የት ገብታ ይሆን? ከልበ-ጠማማው ትውልድ…… ዓለምን ንቃ ገዳም ገብታ ይሆን ወይስ እንደ ኤልያስ በሰረገላ ወደ ሰማይ አርጋ እያለ በሀሳቡ ወደ ፀርአርያም፣ በምናቡ ወደ ሰማይ ሰማያት ቢመጥቅም፤ እነሆ መሀል መርካቶ ከፊት ለፊቱ እየተቁለጨለጨች ነው…. አይናለም መኮንን፡፡ የህይወት ምፁት የሚባለው ይህን መሰሉ ገጠመኝ ይሆን እንዴ! …… ሚሊዮን ቡናውን ፉት! እያለ “ሕይወት …ኑሮ ... ትዳር ያዝሽ ?” ዓይናለም ጥያቄው አላስደሰታትም፤ ምላሽ አልሰጠችውም፡፡ ከአላስፈላጊ ጥያቄ መቆጠብ እንዳለበት እያውጠነጠነ፤
“… መርካቶ ምን እግር ጣለሽ?”
አክስቷ ለህክምና ከክፍለሀገር እሷ ዘንድ እንዳረፉ…. ለህክምና ብሯን ማሟጠጧን… ከመ/ቤት የተበደረችውም ገንዘብ በማለቁ 2,000 ብር ለመድሃኒት መግዥያ ለማግኘት መርካቶ የቅርብ ዘመዷ ጋር ብትመጣም እንዳልተሳካላት …. አጫወተችው፡፡….ሚሊዮን ሳያንገራግር 2000 ብር ቆጥሮ ሰጣት፡፡
…..ከምዕራብ ሆቴል ወጡ፤ ከፋርማሲ ለአክስቷ መድሃኒት ገዛች፤ ሚሊዮን ሊለያት አልፈለገም፤ እሷም ተረድታዋለች…..
“ለምን አክስቴን አታያትም፤ ባለውለታዋ ነህ እኮ!” …. ታክሲ ይዘው ወደ መኖሪያ ቤቷ አመሩ፡፡
….አክስትየው ተዳክመዋል፤ አምላክ የህይወታቸውን ሻማ እፍ ሊለው የተቃረበ ይመስላል። ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዷቸዋል፡፡ አይናለም እንዳትቀሰቅሳቸው ተጠንቅቃ፣ ሚሊዮንን አስከትላ ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ክፍሏ ሶስት በአራት ስፋት ሲኖራት፣ በጨለማ ተውጣለች፡፡
 “መስኮቱን ልክፈተው? ጨለማ ውስጥ ነን...” ጠየቀ ሚሊዮን፡፡
“…አትክፈተው! የተረገመ ብርሃን ማየት አልፈልግም... ጨለማውን እመርጣለሁ...ከተፈጠርኩባት ንጥረ ነገር አንዱ ይመስለኛል፤ ጨለማው…”
ሚሊዮን በግርምት አፈጠጠባት፡፡ በአይናለም ህይወት ውስጥ ማንም የማያውቀው አንድ ሚስጢር አለ፤ ወይንም የለም፡፡
“….ታስታውሻለሽ ከተማውን ልትለቂ  በመጨረሻዋ ምሽት ቤትሽ መጥቼ…”
“….አስታውሳለሁ እንዴት እረሳለሁ”
“…አመጣጤ የፍቅሬን ጣር ልተነፍሥልሽ ነበር፤ አሁን ምን ቀረ ባዶ ትዝታ!” ከአፉ ቀበል አድርጋ፤
“አዎ ባዶ ትዝታ!! ሁሉንም ነገር አራግፌ ባዶነት ላይ ነኝ፤ እያንዳንዱ የራሱን ጥግ መያዝ አለበት ከእጣ ፈንታው ጋር!”
“ፍቅር የዕጣ ፋንታ ጉዳይ ነው፤ የነፍስ ለነፍስ መሳሳብ ትስስር” ሚሊዮን ቃላት ትርጉመ - ቢስ ሆነውበት ፀጥ አለ፡፡ እሷም ፀጥ፡፡ ጭጭ፡፡ ከመቃብር የከበደ ፀጥታ፡፡ የሚቀፍ የዝምታ አዚም፡፡
….ድንገት አንዳች ምስጢራዊ የስበት ሀይል፣ ጣዝማ መሣይ ማር አካሏ ላይ አጣበቀው፤ ልጥፍ አለችበት፡፡ ትንፋሻቸው በቁማቸው እንደ ወላፈን አቃጠላቸው፡፡ የወይን ዘለላ ከንፈሯን መጠጠ፡፡ ምስጢራዊ የሴት ልጅ ውበት፡፡ ምትሀታዊ ውበት፡፡ የህልም አለም ውበት፡፡ ……ልብሶቻቸው በራሣቸው ሀይል ከገላዎቻቸው ሸሽተው እየተንሣፈፉ ወለሉ ላይ ወደቁ- ኮሽታ ሣያሰሙ … እርቃን የቀረ ጠንበለል ገላዋን ተሸክሞ አልጋው ላይ አሣረፈው….ጡቶቿ ማህል ሟሟ… ወደ ልዩ የተረት ዓለም…..ወደ ወደ ሰማየ ሰማያት በሩካቤ ሠረገላ መጠቁ…. ከዋክብት ከሰው፤ እንደ አበባ ረገፉ… ጨረቃ ዱንቡል’ቃ የደም እንባ አነባች - ብር አምባር ሰበረሎዎ!! ላቡ እንደ ጤዛ ኮለል ብሎ ወረደ:: እንባዋ ገባር ወንዝ ሆኖ ተመመ:: እንባ:: ላብ:: ደም፡፡ ፍቅር፡፡ ቀና ብላ አየችው - ከአይኖቿ የሚወጣ ጭስ አልባ የበቀል ብናኞች ያየ መሰለው፡፡ ጨለምለም ሲል ቤቱ ደረሰ፡፡
“ወይኔ እግሬን ጠዘጠዘኝ---” እያለች ታቃስታለች - ባለቤቱ አዜብ፡፡ እግሯ ጤነኛ የሆነበትን ጊዜ አያስታውስም፡፡ የ4 ዓመቱ ናታን ሮጦ ተጠመጠመበት፤ ሚሊዮን ሽምቅቅ አለ፡፡
“…ፊትህ ላይ የሆነ ነገር ይነበባል፤ ገንዘብ ቢኖረኝ ፊርማቶሪ ቀጥሬ ውሎህን እከታተል ነበር ፡፡”………
 በዝምታ ወደ ሻወር ቤት ገባ፤ ተለቃልቆ ወጣ፡፡
አዜብ በሽሙጥ፤ “ትዳር በቆየ ቁጥር እንደ ወይንጠጅ አይጣፍጥም፤ እንዲያውም እጅ እጅ ይላል፤ የሆነ ነገርማ አለ!” ብላ ከት ብላ ሳቀች። አዜብ የስድብ ሎሬት.. የአሽሙር ሞዛርት ናት። እንዴት ጠረጠረች፤ ሴቶች ለየት ያሉ ፍጡራን ናቸው ሲል አውጠነጠነ። ሀሳቡ ወደ አይናለም፤ ወደዚያ ምትሀታዊ የተረት ዓለም የሚመስል የአልጋ ላይ ጨዋታ፡፡
…ወጣ ብሎ ለአይናለም ደወለላት፤ የፍቅር አባዜውን እንደ ባለቅኔ አሽጎ ደጎደገው፡፡
“…የህይወቴ አብሪ ኮከብ ነሽ…. ነገ መ/ቤትሽ እመጣለሁ፤ እነዚያን የብርሃን ፀዳል የሚረጩ አንፀባራቂ አይኖችሽን ማየት አለብኝ፤ ከዛም ይዤሽ ወደ አለም ዳርቻ ”
“…እጠብቅሃለሁ ሚሊ! ሶስተኛ ፎቅ ቢሮ       ቁጥር 8…”
….በማግስቱ ከመስሪያ ቤቱ ለ3 ቀን ፈቃድ ጠይቆ ወጣ፤ ከአይናለም ጋር  የጫጉላ ሽርሽር ዓይነት ጉዞ ማድረግ አለበት፡፡….. ወደ 5፡00 ሰዓት ላይ ዓይናለም የምትሰራበት መ/ቤት ደረሰ፡፡ ወደ ግቢው ዘለቀ። ደጋግሞ ቢደውልላትም ስልኳ ዝግ ነበር፤ ወደ 3ተኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 8 ለመሄድ ሊፍት ለመጠበቅ ቆም አለ፣ አይኖቹን እንደ ዘበት ማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ጣል አደረገ …. ያነበበውን በፍፁም አላመነም፤ በህልም ይሁን በቅዥት ዓለም ድንግርግር አለው፡፡ እግሩ እየተንቀጠቀጠ ዓይኖቹን ወደ ማስታወቂያው ቢልክም፣ የሚያየው ሁሉ በስስ ደመና የተሸፈነ አብስትራክት ሥዕል ሆነበት፡፡ ዳግም ማስታወቂያው ላይ አፈጠጠ፤ ፊደላቱ ዚግዛግ እየመቱ አጥበረበሩት … እንደ ምንም ራሱን አረጋግቶ መራሩን እውነት አነበበ….
…….የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ  የዓይናለም መኮንን ስርዓተ ቀብር ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በየካ ሚካኤል ይፈፀማል፡፡
ሶሻል ኮሚቴው
“….እንዴት ሆና ! ” ሲል አንባረቀ ……….
“ግን ሆነ ! ……” ከገባበት ድንዛዜ አልወጣም፤ በመሀል ብንን ብሎ ሰዓቱን አየ፤ 5፡15፡፡ ቀብሩ 6፡00 ሰዓት ነው፡፡ ወደ ቤት ከመሄድ በቀጥታ ስርዓተ ቀብሩ ወደሚፈጸምበት…. የመገናኛን ታክሲ ያዘ፤ ሾላ ወረደ፤ ወደ የካ ሚካኤል በፈጣን እርምጃ ገሰገሰ፡፡ ሁለት የለቀስተኛ ቡድን በተለየ አቅጣጫ አስከሬን ይዞ እየሄደ ደረሰ፡፡ ወደ የትኛው እንደሚሄድ ተደናግሮት ቆም አለ፤ በጥድፊያ የሚራመድን ጎልማሳ ከተል ብሎ፤ “የዓይናለም ….” ብሎ ሣይጨርስ ሰውዬው “የአይናለም መኮንን ያኛው” ብሎ ጠቆመው፡፡ በሶምሶማ ሩጫ ለቀስተኛው ጋር ተቀላቀለ፤ አፈር ሲመለስ ደረሰ - ወዕንበል ፍጻሜ፡፡ ስቅሥቅ ብሎ አነባ፤ የመለየት ጣር እንደ ካራ ውስጡን ዘለዘለው። ፍፁም ባዶ ኦና፡፡ የተሰበረ ልብ፡፡ የተሰበረ ቅስም። ከቤተ ክርስቲያን ቅፅር ለመውጣት ከሚግተለተል ለቀስተኛ መሀል ሚሊዮን በዝግታ እየተራመደ ሳለ፣ ከኋላው አንድ ሰው በጣቶቹ ትከሻውን ነካ አደረገው፤ ዘወር ብሎ ባየው ምትሀታዊ ጉድ ክው አለ፤ ብርክ ያዘው፡፡ መልአከ ሞት ፀአረ መንፈስ… የሌሊቷ ንግስት… አይኖቿ እየተሽከረከሩ…. ፈገግ ብላ እጆቿን ዘረጋችለት፡፡ ማምለጥ አለበት ግን አንዲትም ጋት መላወስ አልቻለም፤ እግሩ ውሃ ሆነበት፤ በቆመበት ተሽመደመደ፡፡
…ከወረደበት መብረቃዊ ድንጋጤ መለስ ብሎ በግርምት አፈጠጠ - ዓይናለም መኮንን ላይ፡፡ እጆቹን ይዛ ከለቀስተኛው መሀል እያወጣችው፤ “…እባክህን ተረጋጋ! .... ያረፈችው ወ/ሮ ዓይናለም መኮንን የተባለች ነባር ሰራተኛ ነች፤ በስመ ሞክሼ የተፈጠረ ሰይጣናዊ እኩይ ገጠመኝ….” 

Read 4706 times