Sunday, 18 June 2017 00:00

ዜድቲኢ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ የፈጠራ ማዕከል ሊገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     5G የቴሌኮም አገልግሎት አቀርባለሁ ብሏል

      የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ በኢትዮጵያ፤ የቴሌኮም ምርምርና ፈጠራ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር መፈራረሙን አስታወቀ። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለው የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከሉ፤ አዳዲስ የቴሌኮሚኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማራጮችን እዚሁ ሀገር ቤት በመፍጠር ለተጠቃሚዎች ያቀርባል ተብሏል፡፡
የምርምርና ፈጠራ ተግባር ከሚያከናውንባቸው ዘርፎች መካከልም በገመድ አልባ ኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነቶች፣ የኔትዎርክ ሽፋንና ጥራትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ምርምርና ፈጠራ እንዲሁም በሀገሪቱ የተዘረጋውን የቴሌኮም መዋቅር የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከሎች ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል የተባለውና በ3 ሺህ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው የፈጠራ ማዕከሉ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ያፈልቃል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ኩባንያው የ5ኛው ትውልድ (5G) የቴሌኮም አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማቅረብና ለማስፋፋት እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡

Read 1339 times