Tuesday, 13 June 2017 00:00

ሞዛምቢክ ራሰ-በራ ዜጎቿን ከግድያ ጥቃት እንዲጠነቀቁ አሳሰበች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ከሳምንታት በፊት በ2 ራሰ-በራዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል
     ራሰ-በራ የሆኑ ሞዛምቢካውያን የባዕድ አምልኮ ተከታዮች በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል ያስጠነቀቀው የአገሪቱ መንግስት፤ ራሰ-በራዎች ራሳቸውን ከጥቃት ለማዳን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሞዛምቢክ የባዕድ አምልኮ ተከታዮች የሆኑ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ እነዚህ የባዕድ አምልኮ ተከታዮች ራሰ-በራ በሆኑ ሰዎች የራስ ቅል ውስጥ ወርቅ ይገኛል ብለው በማመን ግድያ እንደሚፈጽሙባቸው የአገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
የባዕድ አምልኮ ተከታዮች የሆኑ ግለሰቦች ዛምቤዚያ በተባለቺው የአገሪቱ ግዛት ከሳምንታት በፊት በሁለት ራሰ-በራ ሞዛምቢካውያን ላይ አሰቃቂ የግድያ ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ መሰል ጥቃቶች በቀጣይም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የአገሪቱ ፖሊስ ሰሞኑን ማስጠንቀቁን ገልጧል፡፡
ከሳምንታት በፊት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ሰለባ የሆነው አንደኛው ራሰ-በራ፣ በባዕድ አምልኮ ተከታዮች አንገቱ ተቀልቶና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቹም ተቆራርጠው መገኘታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ድርጊቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ቤት እንደሚገኙም አስረድቷል፡፡
ግድያውን በመፈጸማቸው በእስር ላይ የሚገኙት ሁለት ሞዛምቢካውያን ወጣቶች ለፖሊስ በሰጡት ቃል፣ የገደሏቸውን ራሰ-በራዎች የሰውነት ክፍሎች ለጠንቋዮች ለመሸጥ አቅደው እንደነበር መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ጠንቋዮቹም የሰውነት ክፍሎቹን በመቀመም ለደምበኞቻቸው ሃብት የሚያትረፈርፍ መድሃኒት እንደሚሰሩበት መግለጻቸውን አክሎ አብራርቷል፡፡

Read 2455 times