Monday, 19 June 2017 09:08

“ሁልሽም አለሽበት! ሁልሽም ጥፋት ሰርተሻል” - የጠ/ሚ ምላሽ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(7 votes)

   1.የፓርላማ አባላት ከማርስ እንደመጣ ቱሪስት ይመስላሉ
                   - አጠያየቃቸው። የሚንስትሮች ምላሽስ? የተሰላቸ አስጎብኚ ገለፃ ይመስላል!
                   • ‘ኤክስፖርት’ አላደገም። እንዲያውም፣ እየወረደ ነው። ምን ይሻላል? - (የፓርላማ አባል ጥያቄ)
                   • መፍትሄው፣ የኤክስፖርት ምርት በስፋት እንዲመረት ማድረግ ነው! – (የገንዘብ ሚኒስትር ምላሽ)
              2. (በዚህ ምላሽ የተቆጡ የፓርላማ አባላት ሳይኖሩ አይቀሩም። ሌላ ሚኒስትር ላይ ወረዱባቸው።
                  • ኤክስፖርት ለምን እንዳሽቆለቆለ በየአመቱ አሰልቺ ሰበብ ከመደርደር፣ ለምን መፍትሄ አትሰጡም? - (የፓርላማ አባል ጥያቄ)
                  • ሰሊጥ አምራች ቀነሰ፣ የዓለም ዋጋ ወረደ፣ ወርቅና ከብት በኮንትሮባንድ አለቀ... (የንግድ ሚኒስትር ምላሽ)
             3. በአላዋቂነት ወይም በአስመሳይነት የቁልቁለት ጉዞን ለመቀጠል ካልሆነ በቀር...
                  • መንግስት፣ ከመነሻው የቢዝነስ ስራ ውስጥ ሲገባ ነው፤ መናገር፣ መተቸትና ማስጠንቀቅ!
                  • ቢዝነስ ውስጥ፣ በኪሳራና በብክነት ሲጨማለቅ ብቻ መጮህ፣ ትርፉ መደናቆር ብቻ ይሆናል።
                  • መንግስት፣ በገንዘብ ህትመት ብርን አርክሶ የዶላርን ምንዛሬን ሲጨመድድ ነው፣ መተቸት!
                  • የዶላር ምንዛሬ ሳይስተካከል፣ ተዓምረኛ መፍትሄ እንዲፈጠር መጮህ፣ ከንዝንዝ አይዘልም!
                     
     ‘ማጋነን’ የአገራችን ባህል ቢሆንም፤ የከተማ ልማት ሚኒስቴር የማጋነን ልማድ፣ ‘ፍሬን የለቀቀ’ ነው። በየአመቱ ‘አዲስ ሪከርድ’ የሚሰብር አዲስ ሪፖርት ለፓርላማ ያቀርባል - የስራ እድሎችን በመፍጠር! እንደወትሮው፣ ዘንድሮም፣ 1.4 ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድሎች እንደተከፈቱ ገልጿል።
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የስራ እድሎችን እየፈጠረ፣ የኢትዮጵያ ከተሞችን በየዓመቱ ያጥለቀልቸዋል። በሰባት ዓመት ውስጥ፣ 14 ሚሊዮን የስራ እድል! “የሪፖርት ዓለም ከተሞች”፣ እንዲህ ናቸው - የስራ እድል ሞልቶ የተትረፈረፈባቸው።
ካለፉት አመታት ግን የዘንድሮው ሪፖርት ይሻላል። ትንሽ አደብ ለመግዛት ሞክሯል ማለት ይቻላል። ከ2 ሚሊዮን በታች ወርዶ አያውቅም ነበር። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው ሌላው ነገር...‘የ150 ሺ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው... ዘንድሮ ይጠናቀቃል’ የሚል ፉከራ ነው። ... ይሄውና አራት አመት አለፈ።
አንድ ሚሊዮን ቤት ፈላጊዎችን ከመዘገበ በኋላ፣  በየዓመቱ 100ሺ ቤቶችን እንደሚገነባ ሲዝት ታስታውሳላችሁ? ዛሬ ድምፁ ጠፍቷል። ከ1997 ዓ.ም እስከ ዘንድሮ ምን ያህል ቤቶችን ለነዋሪዎች እንዳስተላለፈ መመልከት ትችላላችሁ። በዓመት፣ ከ10 ሺ በላይ ቤቶችን ለነዋሪዎች ማስተላለፍ አልቻለም።
ከስራው በላይ አስር እጥፍ እያጋነነ ይናገራል ማለት ነው። 10 ሰርቶ፣ 100 ያወራል።
ግን፣ ሁሉንም ጥፋት፣ ሚኒስትሩ ላይ መጫን ተገቢ አይደለም። ሚኒስትሩ አዲስ ሹመኛ ናቸው፣ ገና አመት አልሞላቸውም። ግን፣ ቢሞላቸውምና አስር ዓመት ቢቆዩም እንኳ፣ ሚኒስትሩን ተጠያቂ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። የገጠማቸው ችግር፣ ቀላል አይደለም። ከስረመሰረቱ ካልተስተካከለ በቀር፣ መፍትሄ የለውም። እንዴት?
ያው! መንግስት ዘው ብሎ የቢዝነስና የግንባታ ስራ ውስጥ ሲገባ፤ ወይም ደግሞ “ብቸኛ የሲሚንቶ፣ የአርማታ፣ የመሬት አቅራቢ እሆንላችኋለሁ” እያለ... ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ሲያምረው፣... ከውድቀት አያመልጥም። ይሄ አከራካሪ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም።  በቲዎሪ እና በተግባር፣ ለአመታት በተደጋጋሚ የተከሰተና የተረጋገጠ እውነታ ነው። በከተማ ልማት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣ በስኳር ኮርፖሬሽንና በብረታብረት ኮርፖሬሽንም የሚታይ እውነታ ነው። በኢህአዴግ ዘመን ብቻ ሳይሆን በደርግ ዘመንም በሰፊው የተከሰተ እውነታም ነው። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ አገራት፣ የአለምን ግማሽ ሕዝብ ሲያደኸይ የነበረ ክስተት ነው።
ግን፣ ለምን? የኑሮና የቢዝነስ መሰረታዊ ሕግ፣ በስኬት ካልሆነ በሌላ በምን ሊመዘን ይችላል? ስኬቱ ደግሞ፣ በምርታማነት ይሰላል። በቀላል ምሳሌ ለመግለፅ ያህል፣ ከተዘራው ስንዴ ይልቅ፣ የሚታጨደው ስንዴ መብለጥ አለበት። ከወጪው ገቢው መብለጥና ትርፍ ማስገኘት ነው ስኬት! አለበለዚያ ኪሳራ ነው። ኪሳራ ደግሞ፣ ከዓመት ዓመት መቀጠል አይችልም። መቀጠል የሚፈልግ ሰው ቢኖር፣ ‘መንገዱ ጨርቅ አይሆንለትም’። ለነገሩ... የራሱ ጉዳይ ነው! የራሱን ሃብት ነው የሚያባክነው። ወደ ህሊናው ካልተመለሰ፣ ከስሮና ባክኖ ኪሱ ባዶ ሲቀር፣... ያኔ ያርፈዋል። መንግስትስ?...
መንግስት፣ በተፈጥሮው ከምርታማነት ስሌት፣ ከትርፍና ከኪሳራ ሚዛን ጋር የመጣላት ዝንባሌ አለው። የባቡር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ፣ ምን እንደተናገሩ አስታውሱ። የመንግስትን ባህርይ፣ በደንብ ገልፀውታል።
የመንግስት ቢዝነስ፤ በስሌት ሳይሆን በስሜትና በድፍረት!
የባቡር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ፣ በአደባባይ፣ ለዚያውም በፓርላማ ፊት ነው፣ ስለ መንግስት ባሕርይ በግላጭ የተናገሩት። የአዲስ አበባ የባቡር መስመር የተዘረጋው፣ በስሌት ሳይሆን በስሜት ነው። መንግስት ትርፍና ኪሳራን አላመዛዘነም። እንዲያውም፣ ትርፋማ እንደማይሆን እያወቀ ነው በድፍረት የገባበት ብለዋል ስራ አስኪያጁ። ባቡሩ እንደታሰበው በቀን 600ሺ ተሳፋሪዎችን ቢያመላልስ እንኳ፣ አትራፊ አይሆንም። ዛሬ ደግሞ እዩት።
በቀን ከ100ሺ ተሳፋሪዎችን ብቻ ያስተናግዳል። ለዚህ ለዚህማ፣ 100 አውቶቡሶችን ማሰማራት በቂ ይሆን ነበር። ለዚህ ነው እንዴ፣ ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የፈሰሰበት? ለዚህ ነው እንዴ፣ በከተማዋ መሃል አጥር ተዘርግቶ መሸጋገሪያ የጠፋው? ለመሆኑ፣ ለዚሁ የአዲስ አበባ ፕሮጀክት በብድር የመጣውን የውጭ እዳ እንዴት ሊመልስ ይችላል? ብድሩን ለመመለስ ይቅርና ወለዱን ብቻ ለመመለስም አይችልም። ያው ከዜጎች ታክስ ተሰብስቦ፣ በጀት ይመደብለት ይሆናላ። ግን፣ ታክስ ቢሰበሰብ እንኳ፣ ዶላርስ ከየት ይመጣል?
የስኳር ፕሮጀክቶች ላይ የሚታየው ችግርም ተመሳሳይ ነው፤ (የችግሩ ዓይነት ተመሳሳይ ነው። የችግሩ መጠን ግን፣ በ10 እጥፍ ይበልጣል)።
የመንግስት ፕሮጀክቶችን ስኬታማነት የሚሰብኩ እልፍ ዲስኩሮች ቢለፈፉም፣ ለውጥ አያመጡም። ቢዝነስ ውስጥ የመንግስት ድርሻ በተስፋፋ ቁጥር፣ የትርፍና የኪሳራ ስሌት፣ እየተቀዣበረና በብዥታ እየተዋጠ ይጠፋል። ከዚያስ? “ትርፍ እንደሌለው እያወቅን ነው፣ በድፍረት የገባንበት!” ተብሎ በግላጭ ሲነገር የምንሰማበት ደረጃ ላይ ደረስን።
እንዲያም ሆኖ፣ የፓርላማ አባላት፣ ከዓመታት ቆይታ በኋላ፣ ድንገት በቁጭት ተንገብግበው መጠየቃቸው አልቀረም - በአዲስ አበባ የባቡር ፕሮጀክት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በስኳር ፕሮጀክቶችም ላይ።
መጠየቃቸው ስህተት አይደለም። እንዲያውም ተገቢ ነው።
የስኳር ፕሮጀክቶች ለ10 ዓመት ተጓትተዋል። ብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት በከንቱ ባክኗል። ከአስሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ማጠናቀቂያ የተቃረበው። እሱም ግን አልተሳካም። በ20 ኪሎሜትር፣ በ30 ኪሎሜትር የተዘረጉ የመስኖ ካናሎች በጎርፍ ተወሰዱ... በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለ የግድብ ግንባታ 10 ዓመት ሞላው.. ገና ግንባታው ሳይጠናቀቅ፣ ጥገናና እድሳት፣ ማሻሻያና ክለሳ አስፈልጎት ተጓተተ...።
አዎ፣ የኋላ ኋላ፣ እንደምንም በሺ ሄክታሮች 100 ሚ ብር የሚያወጣ የስኳር አገዳ ይመረታል፤... ምን ዋጋ አለው? የስኳር ፋብሪካው ገና ስላለቀ፣ አገዳው እንዲቃጠል ይደረጋል። ይሄ የየዓመቱ አሳዛኝ ትዕይንት ሲሆን ይታያችሁ። ‘የስኳር ፋብሪካው ተጠናቀቀ’ ሲባል ደግሞ፣ የስኳር አገዳ የለም። ከዓመት በኋላ፣ ‘አገዳው ደረሰ’ ቢባልስ? ፋብሪካው ተበላሽቷል።... እንግዲህ፣ ይሄኛው ፕሮጀክት፣ ከሌሎቹ ቀድሞ የተጀመረና፣ በ10 ዓመት ሊጠናቀቅ የተቃረበ ነው። ከሰባ እስከ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ የፈሰሰባቸው ሌሎቹ ፕሮጀክቶች፣ ገና በጣም ገና ናቸው።...
የፓርላማ አባላት፣... ከስንት ዓመት በኋላ፣ ዘንድሮ፣ “ያሳዝናል... ያስቆጫል...” በማለት ስለ ስኳር ፕሮጀክቶች ጥያቄ ማቅረባቸው፣ መጥፎ አይደለም። ግን፣ ከማርስ የመጡ እንግዳ ቱሪስት መምሰልና ማስመሰል የለባቸውም። ለማንኛውም፣ የፓርላማ አባላት፣ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ለስኳር ኮርፖሬሽን ብቻ አይደለም፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር ነው።
•    የጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ የብልጥ ፖለቲከኛ ምላሽ!
የስኳር ፕሮጀክት የሚካሄድባቸው ቦታዎች፣... መግቢያ መውጪያ መንገድ የሌላቸው ሩቅ ቦታዎች ናቸው። እዚህ ፓርላማ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ እንደተወያየነው፤ ቦታዎቹ፤ ለመንገድ ስራ ያስቸግራሉ። ከፍተኛ የገንዘብ፣ የሙያና የተቋም አቅምን እንደሚጠይቁም፤ ፓርላማው ያውቃል። ለፕሮጀክቶቹ የሚመጥን አቅም የለንም። በዚያ ላይ በጥድፊያ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ናቸው። ትርፍና ኪሳራቸው ሳይሰላ፣ አዋጪ መሆን አለመሆናቸው ሳይጠና፣ በወጉ ዲዛይንና እቅድ ሳይወጣላቸው ነው በድፍረት የገባንባቸው።...
ይሄ፣ የጠ/ሚ ኃይለማሪያም ምላሽ ነው። በርካታ ፕሮጀክቶች፣ በስሌት ሳይሆን በድፍረት ተጀምረዋል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ችግርና ስህተት ቢከሰት፣ ኪሳራና ብክነት ቢፈጠር አይገርምም።... እንዲህ እውነታውን መናገራቸው ጥሩ ነው። እንደ ድሮው፣ “ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው ጊዜና እቅድ እየተከናወኑ ናቸው” የሚል የውሸት መግለጫ እየደጋገሙ መቀጠል ዋጋ የለውም። በእርግጥ፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ ጥፋት ሰርተናል ብለው እቅጩን አልገለፁም።  “ጥፋት ሰርተን ከሆነ...” ወይም “ጥፋት ስለሰራን...” የሚል መሸጋገሪያ ሳይጠቀሙ ነው፤ ንግግራቸውን የቀጠሉት። የተሰሩ ጥፋቶችን በቀጥታ እየዘረዘሩ፣ ጥፋት ሰሪዎችን ግን በውስጠ ታዋቂነት የሚጠቁሙና “ሁልሽም፣ ጥፋት ሰርተሻል” የሚሉ ይመስላል።   
ፓርላማውም እንደሚገነዘበው፣ ከዓመታት በፊት የፕሮጀክቶቹ ቦታ ሲወሰን፣ መግቢያ መውጪያ መንገድ እንደሌለው ይታወቅ ነበር። ለፕሮጀክቶቹ የሚመጥን አቅም እንደሌለን ይታወቅ ነበር። ትርፍና ኪሳራቸው በወጉ እንዳልተጠናና እንዳልታቀደ ይታወቅ ነበር።... ይህንን እያወቅን ነው፤ ደፍረን እንግባበት? ወይስ፣ አቅም ለመፍጠርና ጥናት ለማካሄድ ረዥም ዓመታትን መጠበቅ ይሻላል? እዚህ ፓርላማ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው፤ በድፍረት ገብተን እንስራ በሚል የተጀመሩ... የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ናቸው።...
እንዲህ ጫን አድርገው የተናገሩት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ ወደተለመደው “የቢሮክራሲ አገላለፅ” ተመልሰው፤ መደምደሚያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል - “በፕሮጀክቶቹ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ፤ ወደፊትም የፕሮጀክቶች ስራ በጥናትና በእቅድ እንዲመራ ለማድረግ...” የሚል አገላለፅ ማለቴ ነው።
•    “ሁልሽም፣ ጥፋት ሰርተሻል!”
ከጠ/ሚ ኃይለማሪያም ምላሽ ውስጥ የሚመዘዘው ዋናው ቁምነገር ምንድነው?
በፕሮጀክቶቹ ሳቢያ ለዓመታት ሲባክን የቆየው ሃብት በጣም ያሳዝናል፤ ያስቆጫል። የፓርላማ አባላትም፣ እጅጉን አዝነው በቁጭት ጥያቄ ቢያቀርቡ ተገቢ ነው። ነገር ግን፣ የዓመታት የብዙ ቢሊዮን ብር ብከነት፣... በስውር የተፈፀመ፣ በድብቅ የቆየ ሚስጥር አይደለም። የፕሮጀክቶቹ ምንነት፣ በ2003 ዓ.ም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ተገልጿል። በዚያን ወቅት፣ የስኳር ፕሮጀክቶቹ ላይ፣ ትችትና የማስተካከያ አስተያየት የሰነዘረ የፓርላማ አባል፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወይም ምሁር አልነበረም።
መንግስት፣ የስኳር ምርትና ቢዝነስ፣ በግል ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ አለማድረጉ ብቻ አይደለም ችግሩ። የኤሌክትሪክ ግድብ ላይ እንደሚደረገው እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በጨረታ ለግል ኩባንያዎችና ለስራ ተቋራጮች ቢሰጥ ይሻላል ብሎ ሃሳብ ያቀረበ የገዢው ፓርቲ የፓርላማ አባል ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛ አልነበረም። በመንግስት የተያዘ ቢዝነስና በመንግስት የሚካሄድ ግንባታ፣ ከኪሳራና ከብክነት ሊያመልጥ ይችላል ብለው ያስባሉ? የማይሆን ነገር!
ቢሆንም ግን፤ ቀደም ብለው በተጀመሩ ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ኪሳራዎችንና ብክነቶችን መነሻ በማድረግ፤ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ለማሰማት የሞከረ የለም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ፣ በመንግስት የስኳር ፕሮጀክቶች ኪሳራና ብክነት ዙሪያ ተከታታይ ዘገባዎችን ሰርቷል። የፌደራል ኦዲተር ደግሞ፣ በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ሪፖርቱን ለፓርላማ እንዳቀረበ ይታወቃል።
ስለዚህ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የፓርላማ አባላት፣ “አልሰማንም ነበር፤ አላየንም ነበር፤ አላወቅንም ነበር” ሊሉ አይችሉም። ዘንድሮ ድንገት ተነስተው፤ “ጉድ! ጉድ!” ለማለት የሚሞክር ካለ፤ ራሱን ከማታለል ያለፈ ቁምነገር አይኖረውም። ለነገሩ፣ የፓርላማ አባላት ብቻ ሳይሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ፣ በተለይም፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችም ሆኑ ተቺዎች፤... ዘንድሮ ከማርስ እንደመጣ ቱሪስት፣ “ጉድ! ጉድ!” ብሎ እሪታውን ቢያቀልጠው፤ ተጨማሪ ስህተትና ጥፋት ከማስመዝገብ የዘለለ ትርፍ የለውም። የመጀመሪያ ስህተቱና ጥፋቱ፤ ላለፉት 7 ዓመታት፣ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሲያልፍ መቆየቱ ነው።
ይልቅስ፤ “መንስኤው ምንድነው? ከዚህ በኋላስ ምን ይሻላል?” የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ማተኮር ይመረጣል። በእነዚሁ ጥያቄዎች ፋይዳ ወዳለው ሃሳብና ውይይት ... ወደሚቀጥለው ሳምንት ይዞራል።

Read 2765 times