Monday, 19 June 2017 08:59

አቶ በላይነህ ክንዴ በኢትዮጵያ ቀዳሚው ቢሊዬነር ሆነዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

    • ፎርብስ 5 የኢትዮጵያ ቢሊዬነሮችን ይፋ አድርጓል
                      • ከ50ሚ - 60ሚ.ዶላር በላይ ሃብት አላቸው ተብሏል                        

      በየዓመቱ የዓለም ባለፀጎችን የሃብት መጠን እያጠና ደረጃቸውን ይፋ የሚያደርገው “ፎርብስ” መፅሔት፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 5 የኢትዮጵያ ቢሊየነሮችን የሃብት መጠንና ደረጃ ከተሰማሩባቸው የንግድ ዘርፎች ጋር አውጥቷል፡፡   
ከ5ቱ የኢትዮጵያ ቁንጮ ባለጸጎች በዋናነት በቅባት እህሎች ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ በላይነህ ክንዴ ከ60 ሚ.ዶላር በላይ በማስመዝገብ ቀዳሚው ቢሊዬነር ሊሆኑ በቅተዋል፡፡ በፎርብስ 5 የኢትዮጵያ ቢሊዬነሮች ዝርዝር ውስጥ አንዲት ሴት ባለጸጋም ተካትተዋል፡፡ በ5ኛ ደረጃ ላይ የሰፈሩት ወ/ሮ አኪኮ ስዩም አምባዬ፤ ኦርቼድ ቢዝነስ ግሩፕ በተሰኘው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያቸው፤ ከ50 ሚ.በላይ ሃብት አካብተዋል ብሏል - ፎርብስ፡፡
በቁንጮ ቢሊዬነርነት የተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን የሃብት ምንጭ፡- የግብርና ውጤቶች፣ የምግብ ማቀነባበር፣ የኮንስትራክሽን ሥራ፣ የነዳጅና ሃይል አቅርቦት እንዲሁም የሸቀጦች አከፋፋይነት የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሆኑን የጠቆመው የፎርብስ መረጃ፤ በዚህም ግለሠቦቹ 50 ሚሊዮን ዶላርና ከዚያ በላይ ሃብት ሰብስበዋል ብሏል፡፡ በፎርብስ ሪፖርት፤ ከ1ኛ-5ኛ ደረጃ የተሰጣቸው ባለጸጎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡   
1ኛ- አቶ በላይነህ ክንዴ
የሃብት ምንጫቸው የግብርና ውጤት የሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ንግድ ሲሆን “በላይነህ ክንዴ አስመጪ እና ላኪ” በተሰኘው ኩባንያቸው አማካይነት በአመዛኙ በቅባት እህሎች ንግድ ላይ ተሠማርተው፣ በ2016 እ.ኤ.አ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡ በ1997 ዓ.ም የተመሠረተው ኩባንያቸው፤ በኢትዮጵያ ግዙፉ የግብርና ውጤቶች ንግድ ድርጅት ነው ተብሏል፡፡
የቅባት እህሎችን ብቻ ወደ ውጭ በመላክ ስራውን የጀመረው ኩባንያቸው፤ ዛሬ ለውዝና ጣፋጭ ፍራፍሬዎችን ጭምር ለውጭ ገበያ እንደሚልክ ፎርብስ ጠቁሟል፡፡ ከተመሠረተ ከ12 አመት በላይ ያስቆጠረው ኩባንያው፤ በትራንስፖርት ዘርፍም ተሠማርቶ ከመቶ በላይ የፈሳሽና ደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ባለቤት መሆን ችሏል ተብሏል፡፡  
የበላይነህ  ክንዴ አስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ፤ ላለፉት  15 ዓመታት የቅባት እህሎችን ወደተለያዩ አገራት በመላክ፣ ለአገራቸው  የውጭ ምንዛሪ  በማስገኘት ረገድ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ለዚህ አስተዋጽኦዋቸውም ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተበረከተላቸውን የማበረታቻ ዋንጫን ጨምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ ተሸልመዋል - የሰሊጥ ምርት ወደ የተለያዩ የውጭ አገራት በመላክ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ በማስገኘት፡፡  
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ድርጅታቸው ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል። በ2007 ዓ.ም ብቻ ሰሊጥን ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ ከ 47 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገኘ ሲሆን፤ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ በጥቅሉ 60 ሚሊዮን ዶላር ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል ተብሏል።  
በቅርቡ የንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያ የሆነው በላይነህ ክንዴ፤ በአሁኑ ወቅት ሦስተኛውን ባለ ኮከብ ሆቴል፣ ከአዲስ አበባ በ549 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባህር ዳር ከተማ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የግንባታው ሥራ አፈጻጸም 60 በመቶ መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኩባንያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ ስለ ሆቴሉ ሲገልጹ፤» እየተገነባ ያለው ሆቴል አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የሚይዛቸውን አገልግሎቶች በሙሉ ያካተተ ነው፤ ሆቴሉ 200 የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት የባህር ዳር ከተማ በዓባይ ዳር እስከ ጢስ ዓባይ ድረስ ለመገንባት ካቀደው ናይል ማራቶን የመሮጫ ትራክ ጋር የተጣጣመ ነው፡፡» ብለዋል፡፡
እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የሆቴል ግንባታው አልቆ፣ ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ ሆቴሉ በአጠቃላይ 800 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ግንባታውን የሆቴሉ ባለቤት እህት ኩባንያ፣ በላይነህ ክንዴ ኮንስትራክሽን እያካሄደው ነው፡፡
ከዚህ ግዙፍ ሆቴል በተጨማሪ በላይነህ ክንዴ፤በአዲስ አበባና በአዳማ የሁለት ሆቴሎች ባለቤት ነው፡፡ የመንግሥት የነበረውን አዳማ ራስ ሆቴልን በ41 ሚሊዮን ብር፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን ኢትዮጵያ ሆቴል በ94 ሚሊዮን ብር በመግዛት፤ በሁለቱም ሆቴሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች ቀርጿል፡፡ አዳማ ራስ ሆቴልንና ኢትዮጵያ ሆቴልን ከመንግሥት እንደተረከበ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ በማደስ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በአዳማ ራስ ሆቴል ላይ ተጨማሪ 175 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ፣ የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ እየተገነቡ ያሉት ሁለት ባለ ስድስትና ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅም አዳማ ራስ ተጨማሪ መቶ መኝታ ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን ደረጃውም ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ይሆናል፤ ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባውን ኢትዮጵያ ሆቴል በማፍረስም፣ ባለ 63 ፎቅ ግዙፍ ሆቴል የመገንባት ዕቅድ አላቸው - ኢትዮጰያዊው ቢሊዬነር በላይነህ ክንዴ፡፡
2ኛ. አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ
የሃብት ምንጫቸው በዋናነት የነዳጅ ንግድ ሲሆን አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ የአምቦ የማዕድን ውሃ ኩባንያ ሊቀመንበርና ባለድርሻም ናቸው፡፡ ባለድርሻ የሆኑበት አምቦ ውሃ፤ በሃገሪቱ የማዕድን ውሃ ገበያውን የሚመራ ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን ባለሃብቱ ከዚህ ኩባንያም ዳጎስ ያለ ገቢ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ የተባለውን “ሣውዝ ዌስት ኢነርጂ” የተሠኘ ኩባንያ አቋቁመው፣ በጅግጅጋ አካባቢ ከ350 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ባለው ቦታ ላይ በነዳጅ ማውጣትና ፍለጋ ላይ ተሠማርተዋል ተብሏል። ፎርብስ፤ የባለሃብቱን የሃብት መጠን በአሃዝ አልገለፀም፡፡
3ኛ- አቶ ቡዛየሁ ተ/ቢዘኑ
የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናቸው የተገለጸው አቶ ቡዛየሁ፤ የሃብት ምንጫቸው የተለያዩ ንግዶች ናቸው ተብሏል፡፡ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ኩባንያዎች በመሪነት እንደሚቀመጥ የጠቆመው ፎርብስ፤ ኩባንያው የተሰማራባቸውን ዘርፎች ሲገልጽ፡- የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ አላቂ እቃዎች ምርት፣ የሻይ ቅጠል ልማት፣ የማተሚያ ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርት፣ ሪል እስቴት፣ የሲሚንቶ ማምረትና የከሰል ድንጋይ ማዕድን ማውጣት----መሆኑን ጠቁሟል፡፡
4ኛ. አቶ ከተማ ከበደ
በሙስና ተጠርጥረው የፍርድ ሂደታቸውን ላለፉት 3 ዓመታት ገደማ በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ከተማ ከበደ፤ በበርካታ የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን የሀብት መጠናቸው ከ50 ሚሊዮን ዶላር እንደሚልቅ ተጠቁሟል፡፡
አቶ ከተማ ከበደ ኬኬ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በተሰኘው ኩባንያቸው፣ በዋናነት ብርድልብስ እያመረቱ በመላው አፍሪካና በሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ፈጥረዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በቃጫ፣ ድርና ማግ ምርት እንዲሁም በከባድ ማሽነሪዎች ንግድ ላይ መሰማራታቸውን የጠቀሰው ፎርብስ፤ የማዕድን ማውጫ መሳሪያዎችንም ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገቡ ጠቁሟል፡፡ ባለሃብቱ በኮንስትራክሽን፣ በመንገድ ግንባታና ጥናት የተሰማሩ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚታወቁ የቡና፣ ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ላኪ ነጋዴዎች አንዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
5ኛ. ወ/ሮ አኪኮ ስዩም አምባዬ
ዋነኛ የሀብት ምንጫቸው የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑን የጠቆመው ፎርብስ፤ በኢትዮጵያ ካሉ ሴት ባለሀብቶች በቁንጮነት ተጠቃሽ ናቸው ብሏል፡፡ ኦርቼድ ቢዝነስ ግሩፕ የተሰኘው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያቸው በመንገድ ግንባታ፣ በኮንስትራክሽን ቁሳቁሶች አቅርቦት እንዲሁም የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችን በማከራየት ስራ ላይ ተሰማርቶ ባለሀብቷን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲያካብቱ አድርጓል፡፡

Read 11276 times