Monday, 12 June 2017 06:35

ኮንሰርቱን የማይመጥኑ አዘጋጆች!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

      • ታዳሚውን ለግፊያ፣ ለስርቆት፣ ለእንግልትና ለዱላ ዳርገውታል
                        • አቀንቃኙ ዲሚያን፤ ኢትዮጵያን ሲያወድሳትና ሲያሞጋግሳት አምሽቷል
                      
      በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቦብ ማርሌ የመጨረሻ ልጅ የዲሚያን ጁኒየር ጎንግ ማርሌይ  ‹‹ዋን ላቭ›› የሙዚቃ ኮንሰርት፤ ባለፈው ማክሰኞ ብዙዎቹን የሙዚቃ አድናቂዎችና ታዳሚዎች በእጅጉ አበሳጭቷል፡፡ በእርግጥ እንደ ሌላ ጊዜው ብስጭቱ፤ ከኮንሰርቱ አቀንቃኞች ጋር ፈጽሞ የተገናኘ አይደለም፡፡ ሙሉ በሙሉ በኮንሰርቱ አዘጋጆች ትከሻ ላይ የሚያርፍ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ቀደም ኮንሰርቶችና የተለያዩ የጥበብ ዝግጅቶች ሰዓት ባለማክበርና በሌሎች ጉዳዮች ሲወቀሱ ቆይተዋል፡፡ ይሔኛው ግን ከበድ ያለ ነው፡፡
 የኮንሰርቱ አዘጋጆች፡- ዛክ ፕሮዳክሽን፣ ሲግማ ኢንተርቴይመንትና አውሮራ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ሲሆኑ የጊዮን በሮች በ11፡00 ይከፈታሉ ብለው ባስታወቁት መሰረት፤ታዳሚው እውነት መስሎት፣ ከ11፡30 ጀምሮ ነበር ሰልፍ የያዘው፡፡ ሰልፉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሳም  ናኒ ህንፃን አልፎ እስከ ጊዮን መድሀኒት ቤት ደርሶ ነበር፡፡
ምንም እንኳን ሰልፉ በሁለት ረድፍ የነበረ ቢሆንም ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ ነገሩ ወደለየለት ትርምስና የእርስ በእርስ ግፊያ ተቀይሮ፣ ፌደራል ፖሊስ የሀይል እርምጃ ለመውሰድ ተገዶ ነበር። በዚህም ብዙዎች የፖሊስ ዱላ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ ሲሮጥ ወድቀው የተረጋገጡም ነበሩ። ለትርምሱ ዋነኛ መንስኤ የነበረው ደግሞ ትኬት ቀድሞ የገዛውም ያልገዛውም አብሮ መሰለፉ ሲሆን ትኬት ቀድመው የገዙትንና ያልገዙትን ለብቻ ማስተናገድ ቢቻል ኖሮ ችግሩ አይከሰትም ነበር ብለውናል- አንዳንድ ታዳሚዎች፡፡ በር ላይ የነበረው ውጥንቅጥ ያላማራቸው መደበኛውንም ሆነ ቪአይፒ ትኬት የገዙ በርካታ ታዳሚዎችም፤‹‹ጎመን በጤና›› እያሉ ወደ የቤታቸው ሲመለሱ ታዝበናል፡፡  
አዘጋጆቹ ይህን ያህል ሰው በኮንሰርቱ ላይ ይታደማል ብለው ባለመገመታቸው አንድም ጨርሶ ለማስተናገድ አልተዘጋጁም አሊያም ሙሉ በሙሉ ተዘናግተው ነበር ይላሉ - ኮንሰርቱን ለመታደም ለረዥም ሰዓት ወረፋ ይዘው ከነበሩ ታዳሚዎች አንደኛው በሰጡት አስተያየት፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ትኬት ቀድመው ገዝተውም በግፊያው የተንገላቱ እንዲሁም የፌደራል ፖሊስን ዱላ ቀምሰው፣ ኮንሰርቱ ላይ ሳይታደሙ የቀሩ በርካቶች መኖራቸው ነው፡፡ የአዘጋጆቹን የብቃት ማነስ በግልጽ ያሳየው ትርምስና ግፊያ እስከ ምሽቱ 5፡00 ድረስ መፍትሄ አልተበጀለትም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በኮንሰርቱ ላይ ከዲሚያን ቀድመው ያቀነቀኑትን ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች፡- ጆኒ ራጋንና ዘለቀ ገሰሰን ለመታደም የቻሉት ቀድመው የገቡ ጥቂት ዕድለኞች ብቻ ነበሩ፡፡ ገንዘብ ተከፍሎም ዕድለኛነትን የሚጠይቅ ግራ አጋቢ ኮንሰርት!
በመሰላቸትና ተስፋ በመቁረጥ ወደየ ቤታቸው የተመለሱት ተመልሰው፤ኮንሰርቱን ከ10 ሺ የማያንሱ ሰዎች ታድመውት ነበር፡፡ የሚበዙትም የሬጌ ሙዚቃ አድናቂዎችና አፍቃሪዎች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ታዳሚዎች ስሜታቸውን የሚገልፁበት፣ የሚግባቡበትና ሀሴት የሚያደርጉበት መንገድ የተጠናና ተመሳሳይ ይመስል ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ለሬጌ ሙዚቃ ሩቅ የሆነ ሰውን ባይተዋር ያደርጋል፡፡
የዚህ ኮንሰርት ድምቀት የጀመረው ዲሚያን ልክ ወደ መድረክ ሲወጣ ነው፡፡ ያን ጊዜ ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ የሚጮሁ፣ የሚዘልሉ፣ ራሳቸውን የሳቱ ሁሉ ነበሩ፡፡ አቀንቃኙም የዋዛ አልነበረም፡፡ መድረኩን የተቆጣጠረበት ጥበብና ሀይል አስገራሚ ነበር፡፡ የመድረክ አጋፋሪው፤ ‹‹አንድነት ----- ፍቅር ይስፈን፣ በብሔርና በዘር መከፋፈል ይጥፋ፤ ኢትዮጵያ ቅድስት አገር ናት›› የሚል መልዕክት ሲያስተላልፍ፤ ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ በፉጨትና በጩኸት ሲቀበለው ነበር፡፡ ዲሚያንም በየዘፈኑ መሀል ኢትዮጵያን ደጋግሞ ሲጠራ፤ሲያወዳድስ ነው ያመሸው፡፡ ስለ አንድነትና ፍቅር ሰብኳል፡፡ ኢትዮጵያ ቅዱስ አገር መሆኗን፣ የህዝቧ አንድነትና ፍቅር፤ ለእሱና ለመሰሎቹ ሃይል እንደሆነ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡  
በዚህ ኮንሰርት ላይ የጃንሆይን ፎቶግራፍ በፊቱም በኋላውም የያዘ ባንዲራና የሞአንበሳ ፎቶ በሁለቱም በኩል ያለበት ሌላ ተጨማሪ ባንዲራ ያለተቀናቃኝ ሲውለበለቡ አምሽተዋል፡፡
ከቅርብ ሰዎች ለማጣራት እንደሞከርነው፤ የሞአንበሳ ምስል ያለበት ባንዲራ ሲያውለበልብ ያመሸው፤መድረክ ላይ ካሉት የባንዱ አባላት አንዱ ሲሆን ዲሚያን የትም ዓለም ላይ ኮንሰርት ሲያቀርብ ተመሳሳይ ባንዲራ እያውለበለበ፣ ባንዱን የሚያጅብና ለአቀንቃኙም እንደ ቅርብ ጠባቂው የሚያገለግል ነው፡፡
ዲሚያን በምሽቱ ኮንሰርት ወደ 14 የሚጠጉ የራሱን ስራዎች በላቀ ሀይልና ብቃት አቀንቅኗል። ከነዚህም መካከል ‹‹አፌይር ኦፍ ኤ ኸርት››፣ ‹‹ፔሸንስ››፣ ‹‹ላቭ ኤንድ ኢኒቲ››፣ ‹‹ሚኔም ጁኒየር ጋንግ››፣ ‹‹ሄይ ገርል››፣ ‹‹ሜዲቴሽን››፣“ኤክስትራ”፣ “ቢዩቲፉል”፣ “ሮድ ቱ ዛየን”፣ “ዌል ካም ቱ ጀምሮክ” የተሰኙት ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡ በተለይ “ሮድ ቱ ዛየን” በሚለው ዘፈኑ ላይ ዲሚያን፤ታዳሚው አንድ ነገር እንዲያደርግ አዝዞ ነበር፡፡ ላይተር ያለው ላይተሩን፣ ላይተር የሌለው ስልኩን ያብራ አለ። ስልክ የሌለው ደግሞ እጆቹን እንዲያውለበልብ አዘዘ፡፡ ይሄኔ ህዝቡ ላይተሩንና ስልኩን በማብራት አካባቢውን ደመራ አስመሰለው፡፡ ከፍተኛ ጩኸትና ፉጨት ዙሪያ ገባውን አናወጠው፡፡ ይሄኔ “ፈታሾች” ተመቻቸው፡፡ ታዳሚው በስሜት እጁን ከፍ አድርጎ ሲያውለበልብ፣ የብዙዎች ኪስና ቦርሳ እንደ ጉድ ተበረበረ፡፡ ገንዘብ፣ሞባይል፣ የኪስ ቦርሳ፣ የመኪና ቁልፍ፣ የሴቶች ቦርሳና ጫማ ----- ምን ያልተሰረቀ አለ፡፡ ብዙዎች የነቁት ግን ዘፈኑ ሲጠናቀቅ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የጃሉድ ኮንሰርት ጊዜም ‹‹ሬጌ ዱብ ዱብ›› ሲዘፈን፣ ሌቦች ብዙ ሞባይል ስልኮችን “ዱብ ዱብ” አድርገዋል ተብሏል፡፡  
ዲሚያን ታዳሚው ሁሉ ለምን መብራት እንዲያበራ አዘዘ ስንል ለሬጌ ሙዚቃ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠይቀን ነበር፡፡ የዲሚያን “ሮድ ቱ ዛየን” መልዕክቱ፡- ፂዮን የሚላት ቅድስት አገር ኢትዮጵያን የሚመለከት በመሆኑ፤ልክ ቤተ ክርስቲያን ሲኬድ ሰዎች ጧፍ እንደሚያበሩት ሁሉ ወደ ኢትዮጵያም ሲኬድ ለቅድስናዋ ጧፍ እናብራ የሚለውን መንፈሳዊ እሳቤ ለማስተሳሰር ነው፤ ብለውናል፡፡
አቀንቃኙ በራሱ ዘፈኖች ብቻ ሳይወሰን የአባቱን “ጌት አፕ ስታንዳፕ”፣ “ኩድዩ ቢላቭድ”፣ “አፍሪካ ዩናይት” እና ሌሎችንም የዘፈነ ሲሆን በ1፡50 የመድረክ ቆይታው፣በአጠቃላይ ከ20 በላይ ዘፈኖችን፣በልዩ ብቃት ተጫውቶ፣ ልክ ከሌሊቱ 7፡55 ላይ መድረኩን ለቅቆ ወርዷል፡፡ በሰልፍ፣ በግፊያና በፖሊስ ዱላ ሲንገላታ ያመሸው የኮንሰርቱ ታዳሚም፤ ቢያንስ በዲሚያን አንጀት አርስ ዘፈኖች እንደተካሰና እንደረካ መገመት አያዳግትም፡፡
ዲሚያን ማርሌይ፤ በኮንሰርቱ ማግስት ረቡዕ እለት፣ ኢምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኘውን የአባቱን ሀውልት እንደጎበኘና በጉብኝቱ ወቅት አባቱን አስታውሶ ሲያለቅስ እንደነበረ የኮንሰርቱ አዘጋጆች ገልፀውልናል፡፡ የዚያኑ ዕለት ማታም ወደ አገሩ እንደተመለሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል፤ወደ ማተሚያ ቤት ከመግባታችን ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ በደረሰን መረጃ መሰረት፤ ትኬት አስቀድመው ገዝተው በተፈጠረው ትርምስ፣ በኮንሰርቱ ላይ ሳይታደሙ የቀሩ ሙዚቃ አድናቂዎች ገንዘባቸው ተመላሽ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡ መረጃውን ከኮንሰርቱ አዘጋጆች ማረጋገጥ ግን አልተቻለም፡፡

Read 2727 times