Sunday, 18 June 2017 00:00

ምርጫ ቦርድ፤ ህጋዊነትን ባላሟሉ ፓርቲዎች ላይ ማብራሪያ እንዲሠጥ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “ህጋዊዎቹ ባልተለዩበት የሚደረግ ድርድር የህገ መንግስት ጥሠት ያስከትላል”

      የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ መሰፈርት አሟልተው እየተንቀሣቀሱ ነው ያላቸውን 5 ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ማንነት በዝርዝር እንዲያሣውቅ መኢአድ እና ሠማያዊ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
ቦርዱ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ 22 ፓርቲዎችና በክልል ከሚንቀሳቀሱ 40 ፓርቲዎች መካከል በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሠረት፤ ህጋዊ መስፈርት ያሟሉት 5 ሃገር አቀፍና 5 ክልላዊ ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
ሆኖም ቦርዱ የትኞቹ ፓርቲዎች ህጋዊነቱን እንዳሟሉና እንዳላሟሉ በዝርዝር የገለፀው ነገር የለም፡፡
ይሄን ተከትሎ ሠማያዊ እና መኢአድ፤ የትኞቹ ፓርቲዎች ህጋዊ እንደሆኑ አለማሣወቁ በወደፊት እንቅስቃሴያችን ላይ አሣሣቢ ችግር ይፈጥርብናል” በሚል ቦርዱ ማብራሪያ እንዲሠጣቸው የጠየቀ ሲሆን፤ ህጋዊዎቹ ህጋዊ ካልሆኑት ሣይለዩ ከገዥ ፓርቲ ጋር የሚደረገው ድርድርም ትርጉም እንደሌለው መኢአድ ለአደራዳሪ ቦርድ ፅ/ቤትና ለምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
“ህጋዊ መስፈርት አሟልተው ካልተገኙ ፓርቲዎች ጋር ለድርድር መቀመጥ የህገ መንግስት ጥሠት የሚያስከትልና የህዝብን ጥያቄ የሚያዳፍን በመሆኑ በአፋጣኝ ምርጫ ቦርድ ማብሪያ እንዲሠጥበት መኢአድ በደብዳቤው ጠይቋል፡፡
ማብራሪያው ባልተሠጠበትና ህጋዊች ተለይተው ባልተገለፁበት ሁኔታ ድርድሩን ማካሄድ እንደማይቻልም መኢአድ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሠጥ ላለፉት ሁለት ሣምንታት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡

Read 2084 times