Monday, 19 June 2017 09:06

ዜጎች ጓዳ ያልደረሰው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት (የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገት ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት- ዓለም ባንክ
                 • ፈጣን ዕድገቱ ዜጎችን ከድህነት አላላቀም - የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን
                 • የውጭ ባንኮች መግባት ለካፒታል አቅም ወሳኝ ነው - ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ
                       
     የዓለም ባንክ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው የሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን አስታውቋል - አጠቃላይ አማካይ የኢኮኖሚ እድገት ምጣኔዋ 8.3 መመዝገቡንም በመጥቀስ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት የበላይነቱም ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ተሸጋግሯል ብሏል - ሪፖርቱ።
በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያን በመከተል ታንዛኒያ በ7.2 በመቶ፣ አይቮሪኮስት በ6.8 በመቶ እንዲሁም ሴኔጋል በ6.8 በመቶ ፈጣን እድገት ያስመዘግባሉ ተብሏል፡፡
ከዓለም ባንክ  አስቀድሞ የሀገራትን የልማት ደረጃ ሪፖርት ያወጣው የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙ ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቁሞ፤ ዜጎች ግን ከእድገቱ ትርጉም ያለው ጥቅም አላገኙም ብሏል። በአሃዝ እየተመዘገበ ያለው እድገት በእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ አላመጣም ያለው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ ችግሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን  እያደጉ ነው በሚባሉት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር መሆኑን ጠቅሷል፡፡  
የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም፤ አጠቃላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱ በሚባለው መጠን እየተመዘገበ መሆኑን ይቀበላሉ፤ ነገር ግን የዜጎችን ህይወት መሰረታዊ በሚባል ደረጃ መለወጥ አለመቻሉን የተለያዩ ማስረጃዎች በማቅረብ ይሞግታሉ፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፤ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ መሰረቱ የመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድም የመንግስት ፖሊሲ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ ለወደፊት ያልተነኩ የሀገሪቱ ሀብቶችን አውጥቶ ለመጠቀም፣ የሚገነቡ የመንገድም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ዕድገቱ የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት ላይ ቀጥተኛ ውጤት ሊኖረው የሚችለው መሰረተ ልማቶች ተሟልተው፣ ሌሎች ስራዎችን በእነዚህ ተጠቅሞ መስራት ሲቻል እንደሆነም ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡
“በእቅድና በስልት ደረጃ መንግስት ያወጣቸው ፖሊሲዎች በእርግጥም ይህቺን ሀገር የሚቀይሩ ናቸው” የሚሉት ምሁሩ፤ “ራስን በምግብ መቻል ላይ ግን ከፍተኛ ክፍተት አለ›› ይላሉ፡፡ በምግብ ራስን ለመቻል የተቀመጠው አቅጣጫ ግልፅ አለመሆኑንና እየተመዘገበ ነው ከሚባለው እድገት አንፃርም አብሮ ሊሄድ እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡
የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት በኢኮኖሚ እድገቱ መለወጥ አለበት ሲባል የትምህርትና የጤና ተደራሽ መሆንና አጠቃላይ የኑሮ መሻሻል መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፤ በእነዚህ ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በመንግስት በኩል መልካም አቅጣጫ ተዘርግቷል ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍተው በመቶ ሺዎች ከየዩኒቨርስቲው ተመርቀው ቢወጡም የስራ እድል እንደ ልብ አለመኖሩ በዜጎች እድገት ላይ እንደ ትልቅ ጉድለት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ የግል ዘርፉ አለማደጉ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል - የኢኮኖሚ ምሁሩ፡፡
በከተሞች አካባቢ በዜጎች በኩል ከፍተኛ የስራ መነሣሣትና የስራ ፈጠራ ፍላጎት መኖሩን የጠቆሙት ዶ/ሩ፤ ይሄን የሚደግፍ የፋይናንስ ተቋምና የካፒታል እጥረት መኖሩ እንቅፋት ሆኗል፤ በሃገሪቱ እድገት ልክ ዜጎች ወደፊት እንዳይራመዱም ተግዳሮት ብለዋል፡፡
ይሄንን ካፒታል መንግስት ማፈላለግ አለበት፤ በተለይ ችግሩን ለመቅረፍ የውጭ ሃገር ባንኮች በኢትዮጵያ ገብተው እንዲሠሩ መፍቀድ ይገባል ያሉት ምሁሩ፤ ጎረቤት ጅቡቲ በአቅሟ 8 የውጭ ሃገር ባንኮች ወደ ሃገሯ አስገብታ ለውጥ ማምጣቷን እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡ “ሰፋፊ እርሻዎችና ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት ከተፈለገም የእነዚህ ባንኮች ወደ ሃገር ቤት መግባት ወሳኝ ነው፤ ፈጣን እድገቱም እንዲቀጥል የካፒታልና የፋይናንስ አቅም መፈጠር አለበት” ብለዋል፡፡
“ቻይና 6 ሚሊዮን ሠዎችን በአጭር ጊዜ ከድህነት ማላቀቅ የቻለችው የካፒታልና የፋይናንስ ስርአቷን በመዋቅራዊ ለውጥ በማሻሻሏ ነው፤ መንግስት የያዛቸው ግዙፍ የመሠረት ልማቶች ሣይቀሩ በግል ባለሃብቶች የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፤ እንደ ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉ ኩባንያዎችም በግል ባለሃብትና በመንግስት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ናይጄሪያ የቴሌኮም ዘርፏን ለግል ባለሃብቶች በማስተላለፍ ከፍተኛ ትርፍና ውጤት ማምጣቷንም በምሣሌነት ጠቅሰው፤ እየተመዘገበ ያለው እድገት እንዲቀጥል፣ ሃገሪቱ እንደተባለው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ በአጭር ጊዜ እንድትሰለፍ እንዲህ ያሉ ሪፎርሞችን ማካሄድ እንደሚገባ ዶ/ሩ ይመክራሉ፡፡
“እያንዳንዱ ዜጋ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ዕድገቱ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩ ጋር ሲጣጣም ነው” ያሉት ሌላው ፖለቲከኛና የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ሙሼ ሰሙ፤ ለህዝቡ ትርጉም በሚሰጥ ደረጃ እድገት መንፀባረቅ የሚችለውም እነ ናይጄሪያ የደረሱበት ደረጃ ላይ ሲደረስ ነው ይላሉ፡፡
በሰሞኑ የአለም ባንክ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ እድገት ኬንያን በልጣለች ቢባልም በእያንዳንዱ ዜጋ የነፍስ ወከፍ ገቢ ኬንያ በእጥፍ ብልጫ አላት በማለትም ሁለቱን አገራት በቁጥር ተንትነዋል፡፡  
“በዓለም ባንክ ሪፖርት ላይ፣ 92 ሚሊዮን ህዝብ አላት የተባለችው ኢትዮጵያ፤ የዜጎቿ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ 848 ዶላር ወይም 18 ሺህ 650 ብር ገደማ ሆኗል ይላል፡፡ በአንፃሩ 47 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ እንዳላት የተገመተችው ኬንያ፤ የአንድ ዜጋዋ የነፍስ ወከፍ አማካይ ገቢ 1 ሺህ 650 ዶላር ወይም 36ሺህ 300 ብር መሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ዘንድሮ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ በ78.3 ቢሊዮን ዶላር እንዳደገ፣ የኬንያ ደግሞ በ3 ቢሊዮን ገደማ ከኢትዮጵያ አንሶ 75 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተጠቁሟል፡፡” ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ቢሆንም ለአጠቃላይ ህዝቧ ሲካፈል መጠኑ አነስተኛ ነው፤ በዜጎች ህይወት ላይ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት ያልቻለውም በዚህ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡  
እያንዳንዱ ዜጋ ከአጠቃላይ እድገቱ እንደ ኬንያውያን መልካም ትሩፋት ለማግኘት ወይም ከኬንያውያን ለመስተካከል አሁን ካለው መጠን እጥፍ እድገት መምጣት አለበት ያሉት አቶ ሙሼ፤ ይሄ ደግሞ በአጭር ጊዜ የማይታሰብ ነው ብለዋል። የናይጄሪያ ኢኮኖሚ በዓመት የሚያንቀሳቅሰው 534 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፤ የናይጄሪያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ለህዝቡ ሲካፈል 2 ሺህ 990 ዶላር እንደሚደርስና ኢትዮጵያም ከእነሱ ተርታ ለመሰለፍ በትጋት መሰራት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
የኢኮኖሚ እድገቱ በአመዛኙ በብድርና በእርዳታ የመጣ መሆኑን በመጠቆምም፤ እድገቱ በፈጣንነቱ እንዲቀጥል ከተፈለገም ብድርና እርዳታው አሁንም ሊቀጥል ይገባል ይላሉ፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ የተሰማራችበት የመሰረተ ልማት ግንባታም ለእድገቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጨምረው ገልጠዋል፡፡  
“አሁን ለእድገቱ ግብርናው ተጠቃሽ ቢሆንም በቀጣይ ኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፉ ከተለያዩ ማነቆዎች ተላቆ የሚያድግበት መንገድ ካልተመቻቸ የእድገቱ ቀጣይነት ላይ አጠራጣሪ ሁኔታ ይፈጠራል፤ ለዚህ ደግሞ መንግስት የፋይናንስ ችግሮችን በመቅረፍ ላይ ጠንክሮ መስራት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል - አቶ ሙሼ፡፡
ትንንሽ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት የገለፁት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ችግሯን የምትፈታባቸው መንገዶችም መቀየስ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ፡፡ “የውጪ ንግዱ መቀነሱ ሀገሪቱ ብድር ለመክፈል ያላትን አቅም ይፈታተናታል፤እ ነዚህ ችግሮች የሚቀጥሉ ከሆነ ደግሞ ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ አጠራጣሪ ይሆናል፡፡” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው በፈጣን አሃዝ ተመዝግቧል ከተባለው ኢኮኖሚ ለምን ተጠቃሚ አልሆነም ለሚለው ጥያቄ፤ እድገትና ልማትን ለይቶ ማየት ይገባል ያሉት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሃቢስ ጌታቸው፤ የዜጎች የኑሮ ለውጥን ለመለካት የእድገት ሪፖርት ድርሻው አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ልማት ውስጥ የሚካተቱት የትምህርት ተደራሽነት፣ የጤና ተጠባቂነት፣ የመጠለያና ምግብ ተደራሽነት፣ የሠብአዊ መብት አጠቃቀም የመሳሰሉት እንደሆኑ የሚያስረዱት ባለሙያው፤ እነዚህ የልማት መለኪያዎች ያለ እድገት መምጣት እንደማይችሉ ይገልጻሉ፡፡ ከእድገት በፊት ልማቶችን ለማስቀደም የሚፈልጉ ሃገሮች እምብዛም ውጤታማ መሆን አልቻሉም የሚሉት ባለሙያው፤ በልማት ብቻ ዜጎችን ዝም ብሎ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ መሞከር ውጤት እንደማያመጣ ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ እድገት መኖሩ ግን ለቀጣዩ ጊዜ ጥሩ ነው ይላሉ፡፡ እድገቱ የሚፈጥራቸው ልማቶች ሠፊ ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ መሄዱ አይቀሬ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሃቢስ፤ የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣውም ያን ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
የመሠረተ ልማት ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ የሁለተኛው እድገት እቅዱ ለኢንዱስትሪ የሰጠው ትኩረት፣ መካከለኛ ገቢ ለመግባት ተስፋ ሰጪ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፤ በተቃራኒ ደግሞ ባለፈው አመት ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ተስፋውን ያደበዝዘዋል ይላሉ - ኢንቨስተሮች በቅድሚያ ሠላም ስለሚፈልጉ፣ መንግስት ለሠላም አበክሮ መስራት እንዳለበት በማሳሰብ፡፡
‹‹የኢኮኖሚ እድገት መኖሩን የሚጠቁሙ አስረጅዎች›› እንዳሉ የገለጹት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያና የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሠይፉ በበኩላቸው፤ እድገት ስለመኖሩ ጥርጥር ያለመኖሩን ያህል በህዝቡ ህይወት ላይ መሠረታዊ ለውጥ አለማምጣቱም መታወቅ አለበት ይላሉ፡፡
“በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት 7.8 ሚሊዮን ህዝብ የእለት ደራሽ እርዳታ ጠባቂ ሲሆን ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብም በሴፍቲኔት ውስጥ ነው፤ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ዕድገት እያስመዘገብን ነው ብሎ ከተገቢው በላይ መኩራራት፣ እነዚህ ተረጂ ዜጎችን ታሣቢ አለማድረግ ነው” ብለዋል፡፡ የእድገት ትኩረቱም ዜጎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አይደለም፤ ዜጎች በግለሰብ ደረጃ ስራ እንዲፈጥሩ የማያበረታታና እድል የማይሰጥ ነው ባይ ናቸው - አቶ ግርማ፡፡  
በአንዲት አገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሰላምና መረጋጋት ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፤ አንዱ ያለ አንዱ አይኖሩም፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹም በዚህ ይስማማሉ፡፡
ኢንቨስተሮች የአንድ ዓመት ሰላም ሳይሆን የ10 ዓመት የሀገሪቱን ሁኔታ ቅድሚያ ገምግመው፣ አስተማማኝነቱን አረጋግጠው፣ ከተመቻቸው ብቻ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንደሚኖራቸው የጠቀሱት አቶ ግርማ፤ ይሄን መንግስት በሚገባ ማስተዋል እንዳለበት አሳስበዋል - የሰላም አስተማማኝነት በኢንቨስትመንቱና በኢኮኖሚው ቀጣይነት ላይ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም፡፡  
የፖለቲካ መረጋጋትና ሰላም ለአስተማማኝ እድገት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው፤ ጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጁ ሀገር ለማረጋጋት ጠቃሚ ቢሆንም ውስን ጊዜ ያስፈልገዋል ይላሉ፡፡ “መንግስት በአመፁ ወቅት ወጣቱ በዋናነት ለምን ኢንቨስትመንቶችን ለማውደም ተነሳሳ፤የሚለውን በቅጡ መርምሮ፣ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይገባዋል” ሲሉም ምሁሩ አሳስበዋል፡፡

Read 2686 times