Monday, 19 June 2017 08:58

ኢትዮጵያ በእንግዳ ተቀባይነት በዓለም አንደኛ ተባለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገው ታዋቂው አለማቀፍ የቱሪስት መመሪያ መፅሐፍት አዘጋጅ “ራፍ ጋይድ” በድረ ገፁ ባሰባሰበው የሀገር ጎብኚዎች ድምፅ፤ በእንግዳ አቀባበላቸው ለቱሪስቶች ከተመቹ የዓለም ሀገራት፣ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ደረጃ ማግኘቷን አስታውቋል፡፡
የድረ ገጹ ተከታታይ ሀገር ጎብኝዎች በቆይታቸው የተደሰቱባቸውንና በእንግዳ አቀባበላቸው የረኩባቸውን ሀገራት በኢንተርኔት እንዲመርጡ በተመቻቸው እድል መሰረት ነው ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ተመራጭ ሆናለች የተባለው፡፡
ሀገሪቱ ማራኪ መልክአ ምድር ያላት፣ ቅኝ ያልተገዛችና በሺህ አመታት የሚቆጠር ጥንታዊ ታሪክና ቅርስ ያላት መሆኗ ከእንግዳ አቀባበሏ ጎን ለጎን ቱሪስቶችን እንዳስደሰቷቸው ጠቁሟል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሽን ቦርድ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “እንግዳ ተቀባይነት ወትሮም የኢትዮጵያውያን ባህል ነው፤ ይህ ባህላችን አለማቀፍ እውቅና አግኝቶ በቱሪስቶች ተመስክሮ በዓለም መመረጣችን አስደስቶኛል” ብለዋል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በድረ ገፁ ባሰፈረው መግለጫ፡፡
በእንግዳ ተቀባይነት ሀገሪቱ መመረጧም ቱሪዝምን ለማስፋፋት ለተያዘው እቅድ በእጅጉ አጋዥ እንደሚሆንና እድሉንም ቱሪስቶችን ለመሳብ ሀገሪቱ ልትጠቀምበት እንደሚገባ አቶ ተወልደ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 5230 times