Monday, 19 June 2017 09:12

“ለእኔ አባ ጃሜ ጫካ እንደ በኸር ልጄ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምር መዳረሻነት ከለያቸው ጉዳዮች መካከል ኪነ ጥበብና ጮቄ ተራራ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በተለይ ጮቄ ተራራ ላይ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ቡድን አቋቁሞ በስፋት እየሰራ ነው፡፡ ከተራራው 59 ወንዞችና 273 ምንጮች የሚፈልቁ ሲሆን 53ቱ ወንዞች በግዙፍነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ተራራ ላይ 141 ያህል የአዕዋፋት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን 21ዱ በኢትዮጵያ ብቻ፣ 16ቱ ደግሞ በዚሁ ተራራ ለይ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ በተራራው ላይ ከሚገኙት አዕዋፋት የ31ዱ ዝርያዎች ሊጠፉ መቃረባቸውን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የጮቄ ተራራ የምርምር ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ጌታነህ በላቸው ይገልፃሉ፡፡ ከጮቄ ተራራ ዝቅ ብሎ “አባ ጃሜ” የተሰኘ ጫካ የሚገኝ ሲሆን ደኑ አሁን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ቀድሞ በደን ከመጠቅጠቁ የተነሳ አያሌ የዱር እንስሳትና በርካታ አገር በቀል ዛፎች ይገኙበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ‹‹አባ ጃሜ›› ተከብሮና ተጠብቆእንዲዘልቅ በተለይ አንድ ግለሰብ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ ላለፉት 52 ዓመታት ደኑን
እንደ አብራካቸው ክፋይ ሲንከባከቡ ኖረው፣ ሲደክማቸው ለመንግስት አስረክበው ወደ ቤታቸው ገብተዋል - የ83 ዓመቱ አዛውንት አቶ አድማሴ መላኩ፡፡ እንዴትና ለምን ለብዙ ዓመታት ደኑን ጠበቁት? ምን ፈተናዎች ገጠሟቸው? አሁን ደኑ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? የአዲስ
አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከዕድሜ ባለፀጋው አቶ አድማሴ መላኩ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

     በዚህ ውርጫማ ማለዳ፣ በዚህ ደን አካባቢ ምን እያደረጉ ነው?
ከወረዳው “ለቃለ ምልልስ ትፈለጋለህ ቅረብ” ተብዬ ነው የመጣሁት፤ እስካሁን ያናገረኝም የለም፡፡
ቃለ- መጠየቁ በምን ጉዳይ ነው ተባሉ?
ደኑን ስጠብቅ ስለኖርኩ ይመስለኛል፡፡
ለ52 ዓመታት “አባ ጃሜ” ደንን ጠብቀዋል ይባላል፡፡ እንዴት ሊጠብቁ ቻሉ? ምንስ አነሳሳዎ?
ደኑን መጠበቅ የጀመርኩት በወጣትነቴ ነው፤ ከ52 ዓመት በላይ ነው የጠበቅኩት ዱሮ በአካባቢያችን ደን ስላልነበረ፣ ቤት ሲቃጠልብንም ሆነ አርጅቶ ሲፈርስ፣ እንጨት ለማምጣት የትናየት ርቀን ነበር የምንሄደው፡፡ ከዚያ በኋላ ለምን የራሳችን ደን አይኖረንም፤ ለምን አንጠብቅም ተባለና ስንመካከር፣ ‹ይህን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ማን ነው› ሲባል፤ ‹‹እኔ እጠብቃለሁ›› አልኩኝ፡፡ በቃ አብዛኛው እድሜዬ ከዚህ ደን ጋር ተቆራኘ፡፡ የሚገርምሽ … በጫካው የሚኖር በርካታ አውሬ አለ፤ ጅብ እንኳን ሲያየኝ አይተናኮለኝም ነበር፡፡
የት አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት?
እዚሁ ስናን ወረዳ፣ አባዛሽ ቀበሌ ነው ተወልጄ ያደግኩት፡፡
የ52 ዓመታት የጥበቃ ዘመንዎ ምን ይመስል ነበር?
እንግዲህ አቴጌ መነን ሲሞቱ እንኳን ይህን ደን እጠብቅ ነበር፤ ጫካውን ከብት እንዳይረግጠው፣ ሰው እንዳይጨፈጭፈው ስጠብቅ ኖሬያለሁ፡፡ ቀን ከሌሊት እጠብቅ ስለነበር፣ ብርዱ ውርጩ መቼም በላዬ ላይ ሲወርድብኝ ኖሯል፡፡ እንደምታይው… አካባቢው ከጮቄ ጀምሮ ወደዚህ ያለው ውርጫማ ነው (በጉብኝታችን ወቅት ከውርጩ የተነሳ እጃችን በድኖ አይታዘዝልንም ነበር፡፡)  ይህንን ሁሉ ፈተና ተቋቁሜ ነው የጠበቅኩት፡፡
በዚህ ደን ውስጥ ምን አይነት የዱር እንስሳትና የዛፍ አይነቶች ይገኛሉ?
ከዛፎቹ ውስጥ ኮሶ፣ አምጃ፣ አስታ፣ ወይራ … ኧረ ምኑ ቅጡ … ብዙ አይነት ዛፍ ነው ያለው። ከእንስሳት ደግሞ ቀበሮ፣ ዝንጀሮ፣ ነብር፣ ጅብና ሌሎች በርካታ አይነት የዱር አውሬዎች ይገኛሉ፡፡ ኧረ አንበሳም ሳይኖር አይቀርም አንቺዬ፡፡
መቼ ነው ደኑን መጠበቅ ያቆሙት?
በቅርብ ነው ያቆምኩት፡፡ እንደምታይኝ አረጀሁ። ‹‹ከ83 ዓመት በላይ ነው እድሜዬ … ደከመኝ ሰለቸኝ ተረከቡኝ” ብዬ ለመንግስት ሰጠሁና ወደ ቤቴ ገባሁ፤ አበቃ፡፡ አሁን እንደ ዘበኛ ሆነው በቡድን ይጠብቁታል መሰለኝ፡፡ እኔ ግን  ብቻዬን ነበር ስጠብቅ የኖርኩት፡፡
እርስዎ ጥበቃ ካቆሙ በኋላ ምን ለውጥ አዩበት?
እንደ ዱሮው አይመስለኝም፤ ትንሽ የተጎዳ ነገር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ እንኳን ይሄ ደን ጮቄም አሁን በጤናው አይደለም ሲባል እየሰማሁ ነው፡፡ መቼም ደኑ ችግር ቢያጋጥመው ሰው እየቆረጠው ነው ይባላል፡፡ ጮቄን ምን አይነት ችግር ሊገጥመው እንደቻለ አልተገለጠልኝም፡፡ በእርግጥ እንስሳት ወደ ደኑ አይቀርቡም፤ አውሬውም አያስደርሳቸውም፤ ነገር ግን ዙሪያው እየተረሳ ይመስለኛል፡፡ መቼም እስከ ዛሬ ደኑ አምሮበት የቆየው በእኔ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ከጮቄ ተራራ እንደልቡ በሚያገኘው ያልተቋረጠ ንፁህ ውሃ ነው፡፡ ጮቄ ተራራ እክል ገጥሞታል ከተባለ ደኑም ከችግር አይድንም፤ ይሄ ያሳዝነኛል፡፡
እዚህ ቁጭ ብለው ደኑን አሻግረው ሲመለከቱት ምን ይሰማዎታል?
አወይ ልጄ! በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ‹‹አባጃሜ ጫካ›› ለእኔ እኮ እንደ በኸር ልጄ፣ እንደ አብራኬ ክፋይ ነው የማየው፡፡ ከዚህ ጫካ ጋር ስነጋገርና ስወያይ ስንት ዘመን አሳለፍኩ መሰለሽ (በዱላቸው የተቀመጡበትን መሬት እየተመተሙ ተከዙ) እና ሳየው ደስ ይለኛል፤ እኮራለሁ፤ እንደተጠበቀና እንደታፈረ ቢቀጥል ነው የምወድ፡፡
ትዳር መስርተዋል… ልጆች አፍርተዋል?
አዎ ትዳርም ልጆችም አሉኝ፤ አድገው ትልልቅ ሆነዋል፡፡
የእርስዎን ፈለግ ተከትሎ ‹‹ደኑን እጠብቃለሁ›› ብሎ የተነሳ ልጅ የለዎትም?
 አይ! የለም፡፡ ሁሉም በየፊናው ኑሮውን ይመራል እንጂ ደን እጠብቃለሁ ብሎ የተነሳ የለም፡፡
ከደን ጥበቃ ዘመንዎ የማይረሱት ገጠመኝ ይኖራል?
ብዙ የማይረሳኝ አለ፡፡ እኔ ኑሮዬን ልጆቼን ትቼ ነው፣ ይህን ደን ስጠብቅ የኖርኩት፡፡ አንድ ጊዜ “ደኑን እንቆርጣለን፤ አትቆርጡም” በሚል ከአካባቢው ሰዎች ጋር ግብግብ ገጥሜ እንዳይቆርጡ ብከለክላቸው፣ በሌሊት መጥተው የሳር ቤቴን በላዬ ላይ እሳት ለቀቁበት፤ ቤት ንብረቴ በእሳት ሲነድ፣ እኔ ከእነቤተሰቤ አመለጥኩኝ፡፡ ያን ቤት ለመስራትና ንብረቴን ለመተካት ብዙ ዓመት ፈጅቶብኛል። ምክንያቱም ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው በዚህ ደን ጥበቃ ላይ ነው፡፡ ይሄን መቼም የምረሳው አይሆንም።
ከዚህ ደን ውጭ በአካባቢው ሌላ ጥብቅ ደን አለ?
ሌላ እንኳን የለም፤ እኔ አላውቅም፡፡ በዚህ አካባቢ ያለው ይሄው “አባ ጃሜ” ብቻ ነው፡፡
ለዚህ ውለታዎ እስካሁን የሸለመዎ ወይም ያመሰገንዎ የመንግስት ወይም የግል ተቋም የለም?
 ምንም የተሰጠኝ ነገር የለም፡፡ እስካሁን ያየሁት ነገር የለም፡፡ ዛሬም የጠሩኝ የቃል ጥየቃ ትጠየቃለህ ብለው ነው፡፡ (በስናን ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እሳቸው ጫካ ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ ብቻ የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ ተመልክተናል፡፡) አሁን እኔ እድሜዬም ስለገፋ እቤቴ ቁጭ ብዬ ነው ያለሁት፡፡
ደኑ ምን ጥቅም አለው ብለው ነው ይህን ያህል ዘመን ሲጠብቁት የኖሩት?
አይ የኔ ልጅ … አሁን የደን ጥቅም ለአንቺ ጠፍቶሽ ነው የምትጠይቂኝ፤ ሌላውን ተይው… ደን ሲከፋሽና ሲመርሽ ሄደሽ ትጠለይበታለሽ፤ ነገሩ ከዚህ በላይ ጥቅም አለው፤ ደን እኮ ለመንደሩም ግርማ ሞገስ ነው፡፡ ለዚህ ነው አገሩን ወክዬ ኑሮዬን ትቼ ስጠብቀው የኖርኩት፡፡ አሁንም መንግስት ተረክቦኛል፤ እንደኔ አድርጎ እንዲጠብቀው አደራዬን አስተላልፋለሁ፡፡ እኔ የራሴን ድርሻ ተወጥቼ እዚህ አድርሸዋለሁ፡፡ ስላነጋገርሽኝ አንቺም ተባረኪ የኔ ልጅ፡፡

Read 1712 times